የአክሱም ሙስሊሞች ጥያቄ መቼ ምላሽ ያገኝ ይሆን?

ከአክሱም 15 ኪሎሜትር ርቀት ርቃ በምትገኘው ውቅሮማራይ ሙስሊሞች ጸሎት ሲያደርሱ
አጭር የምስል መግለጫ ከአክሱም 15 ኪሎሜትር ርቀት ርቃ በምትገኘው ውቅሮማራይ ሙስሊሞች ጸሎት ሲያደርሱ

የታሪክ ተመራማሪዎች አክሱም ከ3 ሺህ ዓመት በላይ ያስቆጠረች ጥንታዊ ከተማ ነች ሲሉ፤ የሃይማኖት አባቶች ደግሞ አክሱም ከ6 ሺህ ዓመት በላይ ያስቆጠረች ከተማ ናት ይላሉ።

በዓለማችን ከታዩት ጥንታዊ እና ትልልቅ ስልጣኔዎች መካከል የአክሱም ስልጣኔ አንዱ ነው። የሙሴ ጽላት እንደሚገኝባት የሚታመነው አክሱም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ስፍራ ይሰጣታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በከተማዋ የእስልምና እምነት ተከታዮች ያላቸው የሃይማኖት ነጻነት ጉዳይ እያወዛገበ መልስ ሳያገኝ እስካሁን ድረስ ቆይቷል።

በረመዳን ፆም ምግብ የበሉ 80 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አቶ አዚዝ መሐመድ ሳልህ (ስማቸው የተቀየረ) ተወልደው ያደጉት በአክሱም ከተማ ሲሆን በከተማዋ ቢያንስ ከ26 ዓመታት በላይ ኖረዋል። የአቶ አዚዝ አባት 12 ልጆችን ወልደው ሙሉ ዕድሜያቸውን ያሳለፉትም በአክሱም ከተማ ነው።

''አክሱም ውስጥ ሙስሊም እና ክርስትያን በሃዘን ይሁን በደስታ ተለያይተን አናውቅም'' የሚሉት አቶ አዚዝ፤ የሚቆረቁራቸው ነገር እንዳለ ግን አልሸሸጉም።

''አትስገዱ ብሎ የከለከለን ሰው የለም፤ በየቤታችን መስገድ እንችላለን። አርብ ሲሆን ግን መንገድ ላይ ያውም ፀሐይ ላይ ነው የምንሰግደው። ክርስትያን ወንድሞቻችን 'ትንሽ ቦታ ሰጥተናቸው ለምን ጥላ ስር አይሰግዱም?' ብለው አለማሰባቸው ቅር ያሰኛል'' በማለት ቅሬታቸው ይገልጻሉ።

ሁለት እምነቶችን በአንድ ጣራ ለአስርታት ያሳደሩ ጥንዶች

በአክሱም ዩኒቨርስቲ ግጭት የተጠረጠሩ ተያዙ

በተጨማሪ ''የእስልምና መሪዎቻችን 'ተናግረናል፤ አመለክተናል' ይሉናል እስካሁን ግን ያየነው ነገር ግን የለም'' ይላሉ።

ሌላኛው የአክሱም ከተማ ነዋሪ እና የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑት አቶ አብዱ መሐመድ ዓሊ (ስማቸው የተቀየረ) ለቢቢሲ ሃሳባቸውን አካፍለዋል። ሃሳብ ከመስጠታቸው በፊት ጋዜጠኞች መሆናችንን የሚያሳይ መረጃ ጠይቀውን ካረጋገጡ በኋላ የሚከታተለን ሰው አለመኖሩን ለማጣራት ግራና ቀኝ አማተሩ።

አቶ አብዱ ተወልደው ያደጉት አክሱም ከተማ ማይሹም በሚባል አካባቢ ነው። አቶ አብዱ በአክሱም ከተማ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሆኑ ሰዎች ቁጥር መጨመርን ተከትሎ መስገጃ ቦታ አስፈልጓቸው እንደነበረ ያስታውሳሉ።

አጭር የምስል መግለጫ በኩረ ሊቃውንት ጎደፋ መርሃ፣ በትረ ትጉሃን አምሳሉ ስቡህ እና ሊቀ ካህናት ተክለሃይማኖት

በንጉሡ ዘመን የእስልምና እምነት ተከታይ ባልሆኑ ሰዎች መኖሪያ ቤት ጭምር ከአንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም እስከ ሦስት ብር እየከፈሉ ይሰግዱ እንደነበረ ያስረዳሉ። የእምነቱ ተከታዮች ቁጥር ሲበራከት ግን ከንጉሡ ዘመን ጀምረው መስጊድ መስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው መጠየቅ እንደጀመሩ አቶ አብዱ ያስታውሳሉ።

''አክሱም ገዳም ነው፤ መስጊድ እንድትሰሩ አንፈቅድላችሁም'' የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ያስታውሳሉ።

ቆይቶም አክሱም ውስጥ ማይ ዓኾ በሚባል ስፍራ መስጅድ መስሪያ ቦታ ከተሰጣቸው በኋላ በጭቃና እንጨት መስራት ሲጀምሩ፤ ሰዎች እንዳቃጠሉባቸው ይናገራሉ።

''መስጅድ ብቻ አይደለም፤ መኖሪያ ቤትም አልነበረንም። ደርግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እኩል ናቸው ብሎ መሬት ሰጠን። ነገርግን 'አክሱም ገዳም ስለሆነ መስጅድ ልትሰሩበት አይፈቀድም' ሲሉን እንሰማለን። ማን ነው እንደዚህ ያለው? ከየት የመጣ ህግ ነው?'' ለሚለው ጥያቄ ግን መልስ የለም ይላሉ።

የቻይና ሙስሊሞች ምድራዊ 'ጀሐነም' ሲጋለጥ

የቱሉ ፈራ ደጋግ ኢትዮጵያዊ ልቦች

"እየኖርን ያለነው ከወንድሞቻችን ጋር ነው" የሚሉት አቶ አብዱ ቀደም ሲል 'ሰማይ አምድ የለው፤ እስላም ሃገር የለው' ይባል የነበረው ኋላ ቀር አባባል በደርግ ጊዜ መቅረቱን ነገር ግን ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣም ጥያቄያቸውን ማቅረብ እንደቀጠሉ ይገልጻሉ።

በተጨማሪ ''ወደ አክሱም የሚመጣ ማንኛውም አስተዳዳሪ መስጅድ መስሪያ ቦታ እንዳትሰጥ ተብሎ ውስጥ ለውስጥ ይነገረዋል'' ይላሉ አቶ አብዱ አህመድ።

''የአክሱም ከተማ አስተዳደር 'መስጅድ መፍቀድ የእኛ ስልጣን አይደለም' ሲሉን የ3500 ሰዎች ፊርማ በማሰባሰብ ወደ ትግራይ ክልል አስተዳደር በመሄድ ቅሬታ አቅርበን፤ 'መልስ እንሰጣችኋለን፤ ታገሱ' አሉን። እስካሁን የተሰጠን ምላሽ ግን የለም።'' ሲሉ ያክላሉ።

''አርብ ሲሆን በተከራየነው እና መስጅድ ብለን በምናምነው ቦታ ተሰባስበን እንሰግዳለን። ድምጽ ማጉያ ከተጠቀምን ግን 'ለምን ጮክ አላችሁ? ማርያምን ደፈራችኋት?ድምጽ ቀንሱ፤ ያልነበራችሁን ጠባይ አታምጡ' ይሉናል። ይህ ደግሞ በነጻነት እንዳንሰግድ ጫና ይፈጥርብናል። የምንጸልይበት እና የምንቀበርበት መሬት የፈጣሪ ስጦታ ነው'' ሲሉ ያማርራሉ።

አክሱም ውስጥ የሚገኘው የእስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኪራይ ለ12 ዓመታት እንደከፈለላቸው አቶ አብዱ ገልጸው፤ በ2010 ጥቅምት ወር ግን 'ከአሁን በኋላ አንከፍልላችሁም' ተብለናልም ይላሉ። ''ጽህፈት ቤቱ ገቢ ስለሌለው ክፈሉልን ብለን ቅሬታ አቅርበን እምቢ ብለውናል" በማለት እስካሁን እንዳልተግባቡ ይናገራሉ።

ዴንማርክ ሙሉ የፊት ገጽታን የሚሸፍን 'ሂጃብ' አገደች

ከእምነት ስፍራ ጥያቄው ባሻገር ደግሞ የሙስሊሞች መቃብር እንዲታጠር ጠይቀው እንዳልተፈጸመ፣ ሙስሊሞች እርድ የሚፈጽምበት ቦታ ቢሰጣቸውም ሥጋ የሚከፋፈሉበት ቦታ ግን እንዳላገኙ ይጠቅሳሉ።

በአክሱም የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የሚፈጽሙበት ቦታ ሲጠይቁ ዘመናት ተቆጥረዋል። የደርግ ሥርዓት በወደቀበት የመጀመሪያ ዓመታት አክሱም ውስጥ በሃይማኖት ሰበብ በተቀሰቀሰ ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱም ይታወሳል።

አጭር የምስል መግለጫ የአክሱም ፅዮን ማሪያም ቤተክርስቲያን

''አክሱም ከአንድ ቤተክርስትያን በላይ መሸከም አትችልም''

የአክሱም ገደማትና አድባራት ምክትል አስተዳደር በኩረ ሊቃውንት ጎደፋ መርሃ አክሱም ውስጥ የተለያየ እምነት ያላቸው ሰዎች በሰላም መኖር እንደሚችሉ ይናገራሉ። "ነገር ግን አንዲት ቤተ-ክርስትያን ነች ያለችው፤ ከዚያ ውጭ ሌላ ከተጨመረ ግን የነበረውን ታሪክ ማበላሸት ነው" የሚል የጸና እምነት አላቸው።

"አንዲት ቤተ-ክርስቲያን ግን የተለያዩ እምነቶች በሰላም እና መቻቻል የሚኖሩባት ከተማ ነች" ይላሉ አክሱምን።

''አዲስ መንግሥት በመጣ ቁጥር 'መስጅድ ይሰራልን' እያሉ የሚጠይቁ ሰዎች አሉ" የሚሉት ምክትል አስተዳደሪው፤ ይህንን ጥያቄ የሚያቀርቡት ደግሞ ከሌላ ቦታ የመጡ ሙስሊሞች ናቸው ይላሉ።

ምሳሌም ሲጠቅሱ "የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ከተከፈተ ጀምሮ ጥያቄዎች በማንሳት አክሱም ውስጥ ተወልደው ባደጉት ላይ ተጽኖ እየተፈጠረ ነው። አክሱም ተወልደው ያደጉት ግን ምን የጎደለብን ነገር የለም ነው የሚሉት።" ይላሉ።

"አንድ ሙስሊም ሲሞት፤ ቄስ፣ ዲያቆን እና ምዕመናን ሄደው ይቀብራሉ፣ ያስተዛዝናሉ፣ ያጽናናሉ። በሰርግ ጊዜም እንደዚሁ። የሚካኤል፣ የማርያም ጸበል ሲኖርም ይመጣሉ። አብረን ነው የምንኖረው። እኔ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ነኝ። የልብ ጓደኛዬ ሙስሊም ነው። ልዩነት የለንም'' በማለትም ይናገራሉ።

የሞት ፍርደ ውድቅ የተደረገላት አሲያ ቢቢ ካናዳ ገባች

ቴምር በረመዳን ለምን ይዘወተራል?

ከዚህ አንጻር አቶ አብዱ መሃመድ ከውጭ የሚገፋፋቸው ኃይል አለ በሚለው ሃሳብ አይስማሙም። ከአሁን በፊትም እስላማዊ ትምህርት ቤት ለመስራት ተፈቅዶላቸው መንግሥት መሬት ሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ እንዳልተደረገ ያስታውሳሉ።

በአክሱም የሚኖሩት ሙስሊሞችና ክርስትያኖች ጥብቅ ትስስር እንዳላቸው የሚናገሩት በኩረ ሊቃውንት ጎደፋ ''መስጂድ የሚጠይቀው ሰው አሜሪካ ያለው ነው። ድሬዳዋ እና ጂማ ሆነው 'ፍትህ ለአክሱም ሙስሊሞች' እያሉ ሰው የሚያነሳሱ ምን አገባቸው? እኛ ተከባብረን ነው የምንኖረው'' ሲሉ ይጠይቃሉ።

ጨምረውም አክሱም ውስጥ አስራ ሦስት የሙስሊሞች መስገጃ ቦታዎች እንዳሉና "'መስጅድ የለም' የሚሉት አዲስ አበባ ያሉት ናቸው። 'ምልክት ይደረግበት' ይላሉ። ምልክት ከፈለጉ ከአክሱም 15 ኪሎ ሜትር ውቅሮ ማራይ ወይም አድዋ ሄደው መጠቀም ይችላሉ።''

አክሱም ውስጥ አይታሰብም

በኩረ ሊቃውንት ጎደፋ መርሃ አክሱም ውስጥ መስጂድ መሰራት የለበትም ብለው ከሚያምኑ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው "አክሱም ውስጥ መስጅድ እንዲሰራ ባለመፈቀዱ ሙስሊሞች ይከፉ ይሆናል። እኛ ኦርቶዶክሶች ደግሞ ለምሳሌ መስጅድ ይሰራ የሚል ትእዛዝ ቢመጣ እንሞታለን" በማለት እንደማይቀበሉት ይናገራሉ።

ለዚህ እንደ ዋና ምክንያት የሚያስቀምጡት ወላጆቻቸው ለዘመናት ያቆዩት ታሪክ እንዲለወጥ አለመፈለጋቸው መሆኑን ጠቅሰው "ወላጆቻችን በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ከዚች አንድ ስንዝርም እንዳትቀንሱ እንዳትጨምሩ ብለውን ቃል አስገብተውን ነው ያለፉት" በማለት በከተማዋ መስጅድ መገንባት እንደሌለበት ይሞግታሉ።

ከሚቀርበው ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ክርክር ባሻገር የከተማዋ ሙስሊም ነዋሪዎች ጥያቄ ከሰብዓዊ መብት አንጻርም መታየት አለበት የሚሉ ሰዎች በርካቶች ናቸው። የአክሱም ገደማትና አድባራት ምክትል አስተዳደሪው ግን ይህን "መብት የሁለቱም ወገን ጥያቄን የሚያቅፍ መሆን አለበት" ብለው ይቃወማሉ።

"ለብዙ ዘመናት ቅድመ አያቶቻቸው ያልነበራቸውን ነገር እንዴት አሁን ይጠይቃሉ። ወላጆቻቸው ያቆዩላቸው ነገር ብንከለክላቸው ኖሮ አሁን ጥያቄ ማንሳት ይቻል ነበር። መስጅድ ላይ ምልክት ይደርግበት ማለት ግን ያልነበረ ነገር ነው፤ ታሪክ ማበላሸትም ነው" ሲሉ ይከራከራሉ።

ወደ ለንደን የሚሄደው አስደናቂው የትራምፕ ጓዝ

አጭር የምስል መግለጫ ሙስሊም እናቶች በውቅሮማራይ መስጂድ ውስጥ

አክሱም ክርስትያናዊት ከተማ

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት መሪዎች በአክሱም ከተማ በያሬዳዊ ቃና የታጀበ ቃለ እግዚአብሔር ብቻ ነው መሰማት ያለበት የሚል ጠንካራ ኣቋም አላቸው። የተቀደሰ ስፍራ ነው ብለውም ያምናሉ።

የአክሱም ገደማትና አድባራት ምክትል አስተዳደሪ የሆኑት በኩረ ሊቃውንት ጎደፋ መርሃ "ሙስሊሞች መካን አክብረው እንደሚይዙዋት ሁሉ፤ አክሱምም ለእኛ መካ ማለት ነች። አክሱም ውስጥ ሌላ ድምጽ መሰማት የለበትም። አላህ ወአክበር የሚል ድምጽ ከተሰማ፡ አክሱም ገዳም መሆኗ አበቃ ማለት ነው" ይላሉ።

የአክሱም ፅዮን ማርያም አገልጋይ የሆኑት በትረ ትጉሃን አምሳሉ ስቡህ በበኩላቸው "ጽላተ ሙሴ ባለበት ስፍራ ሌሎች እምነቶች ሊኖሩ አይገባም። ይሄ እምነት እንጂ ጭካኔ አይደለም። በጉልበት እንዲሰራ ከተፈለገ ግን ጦርነት ማወጅ ማለት ነው" በማለት ጉዳዩ አላስፈላጊ መዘዝ እንዳያስከትል ያሳስባሉ።

ከአክሱም በ15 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ውቅሮማራይ የምትባል አነስተኛ ከተማ ትገኛለች። በአንድ መስጊድ በርከት ያሉ እስልምና አማኞች ተሰብስበው እየሰገዱ ነው። ሴቶች ደግሞ የሚበላና የሚጠጣ እያቀረቡ ነበር።

ከመካከላቸውም እድሜያቸው ከ50 እንደሚያልፍ የሚናገሩት እናት "በከተማችን አምስት መስጊዶች አሉ። አክሱም የማርያም ጽዮን መቀመጫ ነች ብለው ስለሚያምኑ በአክሱም ከተማ ግን ከጥንትም መስጊድ ኖሮ አያውቅም። በመመካከርና በሰላም መስጂድ ቢሰራ ጥሩ ነው፤ ከዚያ ውጪ ግን እኛ ከወላጆቻችን አንበልጥም። ሰላም ነው የምንፈልገው" ይላሉ።

አጭር የምስል መግለጫ ከአክሱም 15 ኪሎሜትር ርቀት ርቆ ውቅሮማራይ ከተማ የሚገኘው መስጂድ

ተግባብተን መስራት እንፈልጋለን

በአጸደ እንዳ'ሚካኤል ቤተክርስትያን የሚያገለግሉት ሊቀ ካህናት ተክለሃይማኖት በአክሱም ከተማ ውስጥ መስጂድ እንዲሰራ የመፍቀድም ሆነ የመከልከሉ ነገር በመንግሥት የሚወሰን ጉዳይ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

እንደ እርሳቸው እምነት ይህ የሆነው "መንግሥት መስጊድ ይሰራ ብሎ ቢፈቅድ በነገታው የሚከተለውን አደጋ ስለተረዳ እንጂ ክርስትያንን ወዶ ሙስሊሙን ስለጠላ አይደለም" በማለት ጉዳዩን ከአክሱም ህዝብ ባሻገር የትግራይ ህዝብ ብሎም የኢትዮጵያ ህዝብን የሚመለከት ነው እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

መካ ለሙስሊሞች ቅዱስ ቦታ እንደሆነው ሁሉ አክሱምም ለኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ቅዱስ ቦታ ነው የሚሉት ሊቀ ካህኑ "በመካ ቤተ ክርስትያን ቢሰራም ባይሰራም በእኛ ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም። እኛ ግን አንፈቅድም" ሲሉ ፈርጠም ብለው ይናገራሉ።

በአክሱም ከተማ ጋር ተያይዞ ስለሚነሳው የእስልምና እምነት ተከታዮች መስጂድ እንዲኖራቸው የመፈለግ ጥያቄን በተመለከተ የከተማ አስተዳደር የሚሰጠው ምላሽ ካለ ለቀረበላቸው ጥያቄ አስተያየት ለመስጠት ፈቃኛ ሳይሆን ቀርቷል።

የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ዋና ጸሐፊ አቶ መሐመድ ካሕሳይ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ በኩል መስጂድ እንዲኖር ፍላጎቱ እንዳለ ጠቅሰው "ሕዝበ ሙስሊሙና ክርስትያኑ አምኖበት ነው ይህ ነገር እውን እንዲሆን የምንፈልገው። ተግባብተን ነው መስጂድ መስራት የምናስበው" ብለዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ