ስለ ግንቦት 27፤ 1983 የጎተራው ግምጃ ቤት ፍንዳታ ምን ያስታውሳሉ?

የጎተራ መሣሪያ ማከማቻ ከፈነዳ 28 ዓመት አለፈው Image copyright Francoise De Mulder

ግንቦት 27፤ 1983 ዓ.ም.፤ ደርግ ወድቆ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥልጣን ከያዘ አንድ ሳምንት ሞልቶታል። አዲስ አበባ ከጥይት እና መሰል ድምፆች ጋብ ብላ በእርጋት ማሰብ የጀመረችበት ወቅት ነበር።

ነገር ግን ሌሊት 10 ገደማ የሆነውን ማንም አልጠበቀውም። ሃገር ሰላም ብለው እንቅልፍ ላይ ያሉ አዲስ አበባውያንን ቀልብ የገፈፈ ክስተት። ከ100 በላይ ሰዎችን የቀጠፈ ጉድ።

ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በዕለቱ ያወጣው ዕትም ላይ የአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር በግምት 3 ሚሊዮን ይሆናል ይላል። ታድያ ይህን ሁሉ ሰው በአንዴ 'ክው' የሚያደርግ ምን ሊሆን ይችላል?

የተሰማው ፍንዳታ ነበር። ከበ...ድ ያለ ፍንዳታ። ከጎተራ እስከ ሰሜን ሆቴል የተሰማ። ከአቃቂ እስከ ኮተቤ ቀልብን የገፈፈ።

መታሰቢያ ሸዋዬ ይልማ የዛኔ የ12 ዓመት ታዳጊ ነበርኩ ትላለች፤ የ7ኛ ክፍል ተማሪ። ቢሆንም ክስተቱን መቼም አትረሣውም።

«የዛን ሰሞን ከሁለት ሳምንት ጀምሮ ትምህርት ተዘግቶ ነበር። ልክ ጓድ መንግሥቱ ኃይላማርያም ከሃገር ኮበለሉ ተብሎ የተነገረ 'ለት [ግንቦት 13] ቤተሰቦቻችን ለቅመውን ወደ ቤት ገባን። ከዚያ በኋላ ትምህርት አልነበረም። አስጨናቂ ሳምንት ነበር። ልክ በሳምንቱ [ግንቦት 20] የኢህአዴግ ሠራዊት አዲስ አበባ ገባ። ከዚያ በኋላ የጥይት ድምፅ አልነበረም፤ ትንሽ ጋብ ብሎ ነበር።»

የዛሬ 30 ዓመት... የኮ/ል መንግሥቱ አውሮፕላን ለምን አልጋየም?

አዲስ አበባ ከዚያ በፊት በነበሩት ሳምንታት የጥይት ይሁን መሰል ፍንዳታዎች ድምፅ ይህን ያህል ብርቋ አልነበረም። መታሰቢያ ትቀጥላለች. . .

«ከእንቅልፋችን የቀሰቀሰን ፍንዳታው ነበር። መሬት 'ሚያንቀጠቅጥ ዓይነት ፍንዳታ ነበር። በዚያ ላይ ጨለማ ነው። ምን እንደሆነ አላወቅንም፤ እስከዛን 'ለት ከሰማናቸው ፍንዳታዎችም በጣም የተለየ ነበር። ሁሉም ሰው ተነሳ፤ ነገር ግን ግራ በገባው ስሜት ውስጥ ነበር። ጦርነት ነው እንዳንል ጦርነቱ አልቋል. . .ምን እንበለው? አየቆየ ሲመጣ የጥይት የሚመስሉ ትንንሽ ፍንዳታዎች መስማት ጀመርን።»

ፍንዳታውን የሸሹ ሰዎች እግራቸው ወደመራቸው መትመም ያዙ። ወደ እነመታሰቢያ ሠፈርም የመጡ አልጠፉም።

«እንግዲህ አስበው ሠፈራችን ሰሜና ማዘጋጃ ነው። ግን ፍንዳታውን የሸሹ ሰዎች በግምት ከፍንዳታው አንድ ሁለት ሰዓት በኋላ እኛ ሠፈር ደርሰዋል። ወላጆቼ ወጥተው ሲጠይቁ ፍንዳታ እንደሆነ ተረዱ። የሚቀጣጠል ነገር እንዳለም ከሰዎቹ ሰሙ። ወላጆቼም ግራ ገብቷቸው ነበር። እኛም እንውጣ ወይስ ትንሽ እንጠብቅ ዓይነት ነገር ነበር የነበረው። መጨረሻ ላይ አንድ ድብል...ቅ ያለ ፍንዳታ ተሰማ። በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ መስኮታችን ሁላ የሚረግፍ ነበር የመሰለው። ከዚያ በኋላ ነው ፍንዳታውም የተረጋጋው፤ ቀኑም እየነጋ መጣ።»

የጦር መሣሪያ ማከማቻ

ይድነቅ አብርሃ ክስተቱን ለመዘገብ ካሜራቸውን አንግበው ወደሥፍራው ካመሩ ሰዎች መካከል ነበር። ይድነቅ በወቅቱ የሚያነሳቸውን ፎቶዎችን እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለሕወሓት ማሕደር ክፍል ያስረክባል። ቢሯቸው የነበረው ደግሞ አቡነ ጴጥሮስ አካባቢ የነበረው የኢትዮጵያ ራድዮ ዋና መሥሪያ ቤት።

«ፍንዳታውን ስንሰማ የኛ 'ክሩ' ቪዲዮ እና ፎቶግራፍ ለማንሳት ወደዚያ ሄደ። የፈነዳው የጦር መሣሪያ ማከማቻ የነበረ ሥፍራ ነበር፤ በርካታ ብረታብረቶችም ነበሩ ሥፍራው ላይ። ፍንዳታው አካባቢው በጭስ እንዲዋጥ አድርጎ ነበር። ብዙ ተጎጅዎችም ነበሩ። በርካቶች ሞተዋል፤ የቆሰሉም የትየለሌ ነበሩ። እኛ ፎቶ እና ቪደዮ ስናነሳ የነበረው እዚያ የነበረውን ሁኔታ ነበር።»

ያኔ ጎተራ፤ እንደዛሬ በማሳለጫ ሳትከበብ ግዙፍ የነዳጅ ማከማቻ እና የለስላሳ ፋብሪካ አልተለይዋትም ነበር። የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መናኸሪያም ነበረች ጎተራ። «በጣም አስገራሚው ነገር እንዲያውም ነዳጅ ማደያው አለመፈንዳቱ ነው» ትላለች መታሰቢያ።

«ጎተራ፤ አሁን ያለውን ቅርፅ ሳይዝ በፊት 'ኮንፊውዥን ስኩዌር' ነበር የምንለው። መዓት አስፋልቶች የሚገናኙበት ነበር፤ ባቡሩም ያልፍ ነበር በዚያ በኩል። በሁለቱም አቅጣጫ ነዳጅ ማከማቻዎች ነበሩ፤ የእህል ጎተራው አለ፤ ለስላሳ ፍብሪካው አለ። ሰዉ በኋላ ላይ እንደ ተዓምር ያወራው 'ነዳጅ ማደያዎቹ አለመፈንዳታቸው' እያለ ነበር። ምክንያቱም አደጋ የበለጠ የከፋ ይሆን ነበር።

በወቅቱ በፍንዳታው ምክንያት ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነገረ። የቆሰሉም በርካታ ነበሩ። ያኔ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር ጣቱን በደርግ ሰዎች ላይ ቀሰረ። ማካማቸውን ሆን ብለው ያፈነዱት የደርግ 'ርዝራሾች' ናቸው አለ።

ምሽት ላይ ዜና ሲነበብ ከአደጋው ሌላ አስደንጋጭ ዜና ተሰማ፤ ታዋቂው ጋዜጠኛ ሞሐመድ አሚን በፍንዳታው ምክንያት አንድ እጁን ማጣቱ።

ኮሎኔል መንግሥቱ ለህፃናት አምባ ልጆች ደብዳቤ ላኩ

Image copyright Francoise De Mulder

ሞሃመድ አሚን

ይድነቅ ስለ ሞሐመድ የሚያስታውሰውን ሲወጋ «እኛ በሥፍራው ስንደርስ ሞሐመድ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ፎቶ እያነሱ ነበር» ይላል።

ሞሐመድ አሚን እጁ ላይ ጉዳት የደረሰበት በሁለተኛው ፍንዳታ ነው። ከዚያ በፊት ግን ፍንዳታውን እና አካባቢውን እየዞረ ሲቃኝ፤ ምስልም ሲወስድ ነበር። ነገር ግን ሁለተኛው ፍንዳታ የእርሱን ግራ እጅ የባልደረባው ጆን ማታይን ነብስ ሊወስድ ግድ ሆነ።

«እነዚህማ ለገንዘብ ብለው ነው እንጂ እንዴት እንዲህ ዓይነት ሥፍራ እየገቡ ፎቶ ያነሳሉ በማለት ራቅ ብለን የቆምነው እኔና የኛ ካሜራ ክሩ ስናወጋ ነበር» ይላል ይድነቅ የሞን ጀግንነት ሲያስታውስ።

«አደጋው ሲደርስ በሥፈራው የነበረው አምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ወሰዳቸው። ሥራው ግርግር ነበረው። ካሜራቸውን ጥለው ነበር የሄዱት። እኛ ነን ካሜራቸውን ሰብስበን ያስቀመጥንላቸው።»

እርግጥ የዛኔ ታዳጊ ነበርሽ። ቢሆንም የአደጋው ምክንያት ምን እንደነበር ታስታውሻለች? ለመታሰቢያ ያቀረብንላት ጥያቄ. . .

«እኔ እሱ ነገር ምንም ትዝ አይለኝም። ቀልቤን ስቦት የነበረው ምሽት ላይ የተነገረው ዜና ነው። ሞሐማድ አሚን በፍንዳታው ምክንያት ጉዳት ደረሰበት ተብሎ ሲነገር። ሞሐመድ አሚን ለእኔ በጣም ትልቅ 'አይዶል' ብዬ የምለው ጋዜጠኛ፤ ከኢትዯጵያ ጋር ልዩ ቁርኝት ያለው ሰው ነው።»

ሞሐመድ አሚን አንድ እጁ ጉዳት ደርሶበት እንኳ በአንዱ እጁ ይቀርፅ ነበር አሉ። እውነት ይሆን? ማን ያውጋ የነበረ. . .እንዲሉ ይህን ጥያቄ ለይድነቅ ሰነዘርንለት።

«አይይይይይ. . .እውነት አይደለም። ብዙ ደም እየፈሰሰው ነበር እኮ። ኋላ ላይ በሕክምና ተቆረጠ አንጅ፤ አንድ እጁ ተንጠልጥሎ ነበር። 'ሬዚዝታንስም' አልነበረውም፤ ያ ሁሉ ደም እየፈሰሰ እንዴት ብሎ? ካሜራው እኮ ወድቋል። አምቡላንስ ለሕክምና ወሰደው፤ ንብረቱን ደግሞ እኛ ይዘንለት ሄድን። በኋላ ነው መጥቶ የተረከበው።»

ድኀረ-ኢሕአዴግ ትውልድ ስለ ጎተራው ፍንዳታ እምብዛም ትዝታ ላይኖረው ይችል ይሆናል። በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ሥፍራ ካለው ወርሃ ግንቦት ክስተቶች አንዱ መሆኑ ግን አልቀረም። እኛም ለማጣቀሻ ይሆን ዘንድ ይህችን ከተብናት።

በመፈንቅለ መንግሥቱ ዙሪያ ያልተመለሱት አምስቱ ጥያቄዎች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ