አርቲስት እቴነሽ ግርማ፡ “እዚህ ደረጃ የደረስኩት በእርሷ ብርታት ነው”

ድምፃዊት እቴነሽ ግርማ Image copyright Youtube/Screenshot

ከአርቲስት እቴነሽ ግርማ ጋር ላለፉት 31 አመታት ትዳር መስርቶ ይኖሩ እንደነበር ለቢቢሲ የተናገረው ድምጻዊ ደመረ ለገሰ ባለቤቱ እቴነሽ ግርማ ላለፉት አምስት አመታት በጡት ካንሰር ስትታመም መቆይቷን ገልጿል።

ድምጻዊት እቴነሽ የጡት ካንሰሯ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ሕክምና እየተከታተለች እንደነበር ይናገራል። ነገር ግን ካንሰሩ በሰውነቷ ተሰራጭቶ ሳንባዋን ማጥቃቱንና ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷን ባለቤቷ ደመረ ለቢቢሲ ተናግሯል።

አርቲስት እቴነሽ ላለፉት አምስት አመታት ብትታመምም አልጋ ላይ የዋለችው ግን ላለፉት ሶስት ወራት ብቻ ነው። "ከዚያ በፊት እየሰራችም እየታከመችም ነበር" ብሏል ባለቤቷ አርቲስት ደመረ።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ስርጭት "እጅግ አስበርጋጊ" ነው ተባለ

በተበከለ ደም አራት ወንድሞቹ የሞቱበት እንግሊዛዊ

የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ሕገ-ወጥ ስደትን ለመቀነስ አውሮፕላናቸውን ሊሸጡ ነው

ህመሟ ካንሰር መሆኑ እንደተረጋገጠ ጡቷ እንዲቆረጥ ብትጠየቅም 'ሰውነቴን ቢላዋ አይነካውም' በማለት እምቢ እንዳለች ይናገራል።

በበዓላት ወቅት በሚዘፈኑ ዘፈኖች የምትታወቀው ድምጻዊት እቴነሽ ድምጿ ይበልጥ ለአጃቢነት ይፈለግ እንደነበር አርቲስት ደመረ ይናገራል።

አርቲስት እቴነሽ በአማርኛና በኦሮምኛ የተሰሩ ሁለት አልበሞች ያሏት ሲሆን ከሌሎች የሙያ አጋሮቿ ጋር ደግሞ አራት የስብስብ (ኮሌክሽን) ስራዎችን ለገበያ አቅርባለች።

በግሏም ሶስት ነጠላ ዜማዎችን ሰርታለች።

በአሁኑ ወቅትም አዲስ የኦሮምኛ አልበም እየሰራች እንደነበረ የተናገረው አርቲስት ደመረ በየመሃሉ ስትታመም ስለነበረ በተፈለገው ፍጥነት መጨረስ እንዳልቻለች ተናግሯል።

"ወደፊት ከሙዚቃው አቀናባሪ ኢብራሂም ጋር ተመካክረን እንደሚሆን እናደርገዋለን" ብሏል።

የተዋወቅነው በልጅነታችን በማረሚያ ቤት ባንድ ውስጥ ነበር የሚለው ድምፃዊ ደመረ ከዚያ በኋላ ትዳር መስርተን ልጆችም አፍርተን አብረን በዚህ ሙያ ውስጥ ላለፉት ሰላሳ አንድ አመታት በደስታ ኖረናል ብሏል።

"እቴነሽ ባለቤቴ ብቻ ሳትሆን እናቴ ነች፤ ለዚህ ደረጃ የደረስኩት በእርሷ ብርታት ነው። ጠንካራ ሴት ነች" ብሏል።

እቴነሽ ግርማ ጥሩ የጥበብ ሙያ ያላት ነበረች፣ እርሷን በማጣታችን ብዙ ነገር ጎድሎብናል ያለው ደግሞ አርቲስት ታደለ ገመቹ ነው። "እቴነሽ ግርማ በአማርኛና በኦሮምኛ ስራዎችን ከመስራቷ ውጭ ጥሩ የሙያ ስነ ምግባር ያላት አርቲስት ነበረች" በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል።

ባለፈው ማክስኞ ከዚህ አለም በሞት የተለየችው አርቲስት እቴነሽ ግርማ የቀብር ስነ ሥርዓቷም ረቡዕ እለት በአዲስ አበባ ከተማ ለቡ አካባቢ በሚገኘው ገብርኤል ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።

በቀብር ሥነ ስርአቷ ላይም በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ቤተሰቦቿ ተገኝተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች