ኢቦላ ወደ ኡጋንዳ እየተዛመተ ነው

የጤና ባለሙያ የኢቦላ መከላከያ ጭምብል ለብሶ Image copyright Reuters

በኡጋንዳ አንድ የአምስት ዓመት ህፃን በኢቦላ በሽታ መሞቱ ተነገረ።

ይህ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውጪ ኢቦላ ቫይረስ ሲገኝ የመጀመሪያው ነው።

ባለፉት አስር ወራት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ብቻ 2ሺህ ታማሚዎች የተመዘገቡ ሲሆን የበርካቶቹ ጤና በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው ተብሏል።

አሁን በኡጋንዳ በኢቦላ የሞተው ሕፃን ቅዳሜ እለት ከቤተሰቡ ጋር በመሆን ከኮንጎ ወደ ኡጋንዳ በድንብር በኩል የተሻገረ ነው።

እናቱ እና አያቱም በቫይረሱ መያዛቸው ተሰምቷል።

ሴት እግር ኳሰኞች እና ቡድኖች ስንት ይከፈላቸው ይሁን?

በአማራ ክልል በተከሰቱ ግጭቶች 224 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የኡጋንዳ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ሕፃኑ ደም የቀላቀለ ማስመለስና ሌሎች ምልክቶችን እንዳሳየ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር።

በልጁ ደም ውስጥ የኢቦላ ቫይረስ መገኘቱ የታወቀው በኡጋንዳ የቫይረስ ምርመራ ተቋም ውስጥ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ነው።

ወዲያው የዓለም ጤና ድርጅትና የኡጋንዳ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር የአስቸኳይ ጊዜ የሕክምና ቡድን ወደ ስፍራው የላኩ ሲሆን ቡድኑ ሌሎች ሰዎች በቫይረሱ መያዝ አለመያዛቸውን በመለየት አስፈላጊውን ሕክምናና ትምህርት ይሰጣል ብለዋል።

የኡጋንዳ ጤና ሚኒስትር ለመገናኛ ብዙኀን እንደገለፁት የህፃኑ ቤተሰቦችና ሌሎች የኢቦላ ምልክት የሚመስል የታየባቸው ሁለት ሰዎች ክትትል እየተደረገላቸው ነው።

ሚኒስትሯ በቲውተር መልእክታቸው ላይ እንዳስቀመጡት ኡጋንዳ በአሁኑ ሰአት የኢቦላን ወረርሽኝ ለመከላከል በተጠንቀቅ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

አፍሪካ ከቴክኖሎጂ ውጪ ለእድገት ምን አማራጭ አላት?

ኡጋንዳ ከ4500 በላይ ጤና ባለሙያዎችን የኢቦላ መከላከያ ክትባት መስጠቷን የዓለም ጤና ድርጅትና የኡጋንዳ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።

በኮንጎ የደረሰው የኢቦላ ወረርሽኝ በታሪክ ሁለተኛው ነው የተባለ ሲሆን በየሳምንቱ አዳዲስ በሽተኞች በከፍተኛ ቁጥር እየተመዘገቡ ነው ተብሏል።

ከባለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ 1400 ሰዎች በኢቦላ ምክንያት መሞታቸው ታውቋል።

ጉረቤት ሃገሮችም የኢቦላ መዛመት እጅጉን አሳስቧቸዋል። ኢቦላ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወደ ኡጋንዳ መዛመቱ ከተሰማ በኋላ ሩዋንዳ በድንበሮቿ ላይ የኢቦላ በሽታ ቁጥጥርን አጠናክራለች።

ሩዋንዳ በምዕራብ በኩል ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፤ በሰሜን በኩል ደግሞ ከኡጋንዳ ጋር ትዋሰናለች።

የሩዋንዳ የጤና ጥበቃ ሚንስትር ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ''ሩዋንዳ በጎረቤት ሃገራት የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሸኝ አጽንኦት ሰጥታ ትከታተለዋለች'' ብለዋል።

ሩዋንዳ ዜጎቿን የግል ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ እና በኢቦላ ወደተጠቁ ስፍራዎች እንዳይጓዙ አሳስባለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ