ፌስቡክ የአፍሪካ የዴሞክራሲ ሥርዓት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው?

ሙሀመዱ ቡሀሪና ማርክ ዙከርበርግ Image copyright AFP

ፌስቡክ ወቀሳ በዝቶበታል። በተለይም ከአህጉረ አፍሪካ።

በማኅበራዊ ሚዲያው የሚሰራጨውን ሀሰተኛ መረጃ መግታት እንዳልቻለ ተንታኞች ይናገራሉ። የአህጉሪቷን የዴሞክራሲ ሥርዓት አደጋ ውስጥ ከቷልም ተብሏል።

"የአደገኛ ግለሰቦች" የፌስቡክ ገጽ መዘጋት ጀመረ

ሀሰተኛ ዜናዎች አፍሪካ ውስጥ በተካሄዱ ስምንት ምርጫዎች ላይ ተጽዕኖ ማድረጋቸው የተነገረ ሲሆን፤ ፌስቡክ ከዜናው ጀርባ ነበረ ያለውን የእስራኤል ተቋም ገጽ መዝጋቱ ይታወሳል።

'አርኪሜይድ ግሩፕስ' የተባለው የእስራኤል ተቋምን ጨምሮ 256 የፌስቡክና ኢንስታግራም ገጾች ታግደዋል። በእነዚህ ገጾች ይሰራጭ የነበረው መረጃ በዋነኛነት ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ቶጎ፣ አንጎላ፣ ኒጀርና ቱኒዚያ ላይ ያነጣጠረ እንደነበረ ፌስቡክ ይፋ አድርጓል።

ፌስቡክ ሦስት ቢሊዮን አካውንቶችን አገደ

የ 'ወርልድ ዋይድ ዌብ ፋውንዴሽን' ሠራተኛ ናኒንጃ ሳምቡሪ፤ ፌስቡክ እርምጃውን ለመውሰድ ዘግይቷል ይላሉ። "የአህጉሪቷ የዴሞክራሲ ሥርዓት አደጋ ውስጥ ነው። ጥብቅ የመረጃ ደህንነት መቆጣጠሪያ አለመኖሩ አንዱ ችግር ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

አፍሪካና ፌስቡክ

የካሜሩን የቴክኖሎጂ ባለሙያ ሬቤካ ኤኖንችሆን እንደሚናገሩት ፌስቡክ አፍሪካ ውስጥ ያለው አሠራር ከተቀረው ዓለም የተለየ ነው። ለምሳሌ፤ ፌስቡክ በ 'ካምብሪጅ አናሊቲካ'ው አጋጣሚ አፍሪካ ውስጥ እምብዛም አልተወቀሰም።

እንደ ጎርጎራሳውያኑ አቆጣጠር 2018 ላይ ከ230 ሚሊየን በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የግል መረጃ ተመዝብሮ፤ የምርጫ ሂደት ውጤት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር መዋሉ ይፋ መደረጉ ይታወሳል። ምርጫ ከተካሄደባቸው አገሮች መካከል ናይጄሪያና ኬንያ ይገኙበታል።

ፌስቡክ ግላዊ መረጃን አሳልፎ በመስጠት ተከሰሰ

ፌስቡክ አፍሪካ ላይ የተቃጡ ገጾችን መዝጋቱን ሲያሳውቅ፤ የኮንጎው ጦማሪ ሳይመን ንኮላ ማታምባ አንድ ጥያቄ ሰንዝሮ ነበር። "ፌስቡክ በሌሎች አህጉሮች ላይ ለማድረግ የማይደፍረውን ነገር አፍሪካ ውስጥ የሚያደርገው ለምንድን ነው?" የሚል።

መነሻቸው ከእስራኤል ነበር የተባሉት ገጾች ሥራቸውን ለማከናወን ከ2012 እስከ 2019 812,000 ዶላር አወጥተዋል። 2.8 ሚለየን ተከታዮች አፍርተውመ ነበር።

ቢቢሲ 'አርኪሜይድ ግሩፕስ' ከተባለው ተቋም ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። በገጹ ላይ የነበሩ መረጃዎችንም ሙሉ በሙሉ አስወግዷል። ከተወገዱት መረጃዎች ውስጥ የናይጄሪያ ምርጫ ላይ ያተኮሩት ይጠቀሳሉ።

ፌስቡክ አፍሪካ ላይ የተቃጡ ገጾችን ዘጋ

የአሜሪካው የምርምር ተቋም 'ዘ አትላንቲክ ካውስል ዲጂታል ፎረንሲክ ሪሰርች ላብ' በሠራው ጥናት እንደተመለከተው፤ የቀድው የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዘዳንት አቲኩ አቡበከርን ስም የሚያጠለሽ ምስል ተሰራጭቷል።

'ሴንተር ፎር ዴሞክራሲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት' የተባለው አቡጃ የሚገኝ ተቋም ውስጥ የሚሠሩት ኢዳት ሀሰን እንዳሉት፤ ምስሎቹ ከየት እንደመነጩ ማወቅ አልተቻለም።

ፌስቡክ ከዘጋቸው ገጾች አንዱ 'ጋና 24' ይባላል። የዜና ማሰራጫ ገጽ ቢመስለም መረጃው ይተላለፍ የነበረው ከእስራኤልና እንግሊዝ ነበር። በዴሞክራቲክ ኮንጎ ብሔራዊ ምርጫ ወቅት ፌሊክስ ተሺስኬይዲን የሚደግፍ መረጃ የሚሰራጫበት ገጽም ነበር።

እነ ፌስቡክ ግላዊ መረጃዎትን ያለአግባብ እንደሚጠቀሙበት ያውቃሉ?

በእርግጥ በነዚህ ገጾች የሚሰራጨው ሀሰተኛ ዜና በመንግሥት ለውጥ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የሚያሳይ መረጃ የለም። እንዲያውም የአፍሪካ መሪዎች የሀሰተኛ መረጃ ስርጭቱን ሳይጠቀሙበት አልቀሩም።

አደገኛውን የሀሰተኛ መረጃ ርጭት ለመግታት

አፍሪካ ውስጥ ከ139 ሚሊየን በላይ ሰዎች ፌስቡክን በዋነኛነት በስልክ ይጠቀማሉ። አብላጫውን ቁጥር የያዙት ደግሞ ወጣት አፍሪካውያን ናቸው። በምርጫ ወቅት ድምጽ ከሚሰጡ ዜጎች ብዙዎች ወጣቶች እንደመሆናቸው በፌስቡክ የሚሠራጭ መረጃ በቀላሉ ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል።

የካሜሩኗ የቴክኖሎጂ ባለሙያ ሬቤካ እንደሚናገሩት፤ እነዚህ ወጣቶች የሚያገኙት መረጃ ምንጩ ፌስቡክ እንደሆነ ያምናሉ። ፌስቡክን በመጠቀም ሦስተኛ ወገን መረጃ ሊያሠራጭ እንሚችል አይገምቱም። ባለሙያዋ "ፌስቡክ ኃላፊነት ተሰምቶት በማኅበራዊ ሚዲያው የሚሰራጨውን መረጃ መቆጠጠር ግዴታው ነው" ይላሉ።

Image copyright AFP

ፌስቡክ የትራምፕን ክስ ውድቅ አደረገ

አፍሪካ ውስጥ ያሉ ያሉ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ማኅበራዊ ሚድያውን እንዴት ይገለገሉበታል? የሚለውን ጉዳይ ፌስቡክ በአንክሮ እንዲመለከት ባለሙያዋ ያሳስባሉ። ቢቢሲ ይህንን አስተያየት ለፌስቡክ ቢሰጥም ተቀባይነት አላገኘም።

ፌስቡክ እንዳለው፤ ተቋሙ አፍሪካን 'እንደ ቤተ ሙከራ' አድርጓታል የሚለው ክስ ተቀባይነት የለውም። በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት አፍሪካ ላይ ከፍተኛ ገንዘብ እያፈሰሰ በመሆኑን ያክላል።

ፌስቡክ የየአገራቱ ቋንቋ የሚችሉ ባለሙያዎች ከመቅጠር ባሻገር ፓሊሲ ማውጣቱን ይገልጻል። የሀሰተኛ ዜና ሥርጭትን ለመገደብ፤ በፌስቡክ የሚሰራጪ መረጃዎችን የሚገመግም ተቋም በኬንያ መዲና ናይሮቢ እንደሚያቋቁምም አክሏል። በተቋሙ ውስጥ የኦሮምኛ፣ ሶማልኛ፣ ስዋሂሊና ሀውሳ ተናጋሪዎች ይቀጠራሉ።

ግጭትን ለማባባስ ፌስቡክ ጥቅም ላይ ውሏል ተባለ

በተጨማሪም ካሜሩን፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካና ሴኔጋል ውስጥ መረጃ ከሚያጣሩ ድርጅቶች ጋር ተጣምሮ እንደሚሠራ ተመልክቷል።

ፌስቡክ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት ስለሰተኛ መረጃ አደገኛነት ያዘጋጃቸውን ጽሁፎች በጋዜጣ አስነብቧል። ጥያቄው ፌስቡክ የሚጠበቅበትን ሁሉ አድርጓል ወይ? ነው።

አፍሪካ ውስጥ ምርጫ በተካሄደ ቁጥር ዜጎች ማኅበራዊ ሚድያ እንዳይቋረጥባቸው ይሰጋሉ። በፌስቡክና በዋትስአፕ የሚሰራጭ ሀሰተኛ መረጃ ለማስቆም የሚወሰድ እርምጃ እንደሆነም ይነገራል።

ጋናዊው የቴክኖጂ ምሁር ኩዋቤና አኩማኦህ-ቦቴንግ እንደሚናገሩት፤ ፌስቡክን ማገድ ብቻውን ለውጥ አያመጣም። "ስለአንድ ተቋም ብቻ የምናወራ ከሆነ ውጤታማ አንሆንም። መንግሥትና የደህንነት ተቋሞን ሚናም ማየት አለብን" ይላሉ

ባለንበት የመረጃ ዘመን የሀሰተኛ ዜና ስርጭትን ለመግታት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሌሎችም የሚመለከታቸው ተቋሞች መተባበር እንዳለባቸውም ያስረዳሉ።