የሞተር ብስክሌቶች እና ሕገወጥነት በአዲስ አበባ

አዲስ አበባ ፖሊስ አርማ Image copyright Addis ababa Police Facebook page

ግንቦት 28 ቀን 2011 ዓ/ም ከቀኑ 10 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ሲሆን ወ/ሮ ብሩክታዊት ጌታሁን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ስፋራው አውራሪስ ሆቴል አካባቢ ከሚገኘው የአብሲኒያ ባንክ 22 ቅርንጫፍ ገንዘብ ገቢ ለማድረግ እየሄዱ ነበር።

ወደ ባንኩ ከመድረሳቸው በፊት ግን በሞተር የታገዙ ዘራፊዎች የያዙትን ገንዘብ ነጠቋቸው።

ግለሰቧ ገንዘቡን ይዘው የነበረው በፌስታል እንደነበር አብረዋቸው የነበሩት አቶ አለማየሁ ግርማ ለፖሊስ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሱዳን ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል

ኔይማር ደፍሮኛል ያለችው ሴት ቲቪ ላይ ቀርባለች

እግር ኳስ ተጫዋቹ ወንድወሰን ዮሐንስ እንዴት ተገደለ?

የያዙትን ገንዘብ ለመንጠቅ ትግል ሲደረግም ገንዘቡ ይዘረገፋል። ያኔ በአካባቢው የነበሩ ሰዎችና የጥበቃ ሰራተኞች ዘራፊዎችን ለመከላከል የአቅማቸውን ጣሩ።

ግለሰቧ በፌስታል ይዘውት ከነበረው 405 ሺህ ብር መካከልም ከ3 መቶ ሺህ ብር በላይ ማትረፍ እንደተቻለ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ አክሎም ወንጀል ፈፃሚዎቹ ሲገለገሉበት የነበረ አንድ ሞተር ብስክሌት መያዙንም ገልጿል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ኮማንደር ፋሲካው በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በሞተር የታገዘ ዘረፋ እንደሚካሄድ ይሰማል። ነዋሪውም ምሬቱን ይገልፃል ብለን ስለጉዳዩ ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ የሞተር ብስክሌቶች በተለያዩ ወንጀሎች መሳተፍ ብቻ ሳይሆን በጣም በርካታ የሆነ የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ላይም ይገኛሉ ብለዋል።

የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አክለውም አንዳንድ የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች ሐሰተኛ የመንጃ ፈቃድ ይዘው እንደሚያሽከረክሩ፣ ሞተሩ ላይ የራሱ ያልሆነ ሰሌዳ በመለጠፍ እንደሚንቀሳቀሱ ይናገራሉ።

ሰሌዳ ሳይኖራቸው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መጥተው አዲስ አበባ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መኖራቸውንም አልሸሸጉም። ሞተር ብስክሌቶቹ ሥርዓት ይዘው መስራት እንዳለባቸው ስለታመነ በመንግሥት ደረጃ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው የሚሉት ኮማንደር ፋሲካው ችግሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ያገኛል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ቀምተው የሚሮጡ፣ በትራፊክ ደንብ መተላለፍ ጥፋት ላይ የተገኙ ከአስር ሺዎች በላይ ሞተር ብስክሌቶች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ኮማንደር ፋሲካው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በቅሚያ ተግባር ላይ የተሳተፉ ሞተር ብስክሌቶችንም ቢሆን ቀላል ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉትን በቁጥጥር ስር አውለናል ይላሉ።

ኮማንደር ፋሲካው በአዲስ አበባና በኦሮሚያ የሞተር ብስክሌቶች ሰሌዳ አምስት ዲጂት አለመድረሱን አስታውሰው በሕገወጥ ተግባር ላይ የሚሰማሩ ሞተር ብስክሌቶች ሰሌዳቸውን ከሌላ መኪና ላይ ስለሚወስዱ ነዋሪው አጠራጣሪ ነገሮችን በሚመለከትበት ወቅት ጥቆማ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በአሳቻ ስፍራና ጊዜ የሚንቀሳቀሱ እና ሰሌዳ የሌላቸውንም ሞተር ብስክሌቶች መጠቀም አደገኛ ስለሚሆን ነዋሪዎች ጥንቃቄ አንዲያደርጉ አስታውሰዋል።

ተያያዥ ርዕሶች