ቤተሰብና ጓደኛ የሚያከራየው ድርጅት

ዩሺ ኢሺ
አጭር የምስል መግለጫ ዩሺ ኢሺ

ጃፓናዊው ዩሺ ኢሺ 38 ዓመቱ ነው። በልጅ ብዛት ከእድሜ እኩዮቹ መካከል የሚወዳደረው የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም።

25 ቤተሰቦችና 35 ልጆች አሉት። እንዴት? ማለት ጥሩ. . .

አራት ህጻናትን በአንዴ ያገኘው ቤተሰብ ተጨንቋል

ዩሺ፤ ከአስር ዓመት በፊት የመሰረተው 'ፋሚሊ ሮማንስ' የተባለ ድርጅት ያልተለመደ አገልግሎት ይሰጣል- ቤተሰብና ጓደኛ የማከራየት። ድርጅቱ 2,200 ተቀጣሪዎች አሉት። ሥራቸው ደግሞ እንደ አባት፣ እናት፣ አጎት፣ አክስት ወይም አያት ሆኖ መተወን ነው።

እነዚህ ሠራተኞችና ዩሺ 'ቤተሰቦች' እና 'ልጆች' ያፈሩትም በቅጥር ነው።

የኪራይ ቤተሰብና ጓደኛ

ከዩሺ ጓደኞች አንዷ ልጇን መዋለ ህፃናት ለማስገባት ስትሞክር፤ ትምህርት ቤቱ ለልጇና ለባለቤቷ ቃለ መጠይቅ ማድረግ እንደሚፈልግ ተነገራት። የትዳር ጓደኛ ስላልነበራት ዩሺን 'ባሌ ነው' ብላ ለቃለ መጠይቅ ወሰደችው።

ዩሺና ልጁ አንዳችም ትስስር ስለሌላቸው እንደአባትና ልጅ መተወን አልቻሉም። ዩሺ፤ ብዙ ሰዎች ቤተሰብ ወይም ጓደኛ በማጣት እንደሚቸገሩ የተገነዘበበት ወቅት ነበር። 'ፋሚሊ ሮማንስ' የተባለውን የቤተሰብና ጓደኛ አከራይ ድርጅት የወጠነውም በዚህ አጋጣሚ ነበር።

"የውሸት ቢሆንም ለጥቂት ሰዓታት ጓደኛችሁ ወይም ቤተሰባችሁ መሆን እችላለሁ" ይላል።

ጓደኛ ለማፍራት ማወቅ ያለብን ጠቃሚ ነጥቦች

አጭር የምስል መግለጫ ቤተሰብ ወይም ጓደኛ ለአራት ሰዓት ለመከራየት ወደ 5ሺህ ብር ይከፈላል

ዩሺ በየአይነቱ ደንበኞች አሉት። ብዙዎች የኪራይ እናትና አባት ወይም ጓደኛ ይሻሉ።

የኪራይ ቤተሰብ ሲቀጠር፤ የግለሰቡ ገጽታና ተክለ ሰውነት ከግምት ውስጥ ይገባል። 'ልጄ ነው' ከሚሉት ሰው ጋር መመሳሰል አለባቸውና።

ሶሻል ሚድያ በተጠቃሚዎች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ያውቃሉ?

ጓደኛ ከሌለዎት ከማን ጋር ላውራ? ከማንስ ጋር ልንሸራሸር? ብለው መጨነቅ የለብዎትም። በዩሺ ድርጅት የሚከራዩት 'ጓደኛ' አብሮዎት ይበላል፣ ይጠጣል። ማውራት፣ ሸመታ መውጣትና መንሸራሸርም ይቻላል።

ልጅ ወይም የልጅ ልጅ የሚከራዩ የእድሜ ባለጸጋዎችም አሉ። ከልጆቻቸው ጋር ያሳለፉትን ውብ ጊዜ ለማስታወስ አልያም የሌላቸውን 'ልጅ' ለመተካት።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ለልጆቻቸው አባት የሚከራዮ እናቶችም አሉ

"የ 'አባት' ተከራዮች ቁጥር ጨምሯል"

ዩሺ እንደሚለው፤ በእጅጉ ከሚፈለጉ ሚናዎች አንዱ 'አባትነት' ነው። ጃፓን ውስጥ በየዓመቱ 200 ሺህ ሰዎች ስለሚፋቱ ብዙዎች ልጆቻቸውን ለብቻቸው ለማሳደግ ይገደዳሉ።

ማኅበረሰቡ የተፋቱ ሰዎችን ያጥላላል። ልጅ ለብቻ ማሳደግም እምብዛም አይደገፍም። ታዲያ ዩሺ፤ በማኅበረሰቡ ለተገለሉ ሰዎች "ከለላ እንሰጣለን" ይላል።

ከተለያየ አባት የተወለዱት መንትዮች

ደንበኞቹ የተለያየ አይነት ባህሪ ያለው 'አባት' ይፈልጋሉ። ቁጡ፣ ለስላሳ. . . እንደየምርጫቸው 'አባት' ይሰናዳላቸዋል።

አንዳንዴ 'አባት' የሚቀጠርላቸው ህፃናት ነገሩ ትወና መሆኑን ለመገንዘብ እድሜያቸው ስለማይፈቅድ፤ ግለሰቡ የእውነትም ወላጅ አባታቸው እንደሆነ ያምናሉ። ተቀጣሪው ሥራውን ጨርሶ ሲሰናበታቸውም ለመለየት ይከብዳቸዋል።

የ 'ፋሚሊ ሮማንስ' ተቀጣሪዎች 'ቤተሰብ' መሆን የሚችሉት ለአምስት ቤተሰብ ብቻ ነው። ዩሺ እስካሁን ለ25 ቤተሰቦች 'ቤተሰብ' ሆኖ ተውኗል፤ 35 ልጆች 'አባታችን ነው' ብለው ያምናሉ፤ 69 ሰዎች ደግሞ 'ዩሺ የቅርብ ጓደኛዬ' ነው ይላሉ።

"አንዳንዴ የደንበኞቼን ቅጽል ስም ስለምረሳው ማስታወሻ እይዛለሁ" ይላል።

እናት አልባዎቹ መንደሮች

'ልጆቹን' ትምህርት ቤት ያደርሳል፤ የቤተሰብ ውይይት ይካፈላል. . . ሌሎችም የሚጠበቁበት ተግባራትን ያከናውናል።

ሥራው እንደሌሎች ሙያዎች ባሻው ጊዜ እረፍት የሚወጣበት አይደለም። በቀን ከሦስት ሰዓት በላይ ማረፍ አይችልም።

"ከእኩለ ለሊት አንስቶ ለሦስት ሰዓት አርፋለሁ። ፊልም አያለሁ፤ እስላለሁ።"

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ደንበኞቹ በገሀዱ ዓለምና በትወና መካከል ያለውን ልዩነት እንዳይዘነጉ ያስጠነቅቃል

የእውነትና ውሸት መስመር የቱ ጋር ነው?

ዩሺ አላገባም፤ አልወለደም፤ ትዳር መመስረትና ልጅ ማፍራትም አይፈልግም። አዲስ ቤተሰብ ቢመሰርት አሁን ካሉት 25 የውሸት ቤተሰቦች ጋር የሚጋጭ ይመስለዋል።

"የእውነት ባገባ ደንበኞቼ ምን ይሰማቸዋል? ልጆች ብወልድም ከሀሰተኛ ልጆቼ ጋር የሚምታቱብኝ ይመስለኛል።"

ዩሺ የሚነግደው ውሸት ነው። የእንጀራ ገመዱ የተዘረጋውም ማስመሰል ላይ ነው። ታዲያ ይህ የውሸት ዓለም ከገሀዱ ዓለም ጋር እንዳይጋጭ ከደንበኞቹ ጋር የሚስማሙባቸው መርሆች አውጥቷል።

የመይሳው ካሳ የልጅ ልጆች

የድርጅቱ ሠራተኞች የሚመሩባቸው ሕግጋት አሉ። ለምሳሌ ከደንበኞች ጋር መሳሳምና ወሲብ መፈጸም ክልክል ነው። እጅ ለእጅ መያያዝ ግን ይፈቀዳል።

ቤተሰብ ወይም ጓደኛ ለአራት ሰዓት ለመከራየት 180 ዶላር (ወደ 5ሺህ ብር ደገማ) ይከፈላል። ተከራዩ የሠራተኛውን የምግብና መጓጓዣ ወጪ መሸፈንም ይጠበቅበታል።

ድርጅቱ "ከእውነት ደስታ ይበልጣል" በሚል መሪ ቃል ይተዳደራል። ሆኖም 'እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል' እንዲሉ እውነት አንድ ቀን መገለጧ አይቀሬ ነው።

ዩሺ እንደሚለው፤ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን እስከወዲያኛው መዋሸት አይገባቸውም።

የሰዎች ግንኙነት በላላበትና በጋራ መኖር ፈታኝ በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ እንደ 'ፋሚሊ ሮማንስ' ያለ ድርጅት እንደሚያስፈልግ ያምናል። በተለይም ጃፓናዊያን፤ ሰዎች ስለነሱ ያላቸው አስተያየት ስለሚያስጨንቃቸው በድርጅቱ ከመገልገል ወደኋላ አይሉም።

"የምንፈልገውን መሆን ይከብዳል። ራሳችንን ባሻን መንገድ መግለጽም ቀላል አይደለም። ማኅበሰረሱ የኛን አገልግሎት የማይሻበት ዓለም ቢፈጠር መልካም ነበር። ሆኖም እውነታው ከዚህ የራቀ ነው።"