አፍሪካ ቴክኖሎጂ በፍጥነት ሊጣጣሙ የቻሉ አይመስሉም፤ ሌላ አማራጭ ግን የላቸውም

ቴክኖሎጂ Image copyright Getty Images

ያልበለፀገ መሠረተ-ልማት የአህጉረ አፍሪካ ዕድገት ማነቆ መሆኑ አያጠራጥርም። ሎጅስቲክስ [ለጊዜው አቻ የአማርኛ ፍቺ ባናገኝለትም] ደግሞ ለዚህ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ሲነገር እነሰማለን።

አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች ከምግብ እስከ አልባሳት በርካታ ቁሳቁሶችን ያመርታሉ፤ ወደ ገበያ ወስዶ መሸጥ ግን እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም።

ናይት ፍራንክ የተሰኘ አንድ አጥኚ እና አማካሪ ድርጅት የትራንስፖርት ዋጋ የአንድን ሸቀጥ ከ50 እስከ 75 በመቶ ያለውን ድርሻ ሊወስድ ይችላል ሲል ይተነትናል።

አምስቱ የአፍሪካ ቴክኖሎጂ ጎዳናዎች በ2018

ናይጄሪያ ውስጥ የሚገኝ ኮቦ360 የተሰኘ ድርጅት ግን አንድ መላ አመጣ፤ ድርጀቱ የፈጠረው የሞባይል መተግበሪያ [አፕ] ከአምራች እስከ ጫኝና አውራጅ ድረስ ያሉትን በአንድ ገመድ የሚያስተሳስር ነው።

እርስዎ አምራች ቢሆኑ ከምርትዎ ጋር እስከ ወደብ መንከራተት አይጠበቅብዎትም፤ ስልክ እየደወሉ መጨነቅም ቀርቷል። እኒህን ተግባራት የሚከውነው እንግዲህ ይህ የሦስት ዓመት ጨቅላ ድርጅት ነው።

ናይጄሪያ ውስጥ ያሉ ገበሬዎች ከእርሻቸው ከሚልኩት ምርት 50 በመቶው እንኳ በሰላም ነጋዴዎች ደጃፍ ከደረሰ አምላካቸውን ያመሰግናሉ። ታድያ ይህን የተረዳው መተግበሪያው የምርቶችን ደህንነት የሚያስጠብቅ መስመርም ዘርግቷል።

የሴኔጋሏ ከተማ ዳካር ነዋሪዎች ወደ ገበያ መውጣት ቀንሰዋል። ኦንላይን መሸመት እየተቻለ ደግሞ የምን ጉልት ለጉልት መንከራተት ነው ያሉ ይመስላሉ። የኬንያዋ መዲና ናይሮቢም ብትሆን ከራስ ምታት መድሃኒት እስከ ዘይት ድረስ 'ኦንላይን' ሸምተው ቤት ድረስ ማስላክ ይችላሉ። ለዚያውም በግማሽ ሰዓት። ዕድሜ ጁሚያን [ምንም እንኳ ድርጅቱ አፍሪካዊ አይደለም እየተባለ ቢታማም] ለመሳሰሉ ድርጅቶች።

የሰዎችን ማንነት የሚለየው ቴክኖሎጂ እያከራከረ ነው

'ክዊኬሪ' የተሰኘ የሴኔጋል ኩባንያ እርስዎ ከየትኛውም ዓለም የገዙትን ዕቃ ቤትዎ ድረስ መጥቶ፤ አንኳኩቶ ያስረክብዎታል። የድርጅቱ ዋነኛ ተጠቃሚዎች ደግሞ ወጣቶች ናቸው።

ለምሳሌ ያህል ኬንያንና ሴኔጋል አነሳን እንጂ በርካታ ሃገራት ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ከጊዜ ጊዜ የዜጎቻቸውን ሕይወት ለማቅለል እየሞከሩ ነው። በቂ ነው ማለት ግን አይደለም። ተጀመረ እንጂ ገና ብዙ ርቀት መጓዝን ይጠይቃል ይላሉ በዘርፉ 'ጥርስ የነቀሉ' ባለሙያዎች።

ለምሳሌ ለመሰል ቴክኖሎጂዎች የሚሰጠው ብድር ወለድ ከ12-20 በመቶ ያክል ነው። ይህ ደግሞ ድርጅቶቹ አትራፊ እንዳይሆኑ ማነቆ ሆኗል፤ ይላል የአፍሪካ ልማት ባንክ ዘገባ።

የኢንተርኔት ገበያ በሶማሊያ

ናይጄሪያ እኛ በተለምዶ ባጃጅ የምንላቸው ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ኬኬ የተሰኘ ስያሜ አላቸው። እንደተመረቀ ሥራ ብርቁ የሆነው ሳሙኤል ኦጉንዳሬ 'ኬኬ ጋይ' የተሰኘ ድርጅት በማቋቋም አሽከርካሪዎች በድንቡ ለበሰው ደንበኛን እንደንጉስ እየተንከባከቡ እንዲያስተናግዱ ማድረግ ያዘ።

«ሰዎች እኔን ተመልክተው ከትንሽ ነገር ተነስተው ስኬታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ እንዲያምኑ እፈልጋለሁ» ይላል።

ኢትዮጵያም ውስጥ እንደሌሎቹ ሃገራት አርኪ ባይሆንም መሰል ፈጠራዎችን ማየታችን አልቀረም። የበይነ-መረብ ጠንካራ አለመሆን ነገሮችን ሱሪ በአንገት ቢያደርጋቸውም።

ኢትዮጵያም ትሁን አፍሪካ ይላሉ ባለሙያዎች. . . ኢትዮጵያም ትሁን አፍሪቃ ከቴክኖሎጂ ውጭ አማራጭ ያላቸው አይመስልም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ