ባህር ዳር፡ ለተጎዱ ህጻናት ሴቶች መጠለያ የሆነው ማዕከል

ከጀርባዋ የምትታይ ታዳጊ

ሰላም (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስሟ የተቀየረ) ባህር ዳር የደረሰችው ከዘጠኝ ወራት በፊት ነበር። የ14 ዓመቷ ታዳጊ ከቤት ለመውጣት የተገደደችው ከአባቷ ጋር አለመግባባት በመፈጠሩ ነው።

ጓደኛዋ፤ ከመኖሪያ ቀያቸው ጠፍተው ባህር ዳር ቢሄዱ ሥራ እንደሚያገኙና ራሳቸውን ችለው መኖር እንደሚችሉ ደጋግማ ነግራታለች። "ጓደኛዬ እንጥፋ ስትለኝ ስለነበር፤ አባቴ 'ትምህርት ተማሪ' ሲለኝ አልማርም ብዬው ነበር" ትላለች።

ጓደኛዋ ባህር ዳርን ስለምታውቃት አብረው ወደ ባህር ዳር ከኮበለሉ በኋላ ሰው ቤት በሞግዚትነት የመቀጠር ሀሳብ እንደነበራቸው ትናገራለች። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ውሳኔዋ ትክክል አለመሆኑን በመረዳት ሃሳቧን ቀየረች።

"በወንድሜ ለአምስት ዓመታት ተደፍሬአለሁ"

"አባቴን ልማር ስለው መልሶ እምቢ አለኝ" ስትል አለመግባባታቸው እንዴት እንደተጀመረ ታስረዳለች። አለመግባባታቸው አይሎም ከጓደኛዋ ጋር የተስማማችበትን ሀሳብ እንድትተገብር አስገደዳት።

ውሳኔዋን ከግብ ለማድረስ እንዲረዳትም ከቤት ገንዘብ ይዛ ወጣች።

"ብሩን ይዤ ከጓደኛዬ ጋር ከአካባቢዬ ጠፋሁ፤ ጓደኛዬ ደግሞ ብሩን ይዛብኝ ጠፋች።" የምትለው ሰላም በዚህ ሁኔታ አጣብቂኝ ውስጥ ገባች። ወደ ቤተሰቦቿ እንዳትመለስ ገንዘብ ወስዳ መውጣቷ ሊያመጣባት የሚችለው መዘዝ አስፈራት።

ወደ ባህር ዳር እንዳትሄድ ደግሞ ለመጓጓዣ የሚሆን ገንዘብ ስለሌላት አውጥታ አውርዳ የቀራትን ብቸኛ አማራጭ ለመጠቀም ወሰነች - ወደ ሌላ ከተማ ሄዶ ሥራ መቀጠር።

ሌላ ከተማ ሄዳ ሥራ መሥራት ጀመረች፤ እየሰራች ገንዘብ በማጠራቀም ከቤተሰቦቿ ይዛ የተሰወረችውን ገንዘብ በገበያተኛ በኩል መልሳ ላከችላቸው። ሰላም አሁን ከእዳ ነፃ መሆኗ እፎይታን ሰጥቷታልና ስለቀጣይ ጉዞዋ ማውጠንጠን ጀመረች።

ለትራንስፖርት የሚበቃ ገንዘብ ካጠራቀመች በኋላ ጉዞዋን ስታልማት ወደነበረችው ባህር ዳር አደረገች። ባህር ዳር የምታወቀው ሰው አልነበራትም። ከተማዋን እንደምታውቅ የነገረቻት ጓደኛዋም ገንዘቧን ይዛ ተሰውራለች። ብቸኛ ተስፋዋ ሲወራ እንደሰማችው በደላላ በኩል ሥራ መቀጠር ነው።

"ባህር ዳር እንደመጣሁ ደላላው ወደ ቤቱ ወሰደኝ፤ በዚያው በመጀመሪያ ቀን ማታ አስገድዶ ደፈረኝ" ስትል በሃዘን ተሞልታ የደረሰባትን መከራ ትገልጻለች።

ደላላው ለማንም ምንም እንዳትናገር አስጠንቅቆ በቀጣዩ ቀን ሥራ አስቀጠራት። እሷም የሆዷን በሆዷ አድርጋ ሥራዋን መሥራት ጀመረች። ምግብ ቤት ውስጥ ለሁለት ወራትና በግለሰብ መኖሪያ ቤት ደግሞ ለሦስት ወር መሥራቷን ትናገራለች።

"በሀገራችን ከሶስት ሴቶች አንዷ ላይ ጾታዊ ጥቃት ይደርሳል"

ሥራው እንዳሰበችው ቀላል አልነበረም። በ14 ዓመት ታዳጊ አቅም የሚቻል አልሆነም። በተቀጠረችበት መኖሪያ ቤት የሚደርስባት ስቃይ ከድጡ ወደ ማጡ ሆነባት።

"ሥራው በጣም ከባድ ነው፤ ታስርበኛለች፤ ለምን እንደሆነ አላውቅም" ትላለች ስለአሠሪዋ ስትገልጽ።

ሥራ ለመቀየር አስባ ቀጣሪዋ የሠራችበትን ገንዘብ እንድትሰጣት በተደጋጋሚ ብትጠይቅም በምላሹ ትደበድባት እንደነበረ ትናገራለች።

"ካስፈለገ ለፖሊሶች 'ብሯን ሰጥቻታለሁ' ብዬ አስመሰክራለሁ" አለችኝ የምትለው ሰላም ቀጣሪዋ ለአንድ ሾፌር ከፍላ 'ወደማታውቀው ቦታ ውሰዳት' ብላ እንደነገረችው ትገልፃለች። እሱ ግን የወሰዳት ፖሊስ ጣቢያ ነበር።

ፖሊስም ቃሏን ከተቀበለ በኋላ በከተማው የሚንቀሳቀሰው የጎዳና ተዳዳሪ ሴት ህጻናት መከላከያ፣ ተሃድሶና መቋቋሚያ ድርጅት አስገባት።

ድርጅቱ ሰላምን ጨምሮ የጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ህጻናትን እና ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን ማገዝ ከተጀመረ ከ10 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።

ሰላም ወደ ድርጅቱ ከገባች በኋላ የልብስ፣ የምግብ፣ የመኝታ እና የሥነ ልቦና ድጋፍ እየተሰጣት ነው።

"እዚህ እንደመጣሁ በጣም ጨንቆኝ ነበር፤ ለቤተሰቦቼ ሲደወልም 'አንፈልጋትም' ብለዋል አሉ፤ እኔ ይህንን አላወቅኩም። 'አይወስዱሽም' ብለው ሲነግሩኝ ልጠፋ አስቤ በመስኮት ዘልዬ ወጥቼ ሁሉ አውቃለሁ" ትላለች እንባ እየተናነቃት።

የተነጠቀ ልጅነት

በድርጅቱ የሚሰጣት የማማከር አገልግሎት ድርጅቱ ውስጥ ተረጋግታ እንድትኖር ከማድረግ ባለፈ፤ የደረሰባትን አስገድዶ መደፈር ለመጀመሪያ ጊዜ እንድትናገር አድርጓታል። ከማማከሩ በተጨማሪ በመደፈሯ ያጋጠማት የጤና እክል ካለ በሚል ምርመራ ተደርጎላታል።

"አስመርምረውኝ ጤነኛ ነሽ ተብያለሁ" ትላለች።

ወይዘሪት ሠናይት ገዳሙ የጎዳና ተዳዳሪ ሴት ህጻናት መከላከያ፣ ተሃድሶና መቋቋሚያ ድርጅት ውስጥ በአማካሪነት ያገለግላሉ። ያለዕድሜ ጋብቻና ወሲባዊ ትንኮሳ የደረሰባቸው ሴቶች በብዛት ወደ ድርጅቱ እንደሚሄዱ ያስረዳሉ።

"ያለዕድሜያቸው የተዳሩ ልጆች ቤተሰቦችን በማስመጣት እናማክራለን። ህጻናት መማር እንዳለባቸው ነግረን፣ ቤተሰቦቻቸው እንዳይድሯቸው ቃል አስገብተን ልጆቹን ከቤተሰቦቻቸው ጋር አንቀላቅላቸዋለን። ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ህጻናት የሕግ ከለላ አግኝተው ፍትህ አንዲያገኙ እናደርጋለን። ሴቶቹን በማጽናናትና በማማከር ጉዳዩን ረስተው የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ እናግዛለን።" ሲሉ በድርጅቱ የሚያከናውኗቸውን መሰረታዊ ሥራዎች ይጠቅሳሉ።

ወይዘሪት ሠናይት እንደሚሉት ክትትሉ በማዕከሉ ብቻ አይቆምም። ወደ ቤተሰቦቻቸው አሊያም አሳዳጊዎቻቸው ከተቀላቀሉ በኋላም ልጆቹ ትምህርት ስለመጀመራቸውና ስላሉበት ሁኔታም ክትትል ያደርጋሉ።

ከጥር ጀምሮ ባሉት ሦስት ወራት ብቻ 38 ሴቶች ወደ ድርጅቱ የሄዱ ሲሆን፤ በዓመት በአማካይ እስከ 150 ሴቶችን ተቀብለው ያስተናግዳሉ። ህጻናቱን ወደ ድርጅቱ የሚወስደውም ፖሊስ ነው።

ቀኝ እጇን ለገበሬዎች የሰጠችው ኢትዮጵያዊቷ ሳይንቲስት

የባህር ዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሴቶች ህጻናትና ሌሎች ለጉዳት ተጋላጭ ወገኖች ድጋፍና እንክብካቤ አስተባባሪ የሆኑት ዋና ሳጅን መለሰ ዓለሙ እንደሚሉት፤ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን በተመለከተ የሚሠሩ ሴት ፖሊሶች በሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች አሉ።

"በሕገ ወጥ ዝውውር ሲመጡ የምናገኛቸውን ህጻናትም ሆነ ህብረተሰቡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሚልካቸውን ወደ ድርጅቱ እንልካቸዋለን፤ በድርጅቱ የሚሠራው ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማቀላቀል ሥራ ነው" ይላሉ።

ዘመድ የሌላቸው ልጆች በማዕከሉ ትምህርት እንዲከታተሉ የሚደረግ ሲሆን፤ ዕድሜያቸው ለሥራ የደረሱ ግለሰቦች ለአደጋ በማይጋለጡበት ቦታ እንዲሠሩ ምክር ይሰጣቸዋል።

በጎዳና ተዳዳሪ ሴት ህጻናት መከላከያ፣ ተሃድሶና መቋቋሚያ ድርጅት የባህር ዳር ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ግዛው ድርጅቱ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ የህጻናቱን መሠረታዊ ፍላጎት ከማማሏት ባለፈ የሥነ ልቦና ድጋፍ እንደሚሰጥ ይናገራሉ።

"ዋናው ግብ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ህጻናትን ከአካባቢያቸው ሳይርቁ ድጋፍ መስጠት ነው። በዚህም ከ2 ሺህ በላይ ህጻናትን መታደግ መቻል ትልቅ ለውጥ ነው" ይላሉ።

ታሪክ እየቀየሩ ያሉት ሴቶች

ጉዳት የደረሰባቸው ህጻናት ጉዳይ በሕግ እንዲታይ ድርጅቱ ድጋፍ ያደርጋል። በዚህ ረገድ ሰላም ዕድለኛ አልሆነችም። ደላላው የት እንዳለ ባለማወቋ ግለሰቡን ሕግ ፊት ማቅረብ አልተቻለም።

በድርጅቱ በኩል ከቤተሰቦቿ ጋር እንድትቀላቀል ጥረት እየተደረገ ነው፤ ውጤቱንም በጉጉት እየጠበቀች ትገኛለች።

"የምመለስበትን ቀን እየጠበቅኩ ነው፤ እናቴ በጣም ትናፍቀኛለች" የምትለው ሰላም ወደ አካባቢዋ ስትመለስ ትምህርቷን መማር እንደምትፈልግ ያላትን ተስፋ ትገልጻለች።