"የግንቦት 20 ታሪካዊነት አጠያያቂ አይደለም" ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ Image copyright ALEXANDER JOE

ግንቦት 20 እንደዘንድሮ አከራካሪ የሆነበት ጊዜ ያለ አይመስልም። በዓሉ አምባገነኑ የደርግ ሥርዓት የተወገደበትና ኢትዮጵያ ወደዲሞክራሲ ሥርዓት የተሸጋገረችበት ዕለት በመሆኑ በድምቀት መከበሩ መቀጠል አለበት የሚሉት እንዳሉ ሁሉ፤ ይህ ቀን ወንድም ወንድሙን ገድሎ ሥልጣን የያዘበት ዕለት ነው፤ ወደሥልጣን የመጣውም ሌላ አምባገነን ሆኖ እንዴት ክብረ በዓል ይሆናል የሚሉም አሉ።

በሰሜን አሜሪካ የትግራይ ተወላጆች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ አሉላ ሰለሞን በዓሉን ማክበር አለብን ከሚሉት ወገን ናቸው። ምክንያታቸውን ሲጠቅሱም የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት አብቅቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ሰላም የተሻጋገረበት ነው ይላሉ።

አክለውም "ኢትዮጵያ እንደ አገር ወደአዲስ ፖለቲካዊ ምዕራፍ የተሸጋገረችበት ነው የሚለውን አብዛኛው ሰው ይስማማበታል። ተከትሎ በመጣው ፖለቲካዊ ሥርዓት ስምምነት ባይኖርም መሠረታዊ በሆኑ እውነታዎች መለያየት የሚቻል አይመስለኝም" በማለት ያለው የፖለቲካ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ቀኑ መከበር አለበት ይላሉ።

"ጥቃት የደረሰባት ሴት ከግንኙነቱ ለመውጣት 10 ዓመት ይፈጅባታል"

ከሰላሳ በላይ የጴንጤ ቆስጣል አማኞች አሥመራ ውስጥ ታሰሩ

ኮሎኔል መንግሥቱ ለህፃናት አምባ ልጆች ደብዳቤ ላኩ

አቶ አሉላ በዓሉ መከበር የለበትም የሚሉ ወገኖችንም ሀሳብ አከብራለሁ ያሉ ሲሆን፤ ሁሉም በግንቦት 20 ድል ደስተኛ እንደማይሆን አንደሚረዱም ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በአገሪቱ የፕሬስ ነፃነት ባልነበረበት ወቅት በግንቦት 20 የተገኘው ድል ለፕሬሱ ነፃነት የሰጠ ዕለት መሆኑንም ይጠቅሳሉ።

በሂደት ፕሬሱም ሆነ ዲሞክራሲው ማደግ በነበረበት መጠን አላደገም የሚለው ሌላ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ የሚቆይ ነው የሚሉት አቶ አሉላ፤ በታሪክ ግን ነፃ ፕሬስ በኢትዮጵያ ውስጥ የመጣበት መሆኑ እንደማይካድ ይጠቅሳሉ።

ጋዜጠኛና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚጽፉት አቶ ደጀኔ ተሰማ በበኩላቸው፤ ግንቦት 20 ''አምባገነን መንግሥት ተገርስሶ ሌላ አምባገነን መንግሥት ወደሥልጣን የመጣበት ቀን ቢሆንም በዚህኛው መንግሥት ለውጦች እንደመጡ እረዳለሁ'' ይላሉ።

ደርግ መስከረም 2 ብሎ ሲያከብረው በነበረው በዓል እና ኢህአዴግ ግንቦት 20 ብሎ በሚያከብረው በዓል መካከል ምንም አይነት ልዩነት አይታየኝም የሚሉት አቶ ደጀኔ፤ ደርግ መሬት ላረሹ የሚለው የሕዝብ ጥያቄ መመለስ መቻሉን አስታውሰው፤ የግንቦት 20 ድልን ተከትሎ የመጣ ለውጥ ቢኖርም የለውጡ ተጠቃሚ የሆኑት ''ድሉ የኛ ነው የሚሉት ወገኖች ናቸው'' ይላሉ።

የቀድሞው ግንቦት 7 አርበኞች ግንባር አመራር የነበሩት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ደግሞ በዓል የሚከበረው ለሕዝብ ነው፤ ሕዝብ ካላከበረው አልተቀበለውም ማለት ነው ስለዚህ መከበር የለበትም ባይ ናቸው።

"ትንሽ ልጅ እያለሁ መስከረም 2 ይከበር ነበር" የሚሉት አቶ ኤፍሬም፤ ይህ የፊውዳሉ ሥርዓት የተገረሰሰበት በዓል በመሆኑ ትልቅ በዓል ነበር ይላሉ።

ሕወሐት ሥልጣን ሲይዝ ይህንን በዓል ማክበር አቁመን እነሱ የገቡበትን ቀን ማክበር ጀመርን በማለት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት 20 ዓመታት ያለፈችበትን ሁኔታ ማሳያ በመሆኑ "የሚፈጥርብኝ ስሜት ጥሩ አይደለም" ይላሉ።

አቶ ኤፍሬም "ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የለውጥ ሂደት ራሳቸውን አግልለው አሁንም የሚያስቡት ኢትዮጵያን ወደኋላ መመለስ ነው" ይላሉ። አክለውም "እነሱ የቆሙለትን ዓላማና አሁንም የሚታገሉለትን ዓላማ ስመለከት መከበር የለበትም እላለሁ" በማለትም ሀሳባቸውን ይቋጫሉ።

ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ በበኩላቸው የ17 ዓመቱ ጦርነት የአንድ እናት ልጆች የተጋደሉበት፤ የተዋደቁበት ጦርነት ነው ይላሉ። በዓሉ መድፍ እየተተኮሰ መከበሩ "ከመጀመሪያውም ደስ አላለኝም" በማለት፤ ወደፊትም መከበር ካለበት እስከዛሬ ይከበር እንደነበረው መሆን የለበትም ሲሉ ምክራቸውን ይሰጣሉ።

ፕሮፌሰር ገብሩ ግንቦት 20 እንደ በዓል ባይቆጠርም ታሪካዊነቱ አጠያያቂ አይደለም ይላሉ።

አቶ ደጀኔ በበኩላቸው ግንቦት 20 ልንጠየፈውም ሆነ ልናወድሰው የሚገባ ቀን አይደለም የሚል ሃሳብ ይሰነዝራሉ።