የኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ ወዲያና ወዲህ

የኢትዮጵያ ፊልም ጉዞ

የኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ እድሜው ቢቆጠር ገና የአንድ ወጣት እድሜን እንኳ በቅጡ አይሞላም። በእርግጥ ጉማን በእማኝነት ጠርቶ ለሚሞግት ምላሹ የፊልም ኢንዱስትሪው ያንሰራራበትን 1990ዎቹን ብቻ ማስላታችንን መጥቀስ ነው።

የቴዎድሮስ ተሾመ ቀዝቀቃዛ ወላፈን፣ የዮናስ ብርሃነ መዋ ሔርሜላና ጉዲፈቻ የተሰኙ ፊልሞች በየሲኒማ ቤቶች ሸራ ላይ የነገሱበት ዘመን ነበር፡፡ ሺዎች ተሰልፈው ያዩት፤ የከተማው መነጋገሪያ፤ የመገናኛ ብዙኃን ርዕስ ሆነው ነበር።

በ1990ዎቹ ማንሰራራት የጀመረው የኢትዮጵያ ሲኒማ ነገሬ ብሎ የሚያነሳው አጀንዳ፤ በአብይነት አጋፋሪ ሆነው የሚከውኑት ባለሙያዎች፤ ገንዘባቸውንም ላባቸውንም የሚያፈሱለት ጠቢባን ሁሉም ወጣቶች ናቸው።

የዶክተር ዐብይ አሕመድ ፊልም

የኢትዮጵያ ፊልም በወጣቶች ተደራጅቶ፤ ለወጣቶች የእንጀራ ገመድ መሆን ብቻ አይደለም ለጋነቱን የሚያሳየው የሚመደብለትም በጀት ገና ልጅ ነው።

በከተማው ለዕይታ የበቁ ፊልሞችን የገመገመ አንድ ባለሙያ እንደሚለው በአማካይ አንድ ፊልም ተሰርቶ ለእይታ እስኪበቃ ድረስ ስድስት መቶ ሺህ ብር ገደማ ይፈጃል። እርግጥ ነው እንደ ቁራኛ ያሉ ከአለፍ ገደም እስከ 4 ሚሊየን ብር የወጣባቸው ፊልሞች አይታጡም።

ግን ከአማካይ ወጪው አልፎ መበጀት የቻለ ደፋር ፕሮዲውሰር፣ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቁ ፊልሞችንም የጻፈ ደራሲ፤ ገና የፊልም ኢንዱስትሪው ማህጸን አላፈራም። ቢያፈራም እኔ አለሁ ብሎ ወደፊት አልመጣም።

እንደው ለመሆኑ በዓመት ስንት ፊልሞች ታመርታላችሁ ብለን የጠየቅናቸው የፊልም ባለሙያዎች በትንሹ ሰማኒያ በትልቁ ደግሞ መቶ መልሳቸው ነው።

ይህንን መልስ እንደመጨረሻ ወስደን የአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶችን ካሰስን በሳምንት አንድ ወይንም ሁለት ፊልም የሚያስመርቁ አዳራሾችን እናገኛለን።

በፊልም ኢንዱስትሪው መነቃቃት በርካታ የሕንጻ ባለቤቶች እየተበረታቱ ለመሆኑ እማኝ የሚሆኑ እንቅስቃሴዎችም አሉ። እንደ ጋትስ ኢንተርቴይመንት ለአንድ ፊልም 400 ብር ድረስ የሚስከፍሉ የሲኒማ አዳራሾች እንዳሉ ሁሉ በድምጽ ጥራት በምቾትና በሌሎች ግብአቶች ራሳቸውን ብቁ አድርገው ያሉ ሲኒማ ቤቶች በአዲስ አበባ አራቱም አቅጣጫ ይገኛሉ።

"ኢትዮጵያዊ ታሪኮችን ወደ ዓለም አቀፍ የፊልም መድረክ ማምጣት ፈታኝ ነው" ዘረሰናይ መሐሪ

ፊልም መመለክት የፈለገ ከአስኮ እስከ መገናኛ፣ ከአየር ጤና እስከ አዲሱ ገበያ፣ ከአቃቂ እስከ ስድስት ኪሎ በአቅራቢያው የሲኒማ አዳራሽ ያገኛል።

ቦሌ የመጣ ኤድናሞል፣ ሳርቤት ያቀና አዶት ሲኒማ ይዝናናል። ጉርድ ሾላ ነኝ ያለ ሴንቸሪ ሲኒማ፣ ፒያሳ የመጣ አምፔርና ሲኒማ ኢትዮጵያ ገብቶ ያሻውን ይኮመኩማል።

ይህ እንደ ዋርካ እየሰፋ እና እየገዘፈ የሚሄድ የፊልም ኢንዱስትሪ ብርታትና ድክመቱ ምንድን ነው?

አንድ ወደፊት

የፊልም ኢንዱስትሪው ራሳቸውን ባስተማሩ ወጣት ባለሙያዎች የተገነባ ነው የሚለው የፊልም ፕሮዲውሰሮች ማህበር ሰብሳቢው ቢንያም አለማየሁ ነው። ለእርሱ ብቁ ባለሙያዎች እየተፈጠሩ ናቸው።

ይህ ግን በግለሰብ ደረጃ የሚታይ ለፊልሙ እድገት በተናጠል አስተዋፅኦ የሚያበረክት ጉዳይ ነው። ይህንን የግለሰቦች አቅምና ልክ ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው ቋት ሲወሰድ ክፍተት እናያለን ይላል ቢኒያም።

ለፊልም ባለሙያው ድርብ ድል ደግሞ የፊልም እድገትን ለመለካት አንዱ መንገድ የምርት ብዛቱ ነው። የሚዲያው ቴክኖሎጂ በተሻሻለ ቁጥር ፊልምን በቀላሉ በመስራት ለገበያ ማቅረብ ስላስቻለ የምርት መጠኑ ጨምሯል ይላሉ።

ሌላው ደግሞ እንደ አንድ የጥበብ ሥራ በፌስቲቫል ደረጃ ዓለም ላይ ሄዶ በመወዳደር፣ ሀገሪቱንና ባለሙያውን በመወከል ረገድ ያለው እድል ከታየ ግን አሁንም የኢትዮጵያ ፊልም አንካሳ ነው ይላል ድርብ ድል።

ለሲኒማቶግራፈርና ፕሮዲውሰሩ ታምራት መኮንን ግን የፊልም እድገት ላይ የምስል ጥራቱን አይቶ እድል አለ ብሎ ማውራት እንደማይቻል ይናገራል። ለፊልም ጥራቱ አስተዋጽኦ ያደረገው ቴክኖሎጂው ነው፤ በማለት ከዚህ ይልቅ መነሳት ያለባቸው ሌሎች ነገሮች መሆናቸውን ይዘረዝራል።

“አንቺሆዬ”፡ የኢትዮጵያዊያት ታሪክን መናገር

የፊልም ባለሙያው ሔኖክ አየለ ተሰማ በኢትዮጵያዊያን ተመልካቾችና ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ባህሎችና ታሪኮች እጅጉን ይተማመናል። የሀገር ውስጥ ሥራን የመመልከት ባህሉ ለፊልም ሰሪው ተስፋ ሰጪ ነው በማለትም ሥራው ዝቅ ያለ በሆነ ጊዜ እንኳ ተመልካች ከሲኒማ ቤት አለመራቁ እድል ነው ይላል።

ሌላው የተለያዩ ታሪክ ለመተረክ የሚያስችሉ ባህሎች መኖራቸው ለኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስሪ የተቸሩ ጸጋዎ ናቸው ባይ ነው ሔኖክ።

Image copyright Beniyam

ችግሮቹ ምንድን ናቸው?

አቶ ድርብ ድል ፊልም በቀላሉ ዘው የሚባልበት፣ ትንሽ ሰርቶ ብዙ የሚገኝበት ዘርፍ ነው ብሎ ማሰብ ስህተት መሆኑን ጠቅሶ ባለሙያው ራሱን በየጊዜው የሚያሳድግበት የሙያ ሥነ ምግባሩን የሚያከብርበት ዘርፍ ከሆነ የወደፊት ጉዞው የተሳካ ይሆናል ሲል ይናገራል።

ለኢትዮጵያ ተብሎ ፊልም የሚለካበት የተለየ መሥፈርት ሊዘረጋ አይችልም የሚለው ድርብ ድል፤ የሲኒማ ጥበብ ዓለም አቀፋዊነትን እንደ አስረጅ ያነሳል።

የሲኒማ ጥበብ ለዘመናት የራሱ የሆነ የታሪክ መንገሪያ ቅርጽ ያበጀ፣ የራሱን የተለያዩ ዘውጎች ያዳበረ በመሆኑ የእኛ ፊልሞች መንጠራራት ያለባቸው እነዚያ ዓለም አቀፍ የሆኑ መለኪያዎችን ለማሟላት መሆኑን ያስታውሳሉ።

እነዚህን ዓለም አቀፋዊነት ተቀባይነት ያላቸው የፊልም መንገሪያ መዋቅሮችን በማሟላት ደረጃ ደካማ በመሆናችን ግን ኢትዮጵያዊ ፊልም ሰርተን ከዓለም የዘርፉ ጠቢባን ጎን ለመቆም አቅቶናል ይላሉ።

እርግጥ በቁጥር አነስተኛም ቢሆኑ እዚህም እዚያ የኢትዮጵያዊያንንና የፊልም ባለሙያውን ስም ያስጠሩ ሥራዎች ተሰርተው በአውሮፓና በአሜሪካ ፌስቲቫሎች ላይ ዋንጫ ያመጡ ቢኖሩም ፊልሞቻችን ዓለም አቀፍ አቀራረቦችን፤ በቴክኒክ፣ በምስል፣ በድምጽ፣ በትወና ማሳየት ችለዋል የሚለው መመለስ አለበት ይላሉ።

ይህንን ሀሳባቸውን ሲቋጩም ፊልሞቻችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ አልሰራናቸውም በማለት ነው።

ለፊልም ባለሙያው ሔኖክ ከሚሊኒየም በኋላ የነበሩት አምስትና ስድስ ዓመታት የፊልም ዘርፉ ወርቃማ ዓመታት ናቸው። እነ እቴጌ ቁጥር ሁለት፣ የሎሚ ሽታ፣ ረቡኒን በመጥቀስ ወቅቱ አዳዲስ ነገሮች የተሞከሩበት በቅርጽም በስልትም የተሻሉ ነገሮች የቀረቡበት ነበር ሲል ይገልጸዋል።

እነዚህን ፊልሞች በኢኮኖሚ ስኬት፣ በሥራ ጥራት ያመጡትን መሻሻል አለማድነቅና አለማበረታታት ሌሎች ተመሳሳይና የተሻሻሉ ሥራዎች እንዳናይ አድርጎናል ይላል ሔኖክ።

"በሰው ሃገር አገኘሁ የምለው ነገር ስደተኛ በሚል ስም መጠራትን ብቻ ነው።"

የፊልም ባለሙያው የትምህርት ውስንነት አለበት ያለው ሔኖክ የአቅም ችግር፣ የክህሎት ማጣት በዘርፉ ውስጥ የሚታይና በፍጥነት ሊሞላ የሚገባው ክፍተት ነው ለእርሱ።

በእርግጥ የገንዘብ ተግዳሮትም የፊልም ሥራውን ፈትሮ የያዘ ጉዳይ ነው። የሙያ ሥነ ምግባር ጉዳይም የማይታለፍ ነው ሲልም ያክላል። ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች በአጠቃላይ በሙያ ሥነ ምግባር ላይ ዘርፉ ያለበትን ጉድለት ይጋራሉ። በጀትም ቢሆን በአንድ አንደበት የሚናሩለት ችግር ነው።

ለሲኒማቶግራፈሩ ታምራት ደግሞ ለኢትዮጵያ ፊልም እድገት ዋነኛ እንቅፋቱ ባለቤት ማጣቱ ነው። የኢትዮያ ፊልም ኢንዱስትሪ ማነህ? ወዴት ነህ? ብሎ የሚመራው ጠንካራ ተቋም ዛሬም አላገኘም።

የፖሊሲ አለመኖር፣ መመሪያ ማጣትም ሌላው እንከኖቹ ናቸው። "የፊልሙ ኢንዱስትሪ እንደ አንድ ዘርፍ አልታየም" የሚለው ታምራት ዛሬም ሀገሪቱ እየተገለገለችበት ያለው በ1967 ዓ.ም የወጣ ህግን ነው ሲል ዘርፉ ለገጠመው ፈተና አስተዋጽኦ ያደረጉ ነጥቦችን ያነሳል።

ዘርፉ ጠንካራ ሀሳቦችን ሳይሆኑ ቧልት ብቻ የሚታይበት እየሆነ ነው በማለት የፊልም ጽሑፎች ክፍተትንም ይነቅሳል።

"በካሜራ ቴክኖሎጂ መሻሻል ቢታይም በታሪክ ነገራ ዛሬም ድረስ የጀመርንበት ዘመን ላይ ነው ያለነው" የሚለው አቶ ታምራት ዘርፉ የበርካታ ሙያዎች ጥምረት በመሆኑ የእነዚህ ባለመያዎች በበቂ ብዛትና ብቃት አለማግኘት ፈተና መሆኑን ይናገራል።

በወሲብ ፊልሞች ሱሰኛ የሆኑ ወጣት ሴቶች

ዘርፉ ውድ ነው የሚለው ታምራት ጠንካራ ኢትዮጵያዊ የታሪክ ሀሳብ አምጥቶ፣ በፊልም ለመስራት ዋጋው የማይቀመስ ስለሆነ ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት እንዳያደርጉ አድርቸዋል ይላል።

ሲኒማ ቤቶች የሚያስከፍሉት ክፍያ፣ መንግሥት የሚወስደው ታክስ የፊልም ባለሙያው የሰራበትን ዋጋ እንዳይመልስ አድርጎታል የሚለው አቶ ታምራት ፊልም ሰሪ በመሆኑ የሌሎች መጠቀሚያ ከመሆን ባሻገር የፊልም ባለሙያውን የላቡን ውጤት እንዳያገኝ አድርጎታል ሲል ያክላል።

"በእርግጥ አዳዲስ ነገሮችን ለመሞከር የሚፈልግ ባለሙያ የገበያ ፈተና ይገጥመዋል" የሚለው ሔኖክ በበቂ ሁኔታ በመምህራንና ቁሳቁስ የተሟሉና የተደራጁ የፊልም ትምህርት ቤቶች አለመገኘት ክፍተቶቹ የበለጠ እንዲሰፉ ማድረጉን ይጠቅሳል።

ምን ይደረግ?

የፊልም ኢንዱስትሪው እንዲያድግና፤ በኢኮኖሚው ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የመንግሥትን ድጋፍ ይሻል ያሉት ሔኖክና ታምራት ናቸው።

ከእነርሱ የተለየ ሀሳብ ያለው ድርብ ድል ደግሞ መጀመሪያ ባለሙያው ራሱን መመዘንና ያሉበትን ድክመቶች ማሻሻል አለበት ይላል። ባለሙያዎቹ ፊልሙ የሃገሪቱን ባህል በማስተዋወቅ ረገድ ለበርካቶች የሥራ እድል በመፍጠር በኩል በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ቢስማሙም መደረግ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ግን የየራሳቸውን ሀሳብ ያዋጣሉ።

ታምራት መንግሥት የፊልም ኮሚሽን አቋቁሞ ሀገሪቱን የሚያስተዋውቁ ሥራዎችን ማበረታታትና የፊልም ወርክሾፖችንና ትምህርት ቤቶችን መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

መንግሥት ይንን ዘርፍ ይፈልገዋል የሚለው ታምራት ለሥራ እድል ፈጠራ፣ የሀገሪቱን ባህል ለሌሎች ለማስተዋወቅ፣ የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት መንግሥት ሥራዬ ብሎ መስራት አለበት ሲል ሀሳቡን ያጠናክራል።

ለዚህ ደግሞ የደቡብ አፍሪካንና የናይጄሪያን ልምድ ማየት በቂ ነው ባይ ነው።

የፊልም ቁሳቁስ ላይ የሚጣሉ ቀረጦች ላይ ማስተካከያ ቢደረግ የሀገር ውስጥ ፊልም ሰሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ባለሙያዎችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሰሩ በማበረታታት የውጪ ምንዛሪ ያስገኛል፤ የሚለው ታምራት መገንባት የምንፈልገውን ነገር ሁሉ አንደ ሀገር መገንባት የምንችለው ማንቀሳቀስ የምንፈልገውን የምናንቀሳቅሰው ዘርፉ በተገቢው መንገድ ሲደገፍ መሆኑን አጽንኦት ይሰጠዋል።

ድርብ ድል ደግሞ "በፈጠራና በቴክኒክ እውቀት ባለሙያው ራሱን ብቁ ማድረግ አለበት" ይላል። አንድ የፊልም ባለሙያ መናገር የሚፈልገውን ታሪክ፣ ማሳየት የሚፈልገውን ጉዳይ በብስለትና በጥበብ ለማቅረብ ከጽሁፍ ጀምሮ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ የላቀ ሥራ ለማቅረብ ሲጥር አይስተዋልም የሚለው ድርብ ድል "ፊልም መስራትን እንደ ቀላል የመውሰድ አዝማሚያ ስላለ ፊልሞቻችን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ ሳንችል ቀርተናል" ይላል።

የእኛን ፊልም ከሌላው ዓለም ነጥሎ ማየት ተገቢ አይደለም የሚለው ድርብ ድል ፊልም ሰሪው የራሱን አቅም ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ አለመስራቱ ክፍተቱን እንዳይደፍን ማድረጉን ይጠቅሳል።

ለፊልም ፕሮዲውሰሮች ማህበር አመራሩ ቢኒያም የፊልሙን ዘርፍ የሚመራው ባህልና ቱሪዝም ፖሊሲ ካወጣ አንድ ዓመት ከሰባት ወር ቢሆነውም በተግባር ላይ ለማዋል ግን ፈጣን እንቅስቃሴ እያደረገ አለመሆኑ ሊሻሻል የሚገባው ጉዳይ ነው።

"የናንዬ ሕይወት" የአይዳ ዕደማርያም ምስል ከሳች መፀሐፍ

ፖሊሲው ይላል ቢኒያም "ያሉብንን የትምህርት፣ የመሰረተ ልማትና የስርጭት ችግሮችን ይፈታል፤ የስርጭት ችግራችን ብዙ ነው" የሚለው ቢኒያም አንድ ፊልም ለኢንተርኔት፣ ለቴሌቪዥን፣ ለሲኒማ ቤቶች ደጋግሞ የሚሸጥ በመሆኑ ፖሊሲው ወደ ሥራ ቢገባ ያየናቸውን የስርጭት ችግር እንደሚፈታ ያምናል።

አክሎም "ዛሬም እንደ ቅንጦት እቃ ውስኪና ሲጋራ ተደራራቢ ታክስ እንከፍላለን ይህ መስተካከል አለበት" ይላል። መንግሥት የሚፈታቸው ችግሮች እንዳሉ ሆነው የፕሮዲውሰር ማህበሩ በራሱ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታትም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ቢኒያም ይናገራ።

ይህም ከዚህ በፊት ፊልሞች የእይታ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ይሰረቁ እንደነበር በማስታወስ ያንን ለማስቀረት በሁሉም ሲኒማ ቤቶች አዲስ እስከ 4ኬ የሚያጫውት ኢንክሪፕቲቭ ቪዲዮ ዲስፕሌይ ማስገጠማቸውንና የፊልሞችን ደህንትና ጥራት ማስጠበቃቸውን ይገልጻል።

ሌላው ቢኒያም የጠቀሰው ፊልሞቹ የውጭ ምዛሬ እንዲያመጡ በኦንላይን መሸጥ እንዲያስችላቸው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የዲያስፖራ አካውንት ለመክፈት እየሰሩ መሆኑን ነው።

ሔኖክ መንግሥትና የፊልም ሰሪው የሚግባቡበት ፖሊሲ ቀርጸው ማስጸደቃቸውን በማስታወስ ፖሊሲው በቶሎ ሥራ ላይ ይዋል በሚለው የቢኒያም ሀሳብ ይስማማል። እንደፊልም ባለሙያ ግን የግል ብቃትን ማሳደግ፣ የዘርፉን እድገት ለማሻሻል በሚሰሩ ማህበራት ላይ መሳተፍ አስፈላጊ መሆኑንም ይጠቅሳል።

በአሁኑ ጊዜ በርከት ያሉ የፊልም ትምህርት ቤቶች አለመኖራቸውን በማንሳትወደፊት የሚከፈቱት በጥራት ማስተማር እንዲጀመሩ ለማድረግ ሥራዎች ከአሁኑ መሰራት እንዳለባቸው ያስታውሳል።

ጥሩ የተሰሩ ፊልሞችን ማበረታታት ተገቢ ነው የሚለው ሔኖክ ምሳሌ ስለሚሆኑ ሥራዎች አብዝቶ ማውራት ችግር ያለባቸውን ፊልሞች ያክማል ብሎ እንደሚምን በመግለጽ በዘርፉ ገንቢ አስተያየት መለዋወጥ ሚዳብርበት መድረክ እንዲመቻች ያለውን ፍላጎት ይገልጻል።

አክሎም በአፍሪካ ውስጥም ሆነ ከአፍሪካ ውጭ ፊልም ሰሪው በትብብር ከሌሎች ጋር ለመስራት ክፍት መሆን እንደሚያስፈልገው ጠቅሶ ይህን እድል ፊልም ሰሪውም አጥብቆ መፈለግ እንዳለበት ይመክራል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
በማንተጋፍቶት ስለሺ ተፅፎ የተሰናዳው ግርታ ፊልም በቅርቡ በቤልጂየም በተዘጋጀ የአፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል ላይ አሸናፊ ሆኗል።

ሌሎች ኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለፊልም

የዛሬ አርባ ዓመት በሚሼል ፓፓ ታኪስ የተሰራው ባለቀለም ፊልም ጉማ ይሰኛል። ጉማ ስያሜውን ብቻ ሳይሆን ከኦሮምኛ ቋንቋ የወሰደው በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ ባለው የግጭት አፈታት ባህል ላይ በማጠንጠን የተሰራ ዘጋቢ ፊልም እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ፊልም በአማርኛ ቋንቋ የተሰሩ ፊልሞችን በሳምንት ሁለት ወይንም ሦስት ሲያስመርቅ በዓመት በአማካይ ከ 80 በላይ ሲያመርት በሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለመስራት ለምን ወኔ ከዳው?

ባለሙያዎቹ መልስ አላቸው።

ሁሉም ግን መልሳቸውን የሚጀምሩት ኢትዮጵያ በባህል፣ በታሪክ፣ በቋንቋ ብዝሃነት የታደለች መሆኗን በመጥቀስ ነው። ነገር ግን ይላል ታምራት ፊልም ቢዝነስ መሆኑ መረሳት የለበትም።

በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ፊልም ሰርቶ ለገበያ ለማቅረብ ገበያ አለ ወይ? የሚለው መታየት አለበት ሲል ምክንያቱን ያስቀምጣል።

ሌላው ዘርፉን የሚያውቅ፣ ከባህሉ የወጣ ብቁ ባለሙያ አለመኖር ችግር ነው። መንግሥት በተለያዩ ቋንቋዎች ለሚሰሩ ፊልሞችን የሚሰጠው ማበረታቻ ምን ያህል ነው? የሚለው መታየት አለበት ይላሉ ባለሙያዎቹ።

አቶ ድርብ ድል በበኩሉ "በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አለመስራታችን አቢይ ምክንያቱ ለፊልም ትምህርት፣ ለሙያው ያለን ተጋልጦ ማነስ አስተዋጽኦ አድርጓል" ይላል።

ፊልም ለመስራት ሀሳብና ይዘት ይዞ የሚመጣው ሰው ዳራ ወሳኝ ነው በማለት፤ ከተለያዩ አካባቢዎች ፊልም ሰሪዎች እንዳይመጡ የአቅም እና የሙያ ክህሎት ክፍተት መኖሩ ላይ ይስማማል። ሌላው ደግሞ የፊልም ሰሪው ምርጫ ወሳኝ ነው ይላል።

ለሔኖክ በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለመስራት የበጀት ውስንነት እንደልብ እንዳይዘረጉ በማድረግ ምርጫቸውን በመገደብ አሉታዊ ሚና መጫወቱን ይጠቅሳል።

አንድ ፊልም ለመስራት ፍላጎት ቢኖር እንኳ የገንዘብ አቅም ውሱን መሆን በቀላሉ በቅርብ አካባቢ ያሉታሪኮች ላይ ለማተኮር ፊልም ሰሪው ይገደዳል ሲል ያሰስረዳል።

በጣም ጥቂት ሰዎች የሚጠየቀውን በጀት መድበው ፊልሞችን ቢሰሩ እንኳ የገበያ ውስንነት ካለ ፊልሙ የወጣበትን ወጪ ስለማይመልስ የፊልም ፕሮዲውሰሮች በትንሽ ዋጋ ሰርተው ማትረፍ ወደ ሚያስችላቸው ፊልሞች ያዘነብላሉ ይላል።

የፕሮዲውሰሮች ማህበር አመራሩ ቢኒያም በቀጣይ ዓመት በመላ ሀገሪቱ አዳዲስ ደረጃቸውን የጠበቁ 150 ሲኒማ ቤቶች ወደ ሥራ እንደሚገቡ አስታውሶ በየክልሉ ያሉ ፊልም አፍቃሪያንን ለመድረስ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በአማርኛ የሚሰሩ ፊልሞቸን ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተርጉሞ ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑን ተናግሯል።

ተያያዥ ርዕሶች