ትራምፕ በነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ለተፈፀሙት ጥቃቶች ኢራንን ከሰሱ

የአሜሪካ የጦር ኃይል ያወጣው የተንቀሳቃሽ ምስል በትንሽዬ ጀልባ ላይ የሚታዩ የኢራን ኃይሎች ያልፈነዳ ፈንጂ ከአንደኛው መርከብ አካል ላይ ሲያነሱ ያሳያል Image copyright Reuters

ኢራን በዖማን ባሕረ-ሰላጤ ውስጥ በሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ በተፈፀመው ጥቃት ውስጥ እጄ የለበትም ማለቷን የአሜሪካው ፕሬዝደንት አጣጣሉት።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በትንሽዬ ጀልባ ላይ የሚታዩ የኢራን ኃይሎች ያልፈነዳ ፈንጂ ከአንደኛው መርከብ አካል ላይ ሲያነሱ የሚያሳይ የቪዲዮ ማስረጃን በመጥቀስ ነው ኢራንን ተጠያቂ ያደረጉት።

ጉዳዩ ያሳሰባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "እውነታው ጥርት ባለሁኔታ መታወቅ አለበት" ብለዋል።

ሩሲያ በበኩሏ ሁሉም በጥድፊያ ከሚሰጥ ድምዳሜ እንዲቆጠብ አስጠንቅቃለች።

ኢትዮጵያ ኢንትርኔትን ስታቋርጥ በየቀኑ 4.5 ሚሊዮን ዶላር ታጣለች

የደም ሻጮችና ለጋሾች ሠልፍ

የአሁኑ የፈንጂ ጥቃት የተፈፀመው ከወር በፊት ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ አራት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ በተፈፀመ ጥቃት ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ ነው።

አሜሪካም በወቅቱ ለጥቃቶቹ ኢራንን ተጠያቂ አድርጋ ብትከስም ምንም ዓይነት ማስረጃ ግን አላቀረበችም ነበር፤ ኢራንም ክሱን አስተባብላው ቆይታለች።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ከተመረጡ በኋላ በአሜሪካና በኢራን መካከል የነበረው ፍጥጫ በከፍተኛ ደረጃ ተካሯል። ትራምፕ አሜሪካ በፕሬዝደንት ኦባማ የአስተዳደር ዘመን ከኢራን ጋር ደርሰው የነበረውን የኑክሊዬር ስምምነትን ከሰረዙ በኋላ በሃገሪቱ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ አጥብቀውታል።

ትራምፕ ምን አሉ?

ፕሬዝዳንቱ ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት "ኢራን ጥቃቱን ፈፅማዋለች" ብለዋል።

"እንደምገምተው ካጠመዷቸው ፈንጂዎች መካከል እንዱ አልፈነዳም ነበር፤ በላዩ ላይም የኢራን ስም ሳይኖርበት አይቅርም፤ በዛ በጨለማ ከመርከቡ ላይ ያልፈነዳውን ፈንጂ ሲያነሱ ተጋልጠዋል" ሲሉ ኢራንን ከሰዋል።

ፕሬዝደንቱ ጨምረውም በባሕር ላይ ክሚጓጓዘው የዓለም የነዳጅ ፍጆታ አንድ ሦስተኛው የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ሰርጥን ኢራን ልትዘጋው ትችላለች ብለው እንደማያስቡም ገልፀዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ኢራንን የወነጀሉት የሃገራቸው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዎ ጥቃቱን በተመለከተ ፈንጂዎችን፤ የሠለጠኑ ጥቃት ፈፃሚዎችንና በቅርብ በኢራን አማካይነት ተፈጽመዋል የተባሉ ተመሳሳይ ጥቃቶችን በማነጻጸር ኢራን ከጥቃቶቹ ጀርባ እንዳለች ከከሰሱ በኋላ ነው።

ኤርትራ በቤተ ክርስቲያን ስር ያሉ የጤና ተቋማትን ወሰደች

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ፓትሪክ ሻናሃንም "በዚህ ዓለም አቀፍ ችግር ላይ ዓለም አቀፍ መግባባት ለመፍጠር" አሜሪካ ያላትን የደህንነት መረጃ እያጋራች ነው በማለት ጣታቸውን ወደ ኢራን ጠቁመዋል።

የኢራን ምላሽ ምንድን ነው?

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሩሃኒ አርብ ዕለት "አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ መረጋጋት ላይ አሳሳቢ ስጋት እየደቀነች ነው" ሲሉ በዖማን ባሕረ-ሰላጤ ላይ የተፈፀሙትን ጥቃቶች በቀጥታ ሳይጠቅሱ ከስሰዋል።

አክለውም የትራምፕ አስተዳደር በተናጠል እራሱን ያገለለበትን የ2015 የኑክልዬር ስምምነት እንዲከበር ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኢራን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ በትዊተር ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ አሜሪካ "ቅንጣት ታክል ተጨባጭም ሆነ አመላካች ማስረጃ ሳይኖራት ዲፕሎማሲያዊ አሻጥር ለመፈፀም እየሞከረች ነው" ሲሉ ከሰዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ