በአማራ ክልል በተከሰቱ ግጭቶች 224 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ Image copyright FBC
አጭር የምስል መግለጫ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ምግባሩ ከበደ

በአማራ ክልል የተለያዩ ስፍራዎች ከተከሰቱ ግጭቶችን ጋር በተያያዘ 224 ሰዎች በቁጥጥር መዋላቸውን የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታወቀ።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ምግባሩ ከበደ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ ትልቁ የፖለቲካም የመልካም አስተዳደር ሥራ ነው ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ግጭት በተፈጸመባቸው 3 አካባቢዎች ጥፋት የፈጸሙ ሰዎችን ለሕግ ለማቅረብ የምርመራ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል። አቃቤ ሕጉ በማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ኦሮሞ ማህበረሰብ አስተዳደር እና ከቤኔሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ ቦታዎች የምርመራ ሥራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስ፣ የፌደራል እና የክልሉ አቃቤ ሕግ እንዲሁም የዞን ፖሊስ የተካተቱበት የምርመራ ቡድን መመሥረቱንም አቃቤ ሕጉ ተናግረዋል። በማዕከላዊ እና ምእራብ ጎንደር ዞኖች 150 ሰዎች ጉዳያቸው እየተመረመረ በማረሚያ ቤት እንደሚገኙ አቶ ምግባሩ አስታውቀዋል።

ሆኖም ተጠርጣሪዎች ገና በቁጥጥር ሥራ ያልዋሉ ሲሆን ይህም ከነበረው ግጭት ስፋትና ውስብስብነት የተነሳ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ታጣቂዎች አምስት ሰዎች ገደሉ

በካማሼ ዞን ግጭት እጃቸው አለበት የተባሉ በቁጥጥር ስር ዋሉ

በኦሮሞ ማህበረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞን ደግሞ ላለፉት ሶስት ወራት በተሰራው የምርመራ ሥራ ማስረጃ የተገኘባቸው 50 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።

በቤኔሻንጉል ጉሙዝ እና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት 24 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እየተከታተሉ ነው። "የአማራ ክልል በቅርቡ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት እና ሠላም የሰፈነበት ክልል ማድረግ እንደምንችል አምነን እየሠራን ነው የምንገኘው" የሚሉት አቃቤ ሕጉ ምግባሩ ከበደ፤ ህበረተሰቡ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን ሳልፎ በመስጠት ሊተባበር ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።