እግር ኳስ ተጫዋቹ ወንድወሰን ዮሐንስ እንዴት ተገደለ?

ወንድወሰን ዮሐንስ Image copyright Nekemte City Football

ትናንት ህይወቱ ያለፈው የነቀምት ከነማ ተጫዋች ወንድወሰን ዮሐንስ አሟሟት አጠያያቂ ሆኗል።

የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ ትናንት ምሸት በነቀምት ከተማ በአንድ ሆቴል ላይ በተወረወረ ቦንብ አንድ ሰው ተገደለ ቢሉም ሟቹን በቅርብ የሚያውቁ እና የሆስፒታል ምንጮች ደግሞ ወጣቱ የተገደለው በጥይት ተመትቶ ነው ይላሉ።

አቶ አዲሱ አረጋ ትናንት ከምሽቱ 1 ሰዓት አካባቢ ነቀምት ከተማ 'ፋክት' በሚባል ሆቴል ላይ በተወረወረ ቦምብ ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውንና አንድ ሰው መገደሉን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፈረዋል።

አቶ አዲሱ የሟቹንም ሆነ በቦንብ ፍንዳታ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር አልጠቀሱም።

የደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ስጋት ላይ ነን ይላሉ

ስለ ግንቦት 27፤ 1983 የጎተራው ፍንዳታ ምን ያስታውሳሉ?

ድምጻዊ ዳዲ ገላንን ገድሏል የተባለው የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

አቶ ቾምቤ ገ/ህይወት የነቀምት ከነማ አሰልጣኝ ሲሆኑ፤ ትናንት የተገደለው ወጣት የቡድናቸው ተጫዋች መሆኑን አረጋግጠዋል።

አቶ ቼምቤ እንደሚሉት ሟች ወንድወሰን ዮሐንስ ህይወቱ ያለፈው በቦንብ ፍንዳታ ሳይሆን ከፍንዳታው በኋላ በተተኮሰበት ጥይት መሆኑን ያስረዳሉ።

''እራት ለመብላት አምስት ሆነን ወጣን። እነሱ የፈረንጅ ምግብ መብላት ፈልገው 'ፋርም ላንድ' ወደሚባል ሆቴል ገቡ። እኔ ደግሞ እነሱ ካሉበት ጎን ወደሚገኘው 'ፋክት' ሆቴል ገባሁ። ቦምቡ የፈነዳው እኔ የነበርኩበት ሆቴል ውስጥ ነው'' የሚሉት አቶ ቾምቤ፤ በፍንዳታው ጉዳት ባይገጥማቸውም፤ ከተፈጠረው ግርግር ለማምለጥ ሲሞክሩ የመፈነካከት ጉዳት እንደደረሰባቸው ያስረዳሉ።

''ቦምቡ ከፈነዳ በኋላ እነ ወንደሰን ደውለው ደህን መሆኔን ጠይቀውኝ ነበር'' የሚሉት አቶ ቾምቤ፤ ተጫዋቾቹ በፍጥነት ከሚገኙበት ሆቴል ወደ መኖሪያ ቦታቸው እንዲሄዱ እንደነገሯቸው አቶ ቾምቤ ያስታውሳሉ።

''ህክምና ለማግኘት ወደ ግል ክሊኒክ ሄጄ ነበር። እዛ እያለሁ አንድ የጸጥታ ኃይል አስከባሪ የሆነ ሰው ስልክ ደውሎ ወንድሰን በጥይት ተመትቶ ሆስፒታል እንደሚገኝ ነገረኝ'' በማለት ትናንት የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

አቶ ቾምቤ ሆስፒታል ሲደርሱ ተጨዋቹ ህይወቱ አልፎ ነበር።

በነቀምት ሆስፒታል ሃኪም የሆኑት ዶ/ር ዳምጠው ጋረደው ተጨዋቹ በጥይት ተመትቶ ህይወቱ ማለፉን ያረጋግጣሉ። ''በስተቀኝ በኩል ከብብቱ ስር የተመታ ሲሆን ጥይቱ በግራ በኩል ወጥቷል'' ያሉት ዶ/ር ዳምጠው፤ ወንድወሰን ወደ ሆስፒታል የመጣው ከምሸቱ ሁለት ሰዓት አከባቢ እንደሆነ እና ሆስፒታል ሲደርስም ህይወቱ አልፎ እንደነበረ ይናገራሉ።

ወንድወሰን ለምን እና ማን በተኮስው ጥይት እንደተገደለ የታወቀ ነገር የለም። ስለጉዳዩ ማብራሪያ ለመጠየቅ ፖሊስን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

'ፋክት' በሚሰኘው ሆቴል ላይም ማን እና ለምን የቦምብ ጥቃት እንደሰነዘረ ባይገለጽም፤ አቶ አዲሱ ትናንት በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ ቦምቡን የወረወሩ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል።

'ፋክት' ሆቴል በነቀምት ከተማ በርካታ ተጠቃሚ ካላቸው ታዋቂ ምግብ ቤቶች መካከል አንዱ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። በተጨማሪም የምስራቅ ወለጋ ዞን ፖሊስ ጽ/ቤት፣ ፍርድ ቤት እና የዞኑ አስተዳደር ቢሮዎች 'ፋክት ሆቴል' በሚገኝበት አቅራቢያ ይገኛሉ።