ሀርቪ ዋንስታይን 44 ሚሊየን ዶላር ካሳ ሊከፍል ነው

ሀርቪ ዋይንስታይን Image copyright Getty Images

ሀርቪ ዋንስታይን በወሲባዊ ጥቃት ለከሰሱት ሴቶች 44 ሚሊየን ዶላር ካሳ ለመክፈል መስማማቱን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል። ፊልም ፕሮዲውሰሩ ሀርቪ በርካታ የፊልም ባለሙያ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሷል በሚል መከሰሱ ይታወሳል።

ገንዘቡን ክስ ያቀረቡት ሴቶች እንደሚካፈሉት የተገለጸ ሲሆን፤ የሴቶቹ ማንነት እስካሁን ይፋ አልተደረገም። ዋልስትሪት ጆርናል እንደዘገበው፤ ካሳው ሀርቪ በአሜሪካ፣ እንግሊዝና ካናዳ ለቀረበበት ክስ ነው።

ሀርቪ የፊታችን ሰኔ ኒው ዮርክ የሚገኝ ፍርድ ቤት የሚቀርብ ሲሆን፤ ከቀረቡበት ክሶች መካከል አስገድዶ መድፈር ይገኝበታል። የፊልም ፕሮዲውሰሩ 75 ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ ቢከሰስም መካዱ ይታወሳል። ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የእድሜ ልክ እስራት ይጠብቀዋል።

በሀርቪ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው በይፋ ከተናገሩ ተዋንያን አንዷ አሽሊ ጁድ በበኩሏ ሀርቪን በግሏ ፍርድ ቤት እንደምታቆመው በትዊተር ገጿ አሳውቃለች።

'ሼክስፒር ኢን ላቭ'፣ 'ዘ ኪንግስ ስፒች'፣ 'ዘ አርቲስት' እና ሌሎችም ስኬታማ ፊልሞች ፕሮዲውስ ያደረገው የ67 ዓመቱ ሀርቪ፤ በሠራቸው ፊልሞች በአጠቃላይ 81 የኦስር ሽልማት አግኝቷል።

ቢል ኮዝቢና ፖላንስኪ ከኦስካር አካዳሚ ተባረሩ

እንደ ጎርጎራሳውያኑ አቆጣጠር በ1970 'ሚራማክስ ኢንተርቴይመንትን' አቋቁሞ ነበር። 2005 ላይ ከወንድሙ ቦብ ዋንስታይን ጋር 'ዋንስታይን ሶኦ' መስርቷል። 2017 ላይ ኳርትዝ ባቀረበው ዘገባ ሀርቪ በሆሊውድ ስሙ ከመግነኑ የተነሳ፤ የኦስካር ሽልማት ሲይገኙ ፈጣሪን ከሚያመሰግኑ የፊልም ባለሙያዎች ይልቅ ሀርቪን የሚያመሰግኑት ባለሙያዎች ቁጥር ይበልጥ ነበር።

ሆኖም በርካታ የሆሊውድ የፊልም ባለሙያ ሴቶች ሀርቪ ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሰባቸው ሲናገሩ ክብርና ዝናው ተገፏል።

Image copyright Getty Images

ኒው ዮርክ ታይምስ 2017 ላይ ሀርቪ ወሲባዊ ጥቃት ስላደረሰባቸው ሴቶች ዘገባ አቅርቦ ነበር። አሽሊ ጁድና ሮዝ መግዋን ሀርቪ ያደረሰባቸውን ጥቃት በይፋ ከተናገሩ ግንባር ቀደም ሴቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

ከቀረቡበት ክሶች መካከል ሴቶች እርቃኑን እንዲያዩትና ማሳጅ እንዲያደርጉት ማስገደድ ይገኝበታል። ለሦስት አስርት ዓመታት ሴቶች ላይ ጥቃት ማድረሱን የካደው ሀርቪ፤ "ያሳዘንኳቸውን ሰዎች ይቅርታ እጠይቃለሁ" ማለቱ ይታወሳል።

ሀርቪ ላይ የቀረበው ክስ 'ሚቱ' ንቅናቄ ለመነሳቱ ምክንያት ሲሆን፤ በርካታ ሴቶች በተለያየ ሙያ ላይ የተሰማሩና ወሲባዊ ጥቃት ያደረሱባችን ወንዶች በይፋ ለመክሰስ ድፍረት ያገኙበት እንቅስቃሴ ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ