የኢትዮጵያ ዐይን ባንክ፡ የዐይን ብርሃኑን አጥቶ የተመለሰለት ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የመቀሌ ነዋሪ የሆነው አቡበክር ውሃውረቢ እናቱና አባቱ በፍቺ በመለያየታቸው ዕድገቱ ከእናቱ ጋር ነው። ለቤተሰቡ የመጀመሪያ የሆነው አቡበክር የዐይን ህመሙ የጀመረው ገና የሁለት ዓመት ከሰባት ወር ህፃን ሳለ ነበር።
ያጋጠመው የአለርጂ ህመም ዐይኑን በተደጋጋሚ እሸኝ እሸኝ ይለው ነበር። እርሱም ህመሙ እያስገደደው በተደጋጋሚ ዐይኑን ያሸዋል። ከትምህርት ቤትም ሆነ ከጨዋታ ሲመጣ አይኑ ተጨናብሶና ደም ለብሶ መምጣቱ የተለመደ ሆነ።
ህመሙ የእርሱ ብቻ ሳይሆን የእናቱም የዘወትር ጭንቀት ነበር። "በእኔ ዐይን ምክንያት ዐይኗ እምባ እንዳዘለ፤ እንዳለቀሰች ነው፤ አንተን ከሚያምህ እኔን ለምን አያመኝም? ትለኝ ነበር" ይላል የእናቱን መጠን ያለፈ ጭንቀት ሲያስረዳ።
"በዚህ ዐይን ምክንያት እናቴ ሁል ጊዜ ታለቅስ ነበር" የሚለው አቡበክር እርሱን ለማሳከም ያልጎበኘችው የጤና ተቋም እንዳልነበርም ይናገራል።
ይሁን እንጂ የተወሰነ የህመም ማስታገሻና 'ዕድሜህ ሲጨምር ይተውሃል' ከሚል ምክር በስተቀር የተሰጠው ዘላቂ መፍትሄ አልነበረም። ትምህርት ቤት በሄደ ቁጥር ከነጭ ሰሌዳና ከብርሃን ጋር እንደተሟገቱ ነው። የልጅነት ዐይኑ ብርሃንን ጠላ።
ማስታገሻ መድሃኒት እየተሰጠው፤ እየተሻለው፤ እንደገና እያገረሸበት ትምህርቱን ለመከታታል አዳጋች ሆነበት። ቢሆንም ግን ትምህርቱን እያቋረጠና እንደገና እየቀጠለ አስራ ሁለተኛ ክፍል ደረሰ።
የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ብዥ ማለት የጀመረው ዐይኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ግን የዐይን ዕይታው ጨርሶውኑ ስለቀነሰ ትምህርቱን መማር አልቻለም። ቀስ በቀስም በተለይ የአንደኛው ዐይኑ ዕይታ ሙሉ በሙሉ ጠፋ።
"ከዕይታ በላይ ፈጣሪ የሰጠን ፀጋ የለም፤ ማየት መቻል ትልቅ ነገር መሆኑን ነው የተረዳሁት" ይላል -የዐይኑን ብርሃን ያጣበትን አጋጣሚ ሲያስታውስ።
"ማታ አሞኝ ሳሸው... ሳሸው ቆይቼ ተኛሁ፤ ከዚያም ጠዋት ስነሳ ... አንዱ ዐይኔ አያይም፤ በቃ አበድኩ፤ ጮህኩ፤ ቤተሰቦቼ ተደናገጡ፤ ፍርሃት ፍርሃት አለኝ፤ አንቀጠቀጠኝ" ሲል ሁሉም ነገር እንደጨለመበትና ሁኔታውም በቃላት እንደማይገለፅ ይናገራል።
በዚህ ጊዜ የተደናገጡት ቤተሰቦቹ ደቂቃም ሳያባክኑ ወደ ሆስፒታል ይዘውት ሄዱ፤ ይሁን እንጂ በከተማው ላለው ሐኪም ቤት ከአቅም በላይ ነበር። ለሕክምናው ወደ ውጭ አገር መሄድ እንዳለበት ታዘዘ። ይህ ትዕዛዝ አቅም ለሌላቸው ቤተሰቦቹ ዱብ ዕዳ ነበር።
ጊዜም ሳይወስዱ በነጋታው አዲስ አበባ ወደሚገኘው ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ለተሻለ ሕክምና ወሰዱት። የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ እንደሚደረግለትም የሰማው እዚሁ ነበር። አብዝቶ የሚሰማው ስለ ኩላሊት ንቅለ ተከላ ስለነበር ፅንሰ ሃሳቡ ራሱ እንግዳ ሆነበት።
የዐይን ብሌኑ ሕይወታቸው ካለፉ ሰዎች የተለገሰ እንደሆነ ሲያስበው ደግሞ በጣም ተደናገጠ። ሕክምናው እውነት አልመሰለውም።
'ታዲያ ከፈራህ እምቢ ለምን አላልክም?' አልነው። "ብርሃን አጥቼ እንዴት አልፈልግም እላለሁ፤ ያለውን አማራጭ መሞከር ነው እንጂ" ሲል ነበር ሳያወላዳ ምላሹን የሰጠን። ሙሉ በሙሉ ብርሃን ያጣው ዐይኑ የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላው ተደረገለት።
ከቀዶ ሕክምናው እንደወጣ ህመም ቢሰማውም እየቆየ ግን ዐይኑ በትንሹም ቢሆን ማየት ጀመረ። ለመጀመሪያ ጊዜም ያየው ቀዶ ሕክምናውን ያደረገችለትን ሐኪም እንደሆነ ያስታውሳል።
ከሰው ያውም ሕይወቱ ካለፈ ሰው በተለገሰ የዐይን ብሌን ማየት መቻሉ በጣም አስገርሞታል። የማያውቃቸውን የለጋሽ ቤተሰቦች "የለጋሹ ቤተሰቦች ባላውቃቸውም ለሰዎች የሚያስቡ፣ ጥሩና የዋህ ሰዎች እንደሆኑ ነው የማስበው" ሲል ያመሰግናቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, BSIP
በተለገሰ የዐይን ብሌን ማየት ምን ስሜት ይሰጣል?
አቡበክር አንዳንዴ ንቅለ-ተከላው በተደረገበት ዐይኑ ሲመለከት በእኔ ነው ወይስ በለጋሹ ሰው ዐይን የማየው? የሚለው የሁል ጊዜም ሃሳቡ ነው። ነገር ግን ከራሱ ጋር በሚያደርገው ንግግር ለራሱ መልስ ይሰጣል።
"በለጋሹ ዐይን እኔ የማየውን ነው የማየው" ይላል።
አንዳንዴ ጓደኞቹ "ለጋሹ ያየው የነበረውን እኮ ነው የምታየው" እያሉ እንደሚወርፉትና 'ሙድ' እንደሚይዙበት አልሸሸገንም። ኧረ እንዲያውም በሴት ወይስ በወንድ የዐይን ብሌን ነው የምታየው እያሉ እንደሚጠይቁትም ሳቅ ባልተለየው አንደበቱ አጫውቶናል።
"የዐይን ብሌኑን የለገሱኝን ቤተሰቦች እጅግ አመሰግናቸዋለሁ፤ ባላውቃቸውም አላህ ጥሩ ነገር እንዲሰጣቸው እመኝላቸዋለሁ" ሲል የዐይን ብርሃኑን የመለሱለትን ለጋሾች አመስግኖ አይጠግብም። አቡበክር አሁን የአንድ ዐይኑ ብርሃን ሙሉ ለሙሉ የተመለሰለት ሲሆን ለሌላኛው ዐይኑ ሕክምና ለማድረግም እየተጠባበቀ ይገኛል።
ትምህርቱን ለመቀጠልና እንደርሱ የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት ዶክተር መሆን እንደሚፈልግም ነግሮናል።
የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ
በተለያየ ምክንያት የዐይን ብሌን ላይ የሚከሰት ጠባሳ ለዐይነ ስውርነት ሊዳርግ ይችላል። በተፈጥሮ፣ በአደጋ፣ በኩፍኝ በሽታ ወይም በተለያዩ የዐይን ህመሞች ሊከሰት ይችላል። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊድን የሚችል ዐይነ ስውርነት ይባላል።
የዐይን ብሌን ጠባሳ መሆኑ በሐኪም ከተረጋገጠ በኋላ በንፁህ የዐይን ብሌን የመቀየር ሂደት የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ እንደሚባል የኢትዮጵያ የዐይን ባንክ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ለምለም አየለ ያስረዳሉ።
"አንድ ፍሬም ያለው መስታዎት በድንጋይ ተመቶ ቢሰነጣጠቅ ከውስጥ ወደ ውጭም ሆነ ከውጭ ወደ ውስጥ አያሳይም፤ በመሆኑም ፍሬሙን ቀርፆ አውጥቶ በሌላ መተካት ነው። የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላም እንደዚያው ነው" ሲሉ ምሳሌ ይመዛሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት የጣታችንን ጥፍር ልጦ እንደማንሳት ያህል የዐይን ብሌንን ልጦ ማንሳት ይቻላል። በመሆኑም በዚህ ሂደት ከለጋሹ የተነሳውን የዐይን ብሌን ወደ ታካሚውም በተመሳሳይ መልኩ ማስተላለፍ ይቻላል።
ሕክምናውን ለማግኘት የእድሜ ገደብ የለውም የሚሉት ወ/ሮ ለምለም ለሕፃናት ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ስለሚያስልግ ትንሽ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ይህም እንደ ሐኪሙ ውሳኔ ይወሰናል ይላሉ።
የኢትዮጵያ የዐይን ባንክም ሰዎች በሕይወት እያሉ የዐይን ብሌናቸውን ለመስጠት ቃል እንዲገቡ በማድረግ የዐይን ብሌን የማሰባሰብ ሂደት ይሰራል። በዚህም ቃል የተገቡ የዐይን ብሌኖችን ከሟች ቤተሰቦች ጋር በመነጋጋር እንዲነሱ ያደርጋሉ።
አንድ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ከተረጋገጠ በኋላ በስምንት ሰዓታት ጊዜ ውስጥ የዐይን ብሌኑ ተነስቶ በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ወደ ሚገኘው የኢትዮጵያ ዐይን ባንክ ቢሮ ይመጣል።
ከዚያም የደም ናሙና በመውሰድ የዐይን ብሌኑ ጥራት ይረጋገጣል። በባንኩ ውስጥ የዐይን ብሌኑ የሚቀመጠው ለ14 ቀናት ብቻ ነው። ከ14 ቀን በላይ ከቆየ ስለሚበላሽ ጥቅም ላይ አይውልም።
በመሆኑም እነዚህን ሂደቶች ያለፈ የዐይን ብሌን፤ ንቅለ ተከላ በሚካሄድባቸው በአዲስ አበባ ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታልና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፤ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፣ ኲሓ ሆስፒታል፣ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በጠየቁት ወረፋ መሠረት የዐይን ባንኩ ያዘጋጃቸውን የዐይን ብሌኖች ያሠራጫል።
የኢትዮጵያ የዐይን ባንክ ከተመሠረተ 15 ዓመታትን ቢያስቆጥርም እስከ ፈረንጆቹ 2018 መጨረሻ ድረስ የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው 2112 ኢትዮጵያዊያን ብቻ ናቸው።
ከሚለገሱት የዐይን ብሌኖችም 80 በመቶ ያህሉን ብቻ እንደሚጠቀሙ የሚናገሩት ሥራ አስኪያጇ ቀሪው 20 በመቶ በተለያየ ችግር ምክንያት ከጥቅም ውጭ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
እስካሁን ድረስ ወደ 3 ሺህ የተጠጋ የዐይን ብሌን መለገሱንም ወ/ሮ ለምለም አክለዋል።