የሰሜን ኮርያው ባለሥልጣን እውን ተገድለዋል?

ኪም ኃይክ ኮል፤ በኪም ጆንግ ኡን እና ዶናልድ ትራምፕ ውይይት ወቅት Image copyright EPA/Yonhap
አጭር የምስል መግለጫ ኪም ኃይክ ኮል፤ በኪም ጆንግ ኡን እና ዶናልድ ትራምፕ ውይይት ወቅት

ሰሜን ኮርያ ከኒውክሌር ዘርፍ ተወካዮቿ አንዱን ገድላለች የሚል ዜና መናፈስ ቢጀምርም እውነተኛ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም። በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ዘገባ መሰረት፤ ሰሜን ኮርያ ከአሜሪካ ጋር ያደረገችው ውይይት ፍሬያማ ስላልሆነ፤ የውይይቱ አካል የነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች እርምጃ እየተወሰደባቸው ነው።

መሰል ዜናዎች ከወደሰሜን ኮርያ ሲሰሙ ለማጣራት ስለሚከብድ፤ በአገሪቱ ውስጥ ስለሚፈጸሙ ተግባሮች በድፍረት መናገር ይከብዳል። በተለይም የመንግሥት ባለሥልጣኖች 'ተገድለዋል' ብሎ መዘገብ አስቸጋሪ ነው።

ኪም ጆንግ ኡን የጦርነት ልመና ጥሪ በማድረግ ተወቀሱ

ከዚህ ቀደም የሰሜን ኮርያ ሚድያዎች ሳይቀር 'ተገድለዋል' ያሏቸው የመንግሥት ባለሥልጣኖች፤ ዘገባው ወጥቶ ብዙም ሳይቆይ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ታይተዋል።

ሰሜን ኮርያ በአሜሪካ ጉዳዮች ወክላው የነበረው ኪም ኃይክ ኮል መገደሉን ሱዑል ለሚገኝ ጋዜጣ የተናገረው አንድ ምንጭ ነው። ኪም ኃይክ ኮል፤ ኪም ጆንግ ኡን እና ዶናልድ ትራምፕ ባደረጉት ውይይት ከፍተኛ ሥልጣን ከነበራቸው አንዱ ነበር። ፒዮንግያንግ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ መገደሉም ተዘግቧል።

የዜናውም ምንጭ እንደሚለው፤ ኪም ኃይክ ኮል ከሌሎች አራት የውጪ ጉዳይ ባለሥልጣኖች ጋር ተገድሏል። ባለሥልጣኖቹ ለአሜሪካ በመሰለል ተከሰው ነበር። በተጨማሪም የአሜሪካና የሰሜን ኮርያ ውይይት በተካሄደበት ወቅት የአሜሪካን ፍላጎት በግልጽ የሚያሳይ ሪፖርት አላቀረቡም ተብሏል።

ሰሜን ኮርያ የአሜሪካውያንን አጽም መለሰች

በሌላ በኩል የኪም ጆንግ ኡን 'ቀኝ እጅ' የሚባለው ኪም ኃይክ ኮል፤ በቻይና ድንበር አካባቢ የሚገኝ የመልሶ ስልጠና ማዕከል ውስጥ ገብቷል የሚሉም አሉ። በአሜሪካና ሰሜን ኮርያ ውይይት እጃቸው የነበረ ባለሥልጣኖች ከውይይቱ ወዲህ ከሕዝብ እይታ ተሰውረዋል። ምናልባትም በዚህ ማዕከል የመግባቱ ወሬ እውነት ሊሆንም ይችላል።

ኪም ጆንግ ኡን ከአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጋር ያደረጉት ውይይት አንዳችም ተስፋ አለማሳየቱ እጅግ ስላበሳጫቸው ተጠያቂ የሚያደርጉት ሰው ይፈልጋሉ። ኪም ጆንግ ኡን ከዚህ ቀደም ሰዎች ማስገደላቸውም ይታወቃል። ከዚህ ቀደም የኪም ጆንግ ኡን አጎት ጃንግ ሶንግ ቴክ አገር በመክዳት ተከሰው መገደላቸው ይታወሳል።

'ሲንሙን' የተባለው የመንግሥት ጋዜጣ በዚህ ሳምንት "ፀረ አብዮት ተግባር የፈጸሙ ሰዎች በአብዮቱ ይፈረድባቸዋል" የሚል ረርእሰ አንቀፅ አስነብቧል። የማንም ስም ባይጠቀስም ምን መልዕክት ለማስተላለፍ እንደተፈለገ ግልጽ ነው።

ኪምና ፑቲን ተገናኙ

እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2013 ላይ ኃዮን ሶንግ ውል የተባለች ዘፋኝ መገደሏ በዚሁ ጋዜጣ ቢዘገብም፤ ለክረምት ኦሎምፒክስ ወደሱዑል ካቀናው የልዑካን ቡድን ጋር ታይታለች። አሁን ሰሜን ኮርያ ውስጥ ሀያል ከሚባሉ አንዷም ናት።

2016 ላይ የቀድሞው የወታደር ኃላፊ ሪ ዮንግ ጊል በሙስና ተከሰው መገደላቸው ተዘግቦ ከጥቂት ወራት በኋላ ማዕረግ ተጨምሮላቸው በቴሌቭዥን ታይተዋል። እንደነዚህ አይነት አጋጣሚዎች ሰሜን ኮርያ ውስጥ አንድ ሰው ስለመገደሉ እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንዳይቻል አድርጓል።

የሱዑልና የአሜሪካ የደህንነት ሰዎች ኪም ኃይክ ኮል ተገድሏል ወይስ በሕይወት አለ የሚለውን ለማጣራት እየሞከሩ ነው። ሆኖም ከፒዮንግያንግ መግለጫ እስከሚሰጥ ድረስ አፍ ሞልቶ አለ ወይም ሞቷል ማለት ይከብዳል።