የቦይንግ ኃላፊ የሟቾችን ቤተሰቦች በይፋ ይቅርታ ጠየቁ

የቦይንግ ኃላፊ ዴኒስ ሙይንበርግ

የቦይንግ ኃላፊ ዴኒስ ሙይንበርግ ከሲቢኤስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአውሮፕላን አደጋው ሕይወታቸው ያለፈ ግለሰቦችን ቤተሰቦች ይቅርታ ጠይቀዋል። ኃላፊው ከዚህ ቀደም በቪድዮ በሰጡት መግለጫ ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፤ ይህ ሁለተኛቸው ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን ባለፈው መጋቢት ወር ከተከሰከሰ ከሳምንታት በኋላ ኃላፊው በቦይንግ ስም ይቅርታ ቢጠይቁም፤ የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ ካፒቴን ያሬድ ጌታቸው አባት ዶ/ር ጌታቸው ተሰማ የቦይንግ ይቅርታ "ዘግይቷል" ብለው ነበረ።

ኃላፊው ከሲቢኤስ ጋር ባደረጉት ቆይታ "የደረሱት አደጋዎች እጅግ አሳዝነውናል" ብለዋል።

ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ በደረሰበት አደጋ 157 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል። ከአደጋው ከአምስት ወር በፊት የላየን ኤር አውሮፕላን ተከስክሶ 189 ሰዎች ሞተዋል።

የቦይንግ ኃላፊ ዴኒስ ሙይንበርግ "ስለተፈጠረው ነገር ይቅርታ እንጠይቃለን። በሁለቱም አደጋዎች የሰዎች ሕይወት በመጥፋቱም ይቅርታ እንጠይቀለን" ብለዋል። ኃላፊው በአደጋው ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ግለሰቦችን ይቅርታ ብለው፤ "የተፈጠረው ነገር እንደድርጅቱ መሪነቴ በቀጥታ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል" ሲሉም ተደምጠዋል።

"ቦይንግ ውስጥ ባሳለፍኩት 34 ዓመታት ከተፈጠሩ ነገሮች እጅግ ከባዱ ይህ ነው። የተፈጠረውን መቀየር ባንችልም በቀጣይ ለደህንነት ጉዳዮች የላቀ ትኩረት እንሰጣለን" ብለዋል።

ኃላፊው ቦይንግ "ለወደፊቱም ደህንቱ አስተማማኝ" እንደሚሆንም ለሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል። የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች በኢትዮጵያና በኢንዶኔዥያ ከተከሰከሱ በኋላ ኃላፊው ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ የሲቢኤስ ኒውስ የመጀመሪያቸው ነው።

የቦይንግ ኃላፊ በሁለቱ የአውሮፕላን አደጋዎች ሕይወታቸውን ካጡ ግለሰቦች ቤተሰቦችን በተጨማሪ በአውሮፕላን የሚጓጓዙ ሰዎችን በአጠቃላይም ይቅርታ ጠይቀዋል።

"እምነት ያጡ ተጓጓዦችን ይቅርታ እንጠይቃለን። ደንበኞቻችን ላይ ተጽዕኖ ማሳደራችን ይጸጽተናል" ብለዋል። ቦይንግ ኃላፊነቱን ከመውሰድ ባሻገር አስፈላጊ ማሻሻያ እንደሚያደርግም አክለዋል።