የሴቶች ዓለም ዋንጫ፡ ሴት እግር ኳሰኞች ስንት ይከፈላቸዋል? ዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ ሃገራትስ?

የ2015ቱ የዓለም ዋንጫ Image copyright Getty Images

የሴቶች እግር ኳስ ከጊዜ ጊዜ እያደገ የመጣ ይመስላል፤ ትኩረት መሳብም ጀምሯል። የዘንድሮውን የዓለም የሴቶች ዓለም ዋንጫ ጨዋታ 1 ቢሊዮን ተመልካቾች ይታደሙታል የሚል ግምት አለ።

ወደ ክፍያው ስንመጣስ?

የሉሲዎቹ አምበል የሆነችው ሎዛ አበራ ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር የሴቶች ክፍያ እዚህ ግባ የማይባል ነው ትላለች።

በዓለም አቀፍ ደረጃስ? የባለፈው ዓለም ዋንጫ አሸናፊ የአሜሪካ አጥዊ የሆነችው ሆፕ ሶሎ የሴቶች እና የወንዶች ክፍያ ልዩነት ፊፋ ውስጥ ያለውን 'የወንድ የበላይነት' ያሳያል ስትል ትወቅሳለች።

እስቲ ክፍያውን በቁጥር ከፋፍለን እንመልከተው።

እግር ኳስ ተጫዋቹ ወንድወሰን ዮሐንስ እንዴት ተገደለ?

ፈረንሳይ እየተካሄደ ባለው የዘንድሮው የሴቶች የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ላይ አሸናፊ የምትሆነው ብሔራዊ ቡድን 4 ሚሊዮን ዶላር [115 ሚሊዮን ብር ገደማ] ታገኛለች። ከባለፈው ዓለም ዋንጫ ክፍያ እጥፍ ማለት ነው።

እያንዳንዳቸው ተሳታፊ ቡድኖች ደግሞ ከ750 ሺህ ዶላር [22 ሚሊዮን ብር ገደማ] ጀምሮ በነብስ ወከፍ ይቀበላሉ። ከሽልማት ወጪው በተጨማሪ ለዝግጅት በሚል እያንዳንዷ ቡድን 800 ሺህ ዶላር ከፊፋ ትቀበላለች።

በጠቅላላው ፊፋ ለዘንድሮው ዓለም ዋንጫ 30 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል።

ወደ ወንዶቹ ስንመጣ. . .

ሩስያ አዘጋጅታ ፈረንሳይ በወሰደችው የ2018ቱ የወንዶች ዓለም ዋንጫ ፊፋ ለሽልማት ብሎ ያዘጋጀው ጠቅላላ ገንዘብ 400 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነው፤ ከሴቶቹ ከአስር እጥፍ በላይ ማለት ነው።

ለዝግጅት ተብሎ ለእያንዳንዱ ቡድን በነብስ ወከፍ የተሰጠው ደግሞ 1̋ሚሊዮን ዶላር ነው፤ ከሴቶቹ እጥፍ በላይ ማለት ነው እንግዲህ። አጀብ! የሚያስብል ሆኖ እንዳገኙት እንጠራጠርም።

የወንዶቹ ክፍያ ከሴቶቹ በልጦ የመገኘቱ ጉዳይ ከሚያመጡት ገቢ ጋር መገናኘቱ ነው ብለው የሚከራከሩ አልጠፉም።

ቢሆንም በፊፋ ሕግ መሠረት ከሴቶች እግር ኳስ የሚገኘው ገንዘብ ለሴቶች እግር ኳስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ወጪዎች የሚውል ነው።

ለሃገራት የሚከፈለውን ዶላር ተጫዋቾች ያገኙታል?

ፊፋ ለሃገራት የሚከፍለው ገንዘብ የተጨዋቾች ኪስ ሳይሆን ወደ ፌዴሬሽን ካዝና የሚገባ ነው። የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ድርሻ ቆንጠር አድርጎ ለተጨዋቾች መስጠትና የቀረውን ደግሞ ሌሎች መስኮች ላይ በተን በተን ማድረግ ይሆናል።

ታድያ በፌዴሬሽኖች እና በእግር ኳስ ተጨዋቾች ማሕበር መካከል የሚደረግ ድርድር አለ።

«የኔ ትውልድ ታሪክ እንደሚሠራ እምነት አለኝ» ሎዛ አበራ

የአውስትራሊያ ሴቶች እግር ኳስ ቡድን የትኛውንም ገንዘብ በሽልማት መልክ ሲያገኝ ተጨዋቾች 30 በመቶ እንዲያገኙ ተደራድሯል።

ወደ ክለቦች ስንወርድ ደግሞ የተሻለ ክፍያ የሚያገኙት [ከወንዶች ሲነፃፀር ቁጥሩ እጅግ አናሳ ቢሆንም] በምዕራብ አውሮፓ የሚጫወቱቱ ናቸው።

ገንዘቡ ደግሞ ከ1 ሺህ እስከ 2 ሺህ ዩሮ ይደርሳል፤ ጨዋታ ባለ ቁጥር ደግሞ የላብ መተኪያ የሚሆን ከ50-100 ዩሮ ያገኛሉ። እርግጥ ነው ስም ያላቸው ተጨዋቾች ከዚህ የተሻለ ይከፈላቸዋል።

Image copyright Getty Images

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት ክፍያው ምን ያህል ዝቅ ያለ እንደሆነ መገመት አያዳግትም።

ፊፋ የሴቶች ዓለም የዋንጫ አሸናፊ ሽልማትን ከባለፈው ዓለም ዋንጫ እጥፍ ማድረጉ አንድ እርምጃ ወደፊት ነው የሚሉ ባይጠፉም 'አሁንም ትንሽ ነው' ብለው የሚከራከሩ አልጠፉም።

በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ፊፋ የሴቶች እግር ኳስ ላይ ከ400-500 ሚሊዮን ዶላር አፈሳለሁ ይላል።

ድምፃችን ይሰማ!

የአሜሪካ ሴቶች እግር ኳስ ቡድን የሃገሪቱን እግር ኳስ ማሕበር እኩል ክፍያን እውን አላደረገም በሚል ከሶታል።

የአውስትራሊያ እግር ኳስ ተጫዋቾች ማሕበር ፊፋ የሴቶች እና የወንዶች የዓለም ዋንጫ ሽልማት እኩል መሆን አለበት ሲል እየሞገተ ነው።

2016 ላይ የአፍሪካ ዋንጫን የበላችው የናይጄሪያ ሴቶች ቡድን በክፍያ ጉዳይ ከፌዴሬሽን ጋር በነረው እሰጥ-አገባ አድማ አድርጋ ነበር።

የኒው ዚላንድ ወንዶች እና ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አባላት ከ2018 ጀምሮ ማንኛውም ዓይነት ክፍያ እኩል እንዲያገኙ የሚያደርግ ውል ደርሰዋል፤ በኖርዌይም እንዲሁ።

ምንም እንኳ ልዩነቱ አሁንም የሰማይና ምድርን ያክል [የሎዛ አበራን አገላለፅ ለመጠቀም] ቢሆንም ከጊዜ ጊዜ ግን ለውጥ መምጣቱ አይካድም።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የሴቶች እግር ኳስ የዓለም ዋንጫ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ?

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ