የሱዳን አለመረጋጋት በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ምንድነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በካርቱም አየር ማረፊያ ደርሰው አቀባበል ሲደረግላቸው Image copyright PM office

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ፍጥጫ ላይ ያሉትን የሱዳን መንግሥት ወታደራዊ መሪዎችና ሕዝባዊ ተቃውሞውን የሚመሩትን ተቃዋሚዎች ለማነጋገር ዛሬ ጠዋት ሱዳን መዲና ካርቱም ገብተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ የኢታማዦር ሹሙ ጄነራል ሰዓረ መኮንን፣ አምባሳደር ሙሐመድ ድሪር ከልኡክ ቡድኑ አባላት መካከል ይገኙበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ካርቱም ያቀኑት ሰሞኑን የተከሰተውን ደም አፋሳሽ ግጭት ተከትሎ ነው። በጉዟቸውም በሃገሪቱ የነገሰውን ውጥረት ለማብረድ አልበሸርን ከስልጣን አንስተው ጊዜያዊውን አስተዳደር የሚመሩትን ወታደራዊ ባለስልጣናት አነጋግረዋል።

ወታደራዊው አስተዳደር ስልጣኑን በቶሎ ለሲቪሎች እንዲያስረክብ ግፊት እያደረጉ ያሉትና በርካታ ደጋፊዎቻቸው እንደተገደሉባቸው የሚናገሩትን የተቃዋሚውን ቡድን መሪዎችን ያናግራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር የግብፅ መንግሥት ተወካዮችም ውጥሩቱን ለማርገብ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ሱዳን ግብተዋል። በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ሰላምና ደህንነት ኮሚሸነር ስማሊ ቼሩጉኢ አብረው አብረው እንደሚሆኑ ተነግሯል።

የአክሱም ሙስሊሞች ጥይቄ መቼ ምላሽ ያገኝ ይሆን?

አፍሪካውያን ስደተኞች በአሜሪካ ድንበር ደጅ እየጠኑ ነው

ካፍ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ድጋሚ እንዲካሄድ አዘዘ

የሱዳን አለመረጋጋት በኢትዮጵያ የሚያስከትለው ተጽእኖ ምንድነው?

በኪል ዩኒቨርሲቲ መምህር ለሆኑት አዎል አሎ (ዶክተር) የሱዳን አለመረጋጋት በኢትዮጵያ ላይ ሊፈጥር የሚችለው ቀጥተኛ ተጽእኖ ምንድነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ መስጠት የጀመሩት ሁለቱ ሃገራት ሰፊ ሊባል የሚችል ድንበር እንደሚጋሩ በማስታወስ ነበር።

''ሁለቱ ሃገሮች ሰፊ እና ብዙ ህዝብ የሚመላለስበት ድንበር ይጋራሉ። ሰላም እና ጸጥታ በሁለቱም ሃገራት ድንበር ላይ የማይኖር ከሆነ፤ የተለያዩ ችግሮች ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ይችላል።'' ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዳለ የሚያስታውሱት ዶክተር አወል አሎ፤ ''የሱዳን አለመረጋጋት ይህንን የሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ሰፋ ባለ ሁኔታ ሊያበረታታ ይችላል'' ይላሉ። ዶክተር አዎል አሎ፤ በኢትዮጵያ አለመረጋጋት እያለ የጎረቤት ሃገር መንግሥስትም ሃገሩን መቆጣጠር ካልቻለ፤ ኢትዮጵያን ችግር ውስጥ መክተት ለሚፈልጉ ኃይሎች የሱዳን ምድርን ጥቅም ላይ ሊያውሉ እንደሚችሉ ያስረዳሉ።

ዶ/ር አወል ኢትዮጵያ ሱዳንን በተመለከተ ሌላው ያላት ፍላጎት የአባይ ግድብን በተመለከተ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ''በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል ያለችው ሃገር ሱዳን ነች። በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል አለመግባባቶች ተፈጥረው ወደ ሌላ ደረጃ ቢሸጋገር እንኳ ሱዳን የምትጫወተው ሚና ቀላል አይደለም'' ይላሉ።

Image copyright PMO

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በሱዳን ምን ይገጥማቸው ይሆን?

የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን በቅረበት የሚከታተለው የቢቢሲው ጋዜጠኛ ፈረጌል ኬን ''የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ከእርሱ በእጅጉ የተለዩ ከሆኑት የሱዳን አጋሮቹ ጋር ነው የሚገናኘው'' ይላል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይን ''የቀድሞ የጦር መሪ፤ አሁን ግን በርካታ ላውጦችን ያስመዘገበ መሪ'' ሲል የሚገልጽ ሲሆን፤ የሱዳን ጊዜያዊ ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት መሪዎችን ደግሞ ''ወታደራዊ የሆነ መንግሥታዊ ስርዓትን ለመዘርጋት ቆረጠው የተነሱ'' ሲል ይገልጻቸዋል።

ፈረጌል ኬን በሱዳን ጉዳይ ያገባኛል የሚሉት አካላት ብዛት እና የፍላጎት መለያየትን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ሁሉንም አካላት ማግባባት ቀላል ሊሆን እንደማይችል ግምቱን ያስቀምጣል።

የአፍሪካ ህብረት ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር እስክትመለስ ድረስ ከየትኛውም የህብረቱ እንቅስቃሴ ማገዱ ተገቢ የሚያደርጉ ምክንያቶች አሉ የሚለው ፈረጌል ኪን፤ አፍሪካዊ ያልሆኑት ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች በሱዳን ላይ እያሳደሩ ካሉት ተጽእኖ በላይ የአፍሪካ ህብረት ፈላጭ ቆራጭ መሆን ይጠበቅበታል። ምክንያቱም በሱዳን ነገሮች ቢባባሱ ችግሩ የሚተርፈው ለአህጉሪቱ አገራት እንጂ ለሳዑዲ እና ለአረብ ኢሚሬቶች አይደለምና ይላል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጉዞ የሚደረገው 108 ተቃዋሚ ሰልፈኞች መሞታቸው ከተነገረና ትናንት አፍሪካ ህብረትም ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር እስክትመለስ ድረስ ከየትኛውም የህብረቱ እንቅስቃሴ እንዳገዳት ካስታወቀ በኋላ ነው።

በኪል ዩኒቨርሲቲ መምህር ለሆኑት አዎል አሎ (ዶክተር) የጠቅላይ ሚንስትሩን ጉብኝት ወቅታዊ ነው። ነገሮች ተባብሰው የተለያዩ ኃይሎች ከመፈጠራቸው በፊት ኢትዮጵያ የአስታራቂነት አስተዋጽኦዋን መወጣት ያለባት አሁን ላይ ነው ባይ ናቸው።

ሰሞኑን በተካሄደው ደም አፋሳሽ ተቃውሞ ውስጥ የሀገሪቱ ልዩ ኃይል በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ እርምጃ መውሰዱ የተነገረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሱዳን ከተሞች በስፋት ተሰማርተው ይገኛሉ ተብሏል።

የሱዳን ጤና ጥበቃ ሚኒስትር የተገደሉት ተቃዋሚ ሰልፈኞች 61 ብቻ ናቸው ያሉ ሲሆን፤ ከተቃዋሚ ሰልፈኞች ጋር ግንኙነት ያላቸው የሐኪሞች ቡድን ግን ሟቾቹ 100 እንደሆኑ መግለፃቸው ይታወሳል።

ለወራት የዘለቀው ተቃውሞ ወደ ብጥብጥ ያደገው ሰኞ ዕለት የደህንነት ኃይሎች ለወራት ከመከላከያ ኃይሉ ዋና መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት በመቀመጥ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ሰልፈኞችን ማዋከብ ከጀመሩ በኋላ ነው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሺር ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ይሄኛው ወታደሩ የወሰደው እርምጃ ከፍተኛ ሟቾች የተመዘገበበት ነው።

ከሰኞ ጀምሮ በተቃዋሚዎች እና በወታደራዊ ምክር ቤቱ መካከል ሲደረግ የነበረው ንግግር የተቋረጠ ሲሆን በርካታ ምዕራባውያን ሃገራትም በሱዳን ጉዳይ ያላቸውን ስጋት ገልጠዋል።