የዓለም ጤና ድርጅት፡ 'በየቀኑ አንድ ሚሊየን ሰው በአባላዘር በሽታ ይያዛል'

ኮንዶም Image copyright Getty Images

የዓለም ጤና ድርጅት በዓለማችን ላይ በየዕለቱ አንድ ሚሊየን ሰው በግብረ ሥጋ ግንኙነት በሚተላለፉ የአባላዘር በሽታዎች እንደሚያዝ አስታወቀ።

በግብረ ሥጋ ግንኙነት ከሚተላለፉት አራት ኢንፌክሽኖች መካከል፣ ክላይሜዲያ፣ ጨብጥ፣ቂጥኝና የብልት በሽታ (ትራይኮሞኒያሲስ)፣ በአንዱ የሚያዙ 376 ሚሊየን ሰዎች አሉ ይላል ሪፖርቱ።

የዓለም ጤና ድርጅት አባላዘር በሽታዎችን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ፍሬ አለማፍራቱን በመጥቀስ የአሁኑ መረጃ የማንቂያ ደወል ይሆናል ብሏል።

ለወሲብ ትክክለኛው ዕድሜ የቱ ነው?

የወሲብ ቪዲዮ ህይወቷን ያሳጣት ወጣት

የዘርፉ ባለሙያዎች ደግሞ መድሃኒትን የሚቋቋም የአባላዘር በሽታ መከሰት ይበልጥ አሳስቧቸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት አራቱን በግብረ ሥጋ የሚተላለፉ በሽታዎች በየጊዜው ያሉበትን ደረጃ ይፈትሻል።

በየሃገራቱ በበሽታው ላይ የሚደረጉ ምርምሮችንና የሚታተሙ ጥናታዊ ጽሑፎችን ይመረምራል።

ድርጅቱ በ2012 ካደረገው ፍተሻ በኋላ ያለውን ሲመዝን ምንም የበሽታው ሥርጭት የመቀነስ አዝማሚያ አለመታየቱን ይፋ አድርጓል።

ከ25 ሰዎች አንዱ ከእነዚህ አራት አባላዘር በሽታዎች መካከል በአንዱ፣ ከአንድ በላይ በሆነ ተያያዥ ኢንፌክሽን ይያዛል ሲል ይፋ አድርጓል።

በ2016 ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 በሆኑ ሰዎች ላይ በተሰበሰበ መረጃ

  • 156 ሚሊየን አዲስ ታማሚዎች በብልት በሽታ (ትራይኮሞኒያሲስ) ተይዘዋል።
  • 127 ሚሊየን አዲስ ታማሚዎች በክላይሜዲያ ተይዘዋል።
  • 87 ሚሊየን አዲስ ታማሚዎች በጨብጥ ተይዘዋል።
  • 6.3 ሚሊየን አዲስ ታማሚዎች ቂጥኝ ተገኝቶባቸዋል።

የብልት በሽታ (ትራይኮሞኒያሲስ) በወሲብ ወቅት በጥገኛ ተዋህሲያን የሚተላለፍ ሲሆን ክላይሜዲያ፣ ጨብጥና ቂጥኝ በባክቴሪያ ኢንፌክሽን የሚተላለፉ ናቸው።

Image copyright Getty Images

ትልቅ ቀውስን እየተጋፈጥን ይሆን?

በግብረ ሥጋ የሚተላለፉ የአባላዘር በሽታዎች ሽንት በሚሸናበት ወቅት ማቃጠል፣ ፈሳሽ መኖር፣ በወር አበባ መካከል መድማት ምልክቶቻቸው ናቸው። ቢሆንም እንኳን በርካቶቹ በሽታዎች ምልክቶች የላቸውም።

የእነዚህ በሽታዎች የተባባሱ ጤና መታወኮች የዳሌ አጥንት አካባቢ የሚኖር መቆጥቆጥ፣ ክላይሜዲያና ጨብጥ ደግሞ ሴቶችን ለመካንነት ሊዳርጓቸው ይችላሉ።

በቂጥኝ የተያዘ ሰው በፍጥነት ሕክምና ካላገኘ ከልብና ከነርቭ ሕመም ጋር ተያያዥ ለሆኑ የጤና ችግሮች ሊጋልጥ ይችላል።

አንዲት ሴት ነፍሰጡር እያለች በቂጥኝ ከተያዘች ፅንሱ ሊሞት አልያም ያለ ጊዜው ቀድሞ ሊወለድ፣ የሕፃኑ ክብደት ሊቀንስ፣ የሳንባ ምች፣ ዓይነ ስውርነት እና ለአዕምሮ እድገት ውስንነት ሊያጋልጠው ይችላል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ሰዎች ጥንቃቄ የተሞላበት ወሲብ መፈፀም እንዲሁም ኮንዶም መጠቀም አለባቸው ሲል ይመክራል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ