ኢትዮቴሌኮም ኢንተርኔት ለምን እንደተቋረጠ መግለፅ እንደማይችል አስታወቀ

ኢትዮ ቴሌኮም Image copyright Elvis

በትናንትናው ዕለት የተቋረጠው ኢንተርኔት ወደ አመሻሹ ላይ ቢመለስም ሌሊት እንዲሁም ጠዋት ላይ ተቋርጦ ነበር። ኢንተርኔት የተቋረጠበትን ምክንያት ለመረዳት ቢቢሲ የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አስፈፃሚ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ጨረር አክሊሉን ጠይቋል። እሳቸውም ኢንተርኔት መቋረጡን አምነው ምክንያቱን ግን ኢትዮ ቴሌኮም መግለፅ እንደማይችል አስረድተዋል።

"ምናልባት ሌላ አካል ምክንያቱን ሊገልፀው ይችል ይሆናል። ይሄ ነው ብለን መግለፅ የምንችለው አይደለም" ብለዋል

በኢትዮጵያ ተቋርጦ የነበረው የኢንተርኔት አገልግሎት ተመለሰ

ኢትዮ ቴሌኮም... ወዴት? ወዴት?

የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ በደንበኞች ላይ የሚያደርሰው እንግልት ያሳዘናቸው መሆኑን ገልፀው ይቅርታ የጠየቁት ወይዘሪት ጨረር፤ እንደ አገልግሎት ሰጪም ኩባንያው ላይ የሚፈጥረው ተፅእኖ ቀላል እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ነገር ግን ኢንተርኔት አገልግሎት የሚቋረጠው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያትና ሌላ አማራጭ ሳይኖር ሲቀር ነው ይላሉ።

"እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው መቋረጡ ከዚህ ከሚያመጣው መስተጓጎል በበለጠ ችግር ሲኖርና ሃገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ነው እንዲህ አይነት ውሳኔ የሚተላለፈው፤ ያው ከሃገር ጥቅም የሚበልጥ ጉዳይ የለም" ብለዋል።

ኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን በመበደል ከዓለም ቀዳሚ ሃገራት አንዷ ነች ተባለ

የሳይበር ደህንነትንና በዓለም ላይ የኢንተርኔትን ስርጭት የሚቆጣጠረው ኔት ብሎክስ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በትናትንናው ዕለት እንዲሁም ዛሬ ጥዋት አገሪቷ ሙሉ በሙሉ ኢንተርኔት መቋረጡን በትዊተር ገፁ ያሰፈረ ሲሆን እንደ ምክንያትም የጠቀሰው በትናንትናው ዕለት በተጀመረውን ሃገር አቀፍ ፈተና ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ማጭበርበሮችን ለመከላከል እንደሆነ ነው።

ምንም እንኳን በብዙ አካላት ዘንድ ሀገር አቀፍ ፈተና ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ማጭበርበሮችን ለመቆጣጠር ነው የሚሉ ምክንያቶች ቢሰጡም ወይዘሪት ጨረር "ምክንያቱ ይህ ነው አልልም፤ በደፈናው በሃገር አቀፍ ፈተና ነው የሚል ምክንያት መስጠት አስቸጋሪ ነው" ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት ምን እንደተፈጠረ ይህ ነው የሚል ምክንያት ባይሰጡም ለወደፊት እንደሚገለፅ ተስፋ አላቸው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ