አውታር - አዲስ የሙዚቃ መሸጫ አማራጭ

የአውታር መልቲ ሚዲያ አርማ Image copyright Awetar MultiMedia

የኢትዮጵያን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከሚፈታተኑ በርካታ ነገሮች መካከል አንዱ ቴክኖሎጂ ነው። በመጀመሪያ በሸክላ ይደመጥ የነበረው ሙዚቃ ወደካሴት ከዚያም ወደሲዲ ፈቅ እያለም በሶፍት ኮፒ መሸጥ ጀመረ።

ሁላችንም የስልካችን ምርኮኛ፤ የስልካችን እስረኛ እየሆንን መምጣታችን ለኢትዮጵያ ሙዚቀኞች የሲዲ ገበያ ቸር ወሬ አልነበረም።

ለበርካታ ጊዜያት ጎምቱ ድምጻውያንም ሆኑ አዳዲስ ሙዚቀኞች ሥራዎችን ጨርሰው ለገበያ ለማውጣት እግር ተወርች ከሚያስራቸው ጉዳይ አንዱ የላባቸውን ዋጋ በአግባቡ የሚያገኙበት መሸጫ አለመኖሩ ነበር።

ድምፅ ፈታዮቹ መረዋዎች

ሙዚቃ አቀናባሪው ኤሊያስ መልካ "እኔ ጋር እንኳ የበርካታ ድምፃውያን ሥራ አልቆ ቁጭ ብሏል" በማለት እማኝነቱን ይሰጣል።

ለኤሊያስ የሲዲ ቴክኖሎጂ እየቀረ መምጣቱም ሌላው የሙዚቃ ገበያውን አደጋ ላይ የጣለ ጉዳይ ነው።

ሲዲ የሚወስዱ ቴፕ ሪከርደሮች እየቀሩ፣ ጂፓስ በየቤታችን እየገባ፣ መኪኖች ሳይቀር ፍላሽ ብቻ እንዲያጫውቱ እየሆኑ መምጣታቸውን ያስተዋለው ኤልያስ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር የሚሄድ መፍትሔ ከመሞከር አልቦዘነም።

የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዳዊት ይፍሩም የኤልያስን ስጋት ይጋራሉ። "በኛ አገር ሙዚቀኞች ሥራቸውን ይሠሩና መርካቶ ላሉ አሳታሚዎች በመስጠት ይሸጣሉ" በማለት የሙዚቃ ገበያውን አሠራር ያስረዳሉ።

"በ 'ፍቅር እስከ መቃብር' ላይ ህይወት የዘራው አባቴ ነው"

አሳታሚው ካሳተመ በኋላ ደግሞ በመላው አገሪቱ በማሰራጨት ሽያጭ ይካሄድ ነበር፤ በማለት የድሮውን የሙዚቃ የገበያ ሥርዓት ያብራራሉ።

በዚህ መካከል ድምፃውያን አንዴ በተነጋገሩበት ዋጋ ይሸጣሉ፤ ከዚያ በኋላ ምን ያህል ያወጣል? ምን ያህል ያተርፋል? የሚለው ላይ እጃቸውን አያስገቡም በማለትም ያክላሉ።

ዓመት ዓመትን ሲወልድ አሠራሩ እየተቀየረ መጥትቷል። ካሴት የሚያሳትም የለም። ሲዲ የሚያሳትመውም ቁጥሩ ቀንሷል። ላሳትም ብሎ ደፍሮ ሥራውን ለገበያ የሚያቀርብ ባለሙያም ፈተናው ብዙ ነው። በቀላሉ ኮፒ ተደርገው የሚሸጡበት በመሆኑ ከአጠቃላይ ከሽያጩ እጠቀማለሁ ማለት አይችልም ይላሉ።

ባህልን በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ የቀመመው ሮፍናን

"ለዚህም ነው በዚህ ዘመን አሳታሚ የሌለው" ይላሉ አቶ ዳዊት።

አሁን ያለው ድምፃዊ ተበድሮም ይሁን ተለቅቶ አንድ ነጠላ ዜማ ካወጣ በኋላ ድምፃዊው ስራው ከተወደደለት ሰርግ ወይንም ግብዣዎች ላይ ሲቀናም ከሀገር ውጪ እየተጋበዘ ይሰራል በማለት ያለውን ውጣ ውረድ ይገልጣሉ።

ይህም ከሲዲ ሽያጭ አተርፋለሁ የሚል ድምፃዊ እንዳይኖር አድርጓል።

Image copyright Jack Vartoogian/Getty Images

ታዲያ ምን ተሻለ?

የሙዚቃ አቀናባሪው ኤልያስም ሆነ የሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዝዳንቱ ዳዊት ስጋት ይቀረፍ ዘንድ መፍትሔ ይሆናል በማለት፤ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሰብሰብ ብለው ሀሳብ ያወጡ ያወርዱ ከጀመሩ አምስት ዓመት አልፏቸዋል።

በኋላም የኢትዮጵያ የሙዚቃ ባለሙያዎች ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር ያዘጋጁት አውታር የሙዚቃ መሸጫ መተግበሪያና ድረ ገጽ ሥራወን በማጠናቀቅ ዓርብ ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ .ም. በይፋ ሥራ ይጀምራል ተባለ።

"አዲሱ አመተግበሪያ ኢትዮጵያውያን የፈለጉትን ሙዚቃ በፈለጉት ጊዜና ቦታ በእጅ ስልኮቻቸው በኢንተርኔት አማካይነት ለመግዛት ያስችላቸዋል" ይላል ኤልያስ።

አውታር መልቲ ሚዲያ የተመሰረተው በኤልያስ መልካ፣ ጆኒ ራጋ፣ ዳዊት ንጉሡና ኃይሌ ሩትስ ሲሆን፤ በመተግበሪያው ከሚሸጡት ሙዚቃዎች ኢትዮ-ቴሌኮም ድርሻ ይኖረዋል።

''አዝማሪዎቻችን የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ናቸው"

ድምፃዊት ፀደኒያ ገብረማርቆስ ይህን የሙዚቃ መሸጫ አማራጭ ከሚደግፉት አንዷ ነች። "ስልጡን አማራጭ" ስትልም ትጠራዋለች። የኢንተርኔት አቅምና ተደራሽነት ከፈቀደ በርካታ ሙዚቃ መሸጥ ይቻላል በማለት ተስፋዋን ትገልጻለች።

ሰዎች ዘመናዊ ስልክ መያዝ በመጀመራቸው፣ ኢንተርኔት አጠቃቀማችንም ከፍ እያለ በመምጣቱ እንደዚህ አይነት የመሸጫ መንገድ ማስለመዱ መልካም መሆኑን ትገልፃለች።

ድምጻዊት ፀደኒያ እስካሁን ስራዎቿን ወደ አውታር ወስዳ በእናንተ በኩል ይሸጥልኝ ብላ ባትሰጥም፤ አገልግሎቱ ከተጀመረ ግን ይህንን ለማድረግ አይኗን እንደማታሽ ትናገራለች።

ታዋቂዎቹ ኤርትራዊያን በሙዚቃቸው ምክንያት ይቅርታ ጠየቁ

ብዙ ሰዎች በአንድ ሲዲ ውስጥ ያሉ ሥራዎችን በአጠቃላይ ስለማይወዱት "እያለፉ ነው የሚያደምጡት" የምትለው ፀደኒያ፤ ግዴታ አስራ ምናምን ዘፈኖች መግዛት አይጠበቅባቸውም ትላለች።

ይህ አዲስ መተግበሪያ አንድ ሰው የሚፈልጋቸውንና የሚመርጣቸውን ዘፈኖች ብቻ መርጦ የመግዛት እድል ስለሚሰጥ ተመራጭ መገበያያ መንገድ ነው ስትል ሀሳቧን ታጠናክራለች።

Image copyright Awetar Multi Media

አውታር፡- ችግር የወለደው መፍትሔ

ኤልያስና ጓደኞቹ ኢትዮ-ቴሌኮም ለተጠቃሚዎቹ አጫጭር መልእክቶችን በጅምላ ሲልክ ሲመለከቱ፤ እኛስ በዚህ መንገድ ለምን ሙዚቃ አንሸጥም የሚል ሀሳብ እንዳፈለቁ ያስታውሳል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ዘንድ ቀርበው ሀሳባቸውን ሲያስረዱ ግን በአጫጭር መልእክት ጽሑፍ እንጂ ድምፅ መላክ እንደማይቻል ተነገራቸው።

እነኤልያስ በሙዚቃ ሥራ ውስጥ በየእለቱ ቴክኖሎጂ ሲቀየር ተመልክተዋል። "ከካሴት ወደ ሲዲ በሄድንበት ፍጥነት የሲዲ ቴክኖሎጂም ሲቀየር ተመልክተናል" ይላል። ስለዚህ በድረገጽ የሚሸጡበት መንገድ ያስቡ ጀመር።

ተፈራ ነጋሽ፡ "በነገራችን ላይ ሙዚቃ አልተውኩም"

ይህ ሀሳብ ግን ከዝሆን የገዘፈ ችግር ከፊቱ አለ። ሰዎች ሙዚቃውን መግዛት ቢፈልጉ በምን ሥርዓት መክፈል እንደሚችሉ አይታወቅም። ምክንያቱ ደግሞ የባንክ የክፍያ ስርዓትን በኦን ላየን ግብይት ማድረግ ስለማያስችል ነው።

ስለዚህ ያለው አማራጭ ቴሌ ብቻ ነው። ቴሌ ከእሱ ፈቃድ ወስደው አጫጭር መልዕክቶችን ለሚልኩ ድርጅቶች ከተጠቃሚዎች ገንዘብ ቆርጦ የድርሻውን በመውሰድ ለድርጅቱ ደግሞ የድርሻውን ይሰጣል።

"ቴክኖሎጂው ለጽሑፍ ብቻ ስለሆነ ሙዚቃ መላክ አያስችልም" ቢባሉም እነድምፃዊ ኃይሌ ሩትስ ተስፋ ሳይቆርጡ ተመላልሰው ከቴሌ ጋር ተነጋገሩ። ለዚህ ምክንያት የሆናቸው ቴሌ ፓኬጅ ዳታ መሸጥ መጀመሩ ነው።

በፓኬጅ ዳታው ከፍ ያለ ሜጋ ባይት ኢንተርኔት ስለሚሸጥ፤ ምናልባት አሁን ሳይቻል አይቀርም የሚል ተስፋ አደረባቸው። የኢትዮ-ቴሌኮም ኃላፊ የነበሩት አቶ አንዱዓለም አድማሴም ይቻላል አሏቸው።

Image copyright CRISTINA ALDEHUELA

መነሻ ሀሳብ ወይስ የሙዚቃ ቅጂ መብት ጥሰት?

ኤልያስ አሁንም ግን ቴሌ ራሱ ከጽሑፍ ውጪ ሌላ መልእክት ለመላክ ዝግጁ ስላልነበር ወደሥራ ለመግባት ፈተና እንደሆነባቸው ይናገራል።

የሙዚቃ ባለሙያዎቹ ኤልያስ፣ ጆኒ ራጋ፣ ኃይሌ ሩትስና ዳዊት ንጉሡ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በጋራ የሚሠሩት ይህ የሙዚቃ መሸጫ መተግበሪያ ከ1960ዎቹ ጀምሮ የተሠሩ፤ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን ያቀርባል ተብሏል።

እነዚህ ሙዚቀኞች ሥራውን ለመሥራት ከቴሌ ጋር Value Added Service (VAS) ለመሥራት ፈቃድ ማውጣት ያስፈልግ ስለነበር የንግድ ፈቃድ ማውጣት አስፈልጓቸዋል። በዚህ ምክንያት አውታር መልቲ ሚዲያን አቋቋሙ። ድርጀቱ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በጋራ መሥራት የቫስ (VAS) ፈቃድ ማውጣታቸውንም ገልጠዋል።

ሦስቱ የሙዚቃ ባለሙያዎች በመጪው ዓርብ ማታ በሸራተን ይፋ የሚደረገውን የሙዚቃ ሽያጭ ሥርዓት፤ የአገሪቱ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ የገጠሙትን ፈተናዎች ለመወጣት ኹነኛ መንገድ ነው የሚል ዕምነት አላቸው።

በዚሁ የሽያጭ ሥርዓት ድምፃዊ፣ የግጥም ጸሐፊ፣ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ የዜማ ደራሲና ፕሮዲውሰር ትርፍ እንዲከፋፈሉ ይደረጋል። ሙዚቃው በአውታር መተግበሪያ ተጭኖ እንዲሸጥ አምስቱ ባለሙያዎች ተስማምተው መፈረም ይኖርባቸዋል ይላል ኤልያስ።

አሁን ሰዎች በአንድ ጊዜ አገልግሎቱን ፈልገው ቢመጡ ሊከሰቱ የሚችሉ መዝረክረኮችን ለማስቀረት እየሞከርን ነው የሚለው ኤልያስ፤ ከአርብ ማታ ጀምሮ መተግበሪያው በጎግል ፕሌይ ስቶር ይገኛል ይላል።

በዝማሬ የተካኑት ዓሳ ነባሪዎች

ይህንን መተግበሪያ በሞባይሉ ላይ የጫነና በአገር ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሙዚቃውን መጫን የሚችል ሲሆን፤ ካልሆነ ደግሞ ኢትዮ-ቴሌኮም ሊንክ የሚልክ ይሆናል በማለት አፕሊኬሽኑን ለማስተዋወቅ የሚጠቀሙበትን መንገድ ያብራራል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ለተጠቃሚዎቹ በአጠቃላይ የሚልከው ጥቅል መልእክት ላይ ማስፈንጠሪያውን አብሮ እንደሚልክ የሚናገረው ኤልያስ፤ ስማርት ስልክ ያላቸው ማስፈንጠሪያውን ሲጫኑ ወዲያውኑ በስልካቸው ላይ መተግበሪያው የሚጫን ሲሆን፤ ስማርት ስልክ የሌላቸው ግን በቁጥር እያስመረጠ እንዲጠቀሙ የሚያስችለው ዩ ኤስ ኤስ ዲ የሚባለው ቴክኖሎጂ ለመጨረስ በሥራ ላይ መሆናቸውን ይገልጣል።

Image copyright Getty Images

የአውታር ትሩፋቶች ምን ምን ናቸው?

መተግበሪያው ምስሎች፣ ስለዘፋኙና ሌሎች ሙዚቀኞች መረጃ እንዲሁም የዘፈኑን ግጥም የያዘ መሆኑን የሚናገረው ኤልያስ "ሙዚቃውም ጥራት አለው" ይላል።

ይህ የሙዚቃ መሸጫ መተግበሪያ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው ያሉት አቶ ዳዊት፤ አውታር የተባለው መተግበሪያ ሰዎች የገዙትን ሙዚቃ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለሌላ ሰው ከማስተላለፍ የሚከለክል ሥርዓት አለው ሲሉ ለሙዚቀኞች ያለውን ጥቅም ያብራራሉ።

ሙዚቃ አቀናባሪው ኤልያስ በበኩሉ፤ መተግበሪያው ላይ የተጫነ አንድ ሙዚቃ በአራት ብር ከአምሳ ሳንቲም እንደሚሸጥ ይናገራል። ይህ በአንጋፋዎቹ የሙዚቃ ባለሙያዎች እና በአዳዲስ ድምፃውያን የተሠሩትን ይጨምራል።

መተግበሪያው የኢትዮጵያን ሙዚቃ በውጭ አገራት ስንት ለመሸጥ እንደታቀደ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም ብሏል ኤልያስ። ይህ ጉዳይ የድምፃዊት ፀደኒያም ስጋት ሲሆን፤ እንደሀገር በዚህ ዘርፍ ወደኋላ ቀርተናል በማለት ቁጭቷን ትገልጣለች።

መተግበሪያው በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አገልግሎት ይሰጣል የሚለው ኤልያስ በኦሮምኛ፣ በትግሪኛ፣ በአማርኛና በእንግሊዘኛ እንዲሠራ ሆኖ የተዘጋጀ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ እምነት ተከታዮችም፤ የሙስሊም፣ የኦርቶዶክስ፣ የፕሮቴስታንት፤ የሚፈልጉትን መንፈሳዊ መዝሙር ወይንም መንዙማ ማግኘት እንዲችሉ ተደርጎ መደራጀቱን ያስረዳል።

ፊቼ ጨምበላላ፦ የሲዳማ ሕዝብ አዲስ ዓመት

መተግበሪያው በዓመተ ምሕረት፣ በዘውግ፣ በቋንቋ፣ በስልት ተከፋፍሎ የተቀመጠ መሆኑን አብራርቷል።

"የኢትዮጵያ ሙዚቃ አብዛኛው ገበያ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው" የሚለው ኤልያስ፤ ይህ መተግበሪያ ለጊዜው የሚሠራው ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን ያስረዳል። ነገር ግን ከአገር ውጪ ያሉ አድማጮች ገዝተው መጠቀም እንዲችሉ ከባንክ ጋር እየተነጋገሩ ነው።

በአንድ ሙዚቃ ላይ አምስት ሥራዎች አሉ የሚለው ኤልያስ፤ እነዚህም ማቀናበር፣ መዝፈን፣ ግጥም መፃፍ፣ ዜማ መድረስ እንዲሁም ፕሮዲውስ ማድረግ መሆናቸውን ያስረዳል። በአንድ የሙዚቃ ሥራ ውስጥ እነዚህን ሥራዎች አንድ ወይም ሁለት ሰው ደርቦ የሚሠራቸው ሊሆኑ ቢችሉም፤ ክፍያ ሲቀመጥ ግን ለሥራዎቹ እንደሆነ ያስረዳል።

ስለዚህ ከአንድ የሙዚቃ ሥራ ላይ እነዚህ አምስት ሥራዎች እያንዳንዳቸው 20 በመቶ ክፍያ ያገኛሉ።

ይህ የሙዚቃ መሸጫ መተግበሪያ አርብ ማታ ሥራ ሲጀምር፤ 24 ሰዓት፣ በየትኛውም የአገሪቱ ስፍራ፤ ሰባቱንም ቀን መሸጥ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው። በተለይ አዲስ ድምፃውያን ወረፋ ሳይጠብቁ በፈለጉበት ወቅት የሙዚቃ ገበያውንና አድማጮቻቸውን ማግኘት ይችላሉ።

Image copyright Getty Images

ዝግጅት

በሸክላ የተቀረፁ የድሮ ዘፈኖች፣ በካሴት የተቀዱ የስድሳዎቹና የሰባዎቹ ሥራዎች፣ በሲዲ የነበሩ ሁሉ ተሰብስበው ወደኮምፒውተር ተገልብጠዋል የሚለው ኤሊያስ፤ አንዳንዶቹ ባለቤቶቻቸው በሕይወት ስለሌሉ ከሕጋዊ ወራሾቻቸው ጋር በመነጋገርና በመፈራረም እንዲጫኑ ይደረጋል ብሏል።

ሁለት ዘፈኖች ብቻ ከሚይዘው ሸክላና ከሰዎች ላይ ሙዚቃ በማሰባሰብና በመግዛት ወደኮምፒውተር መገልበጥ ዋናው ሥራ እንደነበር የሚያስታውሰው ኤልያስ፤ "ሁሉም ሙዚቃ እኛ ጋር ባይኖርም በተቻለ መጠን ሁሉንም ለማሟላት እየሠራን ነው" ብሏል።

አንድ ድምፃዊ ሥራው አውታር ላይ እንዲጫን፤ ፎርማቱን ወደ ኤም ፒ 3 በመቀየር 224 ኬቢ ወይንም 160 ኬቢ በማድረግ የዘፈኑን ግጥምና ፎቶውን በሶፍት ኮፒ ማስቀመጥ ብቻ በቂ ነው ይላል።

ከዚያ የገዙትን ሰዎችና ምን ያህል እንደተሸጠ ለማወቅ የሚረዳውን ኮድ ከማግኘቱ በፊት መፈራረም ይጠበቅበታል።

አንድ ነጠላ ዘፈን አራት ብር ከሀምሳ፤ አምስት ዓመት ያልሞላው ሙሉ አልበም አስራ አምስት ብር ይሸጣል። በአንድ ሲዲ ላይ የሚኖረው ዘፈን ምንም ያህል ቁጥር ቢኖረው ሙሉ አልበም 15 ብር እንደሚሸጥ ያሰምርበታል።

በታሪካዊው ቤተ መንግሥት ውስጥ ምን አለ?

አቀናባሪው ተከፍሎት ስለሆነ የሚያቀናብረው እስከአምስት ዓመት ድረስ ሌላ ገንዘብ አይጠይቅም የሚለው ኤልያስ፤ ይህ የድምፃዊው መብት በቅጂና ተዛማጅ መብቶች በኩልም የተጠበቀ ነው በማለት "በአምስት ዓመት ውስጥ ወጪውን ሸፍኖ ትርፍ ያገኛል ተብሎ ይታሰባል" በማለት ያስረዳል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አብዛኛው መብት የዘፋኙ ነው በማለት ያክላል።

ከአምስት ዓመት በኋላ ግን ድጋሚ መክፈል ስላለበት ሙዚቃው ተነጥሎ ነው የሚሸጠው የሚለው ኤልያስ፤ ይህ የሆነው በአንድ ካሴት ውስጥ ያሉ ዘፈኖችን የተለያዩ ሰዎች ስለሚያቀናብሯቸው፣ ግጥምና ዜማቸውንም ስለሚደርሱ ለመክፈል በጅምላ መሸጥ ስለማያዋጣ ነው በማለት አሠራራቸውን ያብራራል።

ተያያዥ ርዕሶች