ሰዎች በክትባት ላይ ያላቸው እምነት መቀነስ አደጋ እንደሆነ እየተነገረ ነው

vaccine Image copyright Getty Images

የዓለም ሕዝብ በክትባት ላይ ያለው እምነት እየተሸረሸረ መሆኑ ባለሙያዎችን ስጋት ላይ የጣለ ይመስላል።

አንድ ጥናት ነው የዓለም ሕዝብ በክትባት ላይ ያለው እምነት እየቀነሰ በመምጣቱ 'ልንከላከላቸው የምንችላቸው በሽታዎች በመስፋፋት ላይ ናቸው' ሲል የጠቆመው።

ክትባት ከየት ተነስቶ የት ደረሰ?

ጥናቱ 140 ሺህ ሰዎችን አሳትፏል፤ ተሳታፊዎቹ ደግሞ የተውጣጡት ከ140 ሃገራት ነው ተብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት 'ለክትባት ትኩረት መንፈግ' ለዓለም ጤና ስጋት ከሆኑ 10 ጉዳዮች አንዱ ነው ሲል ከሰሞኑ ተሰምቷል።

የክትባት ተቀባይነት እያሽቆለቆለ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረገ ዳሰሳ በክትባቶች ላይ ክፍ ያለ መተማመን እንዳለ ተመልክቷል።

ስለክትባቶች አስተማማኝነት፣ ስለክትባቶች ውጤታማነትና ክትባቶች ለህጻናት አስፈላጊ ስለመሆናቸው ከተጠየቁ የጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል ለእያንዳንዱ ጥያቄ 98 በመቶ የሆነ ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል።

(የኢትዮጵያን ውጤት ጨምሮ የሚፈልጉትን ሃገር ስምን ከታች ባለው ሳጥን ላይ በአማርኛ በመጻፍ ውጤቱን ማወቅ ይችላሉ።)

ይህንን ለመመልከት በጃቫስክሪፕት የሚሰራ ዘመናዊ ብራዉዘር ያስፈልግዎታል።

ጥናቱ እንደሚጠቁመው ክትባት ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ወይ? ተብለው በተጠየቁ ጊዜ 79 በመቶዎቹ አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጡ የተቀሩቱ ጥርጣሬያቸውን አሳውቀዋል።

እንደው ክትባት ያድናል ብላችሁ ታምናላችሁልን? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ደግሞ 84 በመቶው እንዴታ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፤ ቀሪው 16 በመቶ ግን ጥርጣሬ እንዳላቸው ነው ያሳወቁት።

እና ምን ችግር አለው?

ሳይንቲስቶች በጣም የጨነቃቸው ጉዳይ በክትባት ሊጠፉ የሚችሉ ገዳይ በሽታዎችን መከላከል እየተቻለ የሰዎች በክትባት ላይ ያላቸው እምነት ግን ከጊዜ ጊዜ መቀነሱ ነው።

Image copyright Science Photo Library

ክትባቶች በዓለም ዙሪያ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከበሽታ የመከላከል አቅም አላቸው። ፈንጣጣ ሙሉ በመሉ የጠፋው በክትባት ነው፤ ፖሊዮ ወደ መጥፋቱ ተቃርቧል - ዕድሜ ለክትባት ይሁንና።

እንደ ኩፍኝ ያሉ በሽታዎች ግን ሊጠፉ ነው ሲባል እያንሰራሩ ፈተና ሆነዋል። ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የዓለም ሕዝብ በክትባት ላይ ያለው እምነት መቀነስ ነው።

ፈር ቀዳጅ የታይፎይድ ክትባት ተገኘ

የዓለም ጤና ድርጅት የሚሠሩት ዶክተር አን ሊንድስትራንድ 'ነገሩ ከበድ ያለ ነው' ይላሉ። «ሰዎች ለክትባት ያላቸው እምነት በመቀነሱ የተነሳ ሊጠፉ የሚገባቸው በሽታዎች ማንሰራራታቸው አንድ እርምጃ ወደኋላ እንደማለት ነው።»

ኩፍኝ ተመልሷል

ኩፍኝን አጥፍተናል ያሉ ሃገራት በሽታው እያንሰራራ መሆኑን እየሰሙ ነው። 2016 ላይ ከነበረው የኩፍኝ በሽታ ምልክት 2017 ላይ የነበረው በ30 በመቶ የሚልቅ ነው።

አንድ ሰው አለመከተቡ ብቻ ሳይሆን በሽታውን ወደ ሌላ ማስተላለፉ ሌላው አደጋ ነው።

አንድ አካባቢ የሚኖሩ በርከት ያሉ ሰዎች ክትባት የሚከተቡ ከሆነ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ከበሽታ የመጠበቅ ዕድላቸው የሰፋ ነው ይላሉ ሳይንቲስቶች።

ኢምራን ካህን የተሰኙ ባለሙያ 'የኩፍኝ በሽታ ከ5 በመቶ በላይ የመስፋፋት ምልክት ካሳየ አደጋ ነው፤ አሁን እያየን ያለነው ደግሞ ይህንን ነው' ባይ ናቸው።

የተሻለ ገቢ አላቸው የሚባሉ ሃገራት የሚኖሩ ሰዎችም ጭምር ናቸው ስለክትባት ያላቸው ግምት የወረደ የሆነው።

ዓለማችን የኩፍኝ ወረርሽኝ ያሰጋታል

ፈረንሳይም ሆነ ጎረቤቷ ጣልያን እንዲሁም አሜሪካ ከሚታሰበው በላይ ሰዎች ክትባት ላይ ያላቸው እምነት እየተሸረሸረ ነው። በጠቅላላው አውሮፓ ደግሞ 59 ገደማ ሰዎቸ ብቻ ናቸው በክትባት ላይ እምነት ያላቸው።

በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካም ቢሆን 30 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ወይ ፈፅሞ በክትባት አያምኑም፤ አሊያም ጥርጣሬ አላቸው።

ዩክሬን [ከፍተኛ የኩፍኝ በሽታ የሚስተዋልባት የአውሮፓ ሃገር] 50 በመቶ ሰዎች ብቻ ናቸው ክትባት ላይ እምነት ያላቸው፤ ቤላሩስ 46 በመቶ፣ ሞልዶቫ 49 እንዲሁም ሩስያ 62 በመቶ በክትባት ላይ እምነት አላቸው፤ የተቀሩት አይስማሙም ማለት ነው።

ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት የሚኖሩ ሰዎች ክትባት ላይ ያላቸው እምነት የተሻለ እንደሆነ ነው ጥናቱ የሚጠቁመው። ደቡብ እስያ ቀዳሚ ክፍለ አህጉር ስትሆን፤ ምሥራቅ አፍሪቃ ተከታይ ናት።

ባንግላዲሽ እና ሩዋንዳ ዜጎቻቸውን በደንቡ በማስከተብ የሚችላቸው አልተገኘም። ሩዋንዳ ለማህፀን በር ጫፍ ካንሰር የሚሆን ክትባት ለዜጎቿ በማድረስ በዓለም ቀዳሚ ናት።

ጥናቱ እንደሚጠቁመው በሳይንስ ዶክተሮችና ነርሶች ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች ክትባት ፍቱን ነው ብለው ያስባሉ። በተቃራኒው ደግሞ ስለ ጉዳዩ በጣም የሚያጠኑ ሰዎች ለክትባት ያላቸው እምነት የሳሳ ነው።

ቢሆንም እምነት ማጣቱ ከበርካታ ጉዳዮች ሊመነጭ እንደሚችል ጥናቱ ሳይጠቁም አያልፍም።