የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን የእግር ኳስ ተጫዋቹ ኦዚል ሚዜ ሆኑ

ኤርዶጋንና ኦዚል Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋ እና ባለቤታቸው ኤሚኔ ከአዲስ ተጋቢዎቹ ጋር ቆመው

ጀርመናዊው የእግር ኳስ ኮከብን የቱርኩ ፕሬዝዳንት ጣይጵ ረሲፕ ኤርዶጋን ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው፣ ጎንበስ ቀና በማለት ሚዜ ሆነው ሞሸሩውታል።

ባለፈው ዓመት የዓለም ዋንጫ ከመካሄዱ በፊት ቱርካዊው ኦዚል ከፕሬዝዳንቱ ጋር ፎቶ ተነስቶ በመታየቱ የጀርመን መገናኛ ብዙኀን አፍ ማሟሻ ሆኖ ነበር።

የ30 አመቱ የአርሴናል የመሃል ተጫዋች ከቀድሞዋ የቱርክ ሞዴል ጋር በቦሰፎረስ የባህር ዳርቻ በሚገኝ ቅንጡ ሆቴል ነው ትናንት የተሞሸረው።

ጥንዶቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት በ2017 ሲሆን የእነርሱን ፍቅር ዓለም የሰማውና ፀሐይ የሞቀው ግን በ2018 ነበር።

የኦዚል የፍቅር ግንኙነት ሰምሮ በትዳር እንዲታሰር ሲወስኑ ደግሞ ለሚዜነት ያሰቡት ለሀገርም ለዓለምም የገዘፉትን ሰው ነበር። እኚህ ሰው የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ናቸው።

«ሳሸንፍ ጀርመናዊ ስሸነፍ ስደተኛ» ኦዚል

«የኔ ትውልድ ታሪክ እንደሚሠራ እምነት አለኝ» ሎዛ አበራ

ኦዚል 'ሚዜ ሆነው ከጎኔ ይቁሙ' ሲላቸው ይሁንታቸውን የሰጡት ያለማቅማማት ነበር።

ጀርመናዊው የአርሴናል እግር ኳስ ተጫዋች ሜሱት ኦዚል ከቱርኩ ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶዋን ጋር በአካል መገናኘቱ በጀርመን ግርግር ማስነሳቱን ቢያውቅም ባለፈው መጋቢት ወር ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ሚዜ እንዲሆኑት ጥያቄ ማቅረቡን ገልጿል።

የቻንስለር አንጌላ ሜርኬል ዋና ጸሃፊ ሄልግ ብራውን ባለፈው አመት ከፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በተመለከተ ለቢልድ ጋዜጣ ሲናገሩ ኦዚል የመምረጥ መብት ቢኖረውም አሳዛኝ ነገር ግን ፈጥሯል ብለው ነበር።

ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን የታዋቂ ሰዎች ዝግጅት ላይ በተደጋጋሚ ይገኛሉ። በተለይ የምርጫ ዘመቻ ሲኖራቸው ቀዳሚ ምርጫቸው ነው። የኦዚል ሚዜ የሆኑትም ለኢስታንቡል የከንቲባ ምርጫ ሊደረግ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ነው። ምክንያቱም ፓርቲያቸው ኤኬፒ በጠባብ ውጤት ያሸነፈበት ምርጫ ዓለም አቀፍ ውግዘት ስለደረሰበት ተሰርዟል።

ባለፈው አመት ምንድን ነው የሆነው?

ከቱርካዊ እናትና አባቱ ጀርመን ውስጥ የተወለደው ኦዚል ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ በተጫወተበት በ2014ቱ የዓለም ዋንጫን ጀርመን እንድታነሳ ጉልህ ድርሻ አበርክቷል።

ከ2011 ጀምሮም የብሔራዊ ቡድኑ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች በማለትም ለአምስት ተከታታይ አመታት ደጋፊዎቹ መርጠውታል።

እግር ኳስ ተጫዋቹ ወንድወሰን ዮሐንስ እንዴት ተገደለ?

ነገር ግን ባለፈው አመት የሩሲያው አለም ዋንጫ ከመካሄዱ በፊት ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ጋር ፎቶ ተነስቶ በመታየቱ "የዚህ ልጅ ታማኝነት ለየትኛዋ ሃገር ነው" በማለት በጀርመን ትልቅ ውዝግብ አስነስቶ ነበር።

በተለይ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያው ዙር ከአለም ዋንጫው ሲሰናበት ትችቱ በርትቶበት ነበር።

ከዚህ በኋላም ኦዚል ራሱን ከብሔራዊ ቡድኑ ማግለሉን የሚገልጽ ረጅም ሃተታ ጽፎ ተሰናብቷል።

ዛቻና ስም ማጥፋት የተቀላቀለ ኢሜይል ደርሶኛል ያለው ኦዚል ከዓለም ዋንጫው ለመባረራቸውም ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ መቆጠሩ እንዳበሳጨው ተናግሯል።

ትኩረት እየሳበ የመጣው የሴቶች እግር ኳስ የዓለም ዋንጫ

"ስናሸንፍ ጀርመናዊ ፣ ስንሸነፍ ደግሞ ስደተኛ እሆናለሁ" በማለት ምሬቱን የገለጸው ኦዚል ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ስኬታማ ጉዞ ቢኖረውም በደጋፊዎቹ ዘንድ የተሰጠው አስተያየት ግን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር እስከመጨረሻው እንዲለያይ አድርጎታል።