አሜሪካ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ተጨማሪ ወታደር ልትልክ ነው

አሜሪካ በኢራን አብዮታዊ ዘብ ደረሰ ያለችውን ጥቃት የሚያሳይ ምስል Image copyright US Department of Defense

አሜሪካ ከኢራን ጋር የገባችው ውጥረት በተካረረበት ማግስት ተጨማሪ 1ሺህ ወታደር ወደ መካከለኛው ምስራቅ ልትልክ መሆኗን አሳውቃለች።

የመከላከያ ተጠባባቂ ጸሐፊ የሆኑት ፓትሪክ ሻናሀን እንዳሉት ተጨማሪ ወታደር ማሰማራት ያስፈለገው የኢራን መንግስት በሚያሳው "ጠብ አጫሪ ባህሪ" የተነሳ ነው።

የአሜሪካ ባህር ኃይል የኢራን አብዮታዊ ዘብ በነዳጅ ጫኝ መርከቦች ጥቃት አድርሷል በማለት ተጨማሪ ምስሎችን አውጥቷል።

ኢራን ሰኞ እለት እንዳስታወቀችው ከእንግዲህ በኋላ በጎርጎሳውያኑ 2015 የኒውክለር ፕሮግራሟን ለመቀነስ የገባችውን ስምምነት እንድታከብር እንደማትገደድ አስታውቃለች።

በአለም አቀፉ ማህበረሰብ የተቀመጠውን የዩራኒየም ውህድ ክምችት ገደብም ከፍ ለማድረግ ወስናለች።

"ለአውሮፕላኑ መከስከስ ፓይለቶች ተጠያቂ ሊሆኑ አይችሉም" አቶ ተወልደ ገብረማርያም

ሞሐመድ ሙርሲ ፍርድ ቤት ውስጥ ሞቱ

አምነስቲ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ለውጥ እንዲደረግበት ጠየቀ

የአሜሪካ ጦር ወደ መካከለኛው ምስራቅ እንዲንቀሳቀስ መደረጉ የተገለፀው ሰኞ እለት ከሰአት በኋላ ነበር።

ፓትሪክ ሻናሀን በመግለጫቸው ላይ እንዳስቀመጡት "አሜሪካ ከኢራን ጋር ግጭት ውስጥ መግባት አትፈልግም።" ነገር ግን እርምጃው የተወሰደው "በቀጠናው የተሰማሩ ወታደራዊ ኃይሎችን ደህንነትና የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ" ነው ብለዋል።

"የቅርብ ጊዜ የኢራን ጥቃት የሚያሳየው በኢራን ኃይሎች የሚፈፀመው ጠብ አጫሪ ባህሪና ቅጥረኛ ቡድኖች አሜሪካን ወታደራዊ ኃይልና በቀጠናው ላይ ያላትን ጥቅም አደጋ ላይ ለመጣል መንቀሳቀሳቸውን ነው" ብለዋል።

አክለውም መከላከያ ኃይሉ ያለውን ሁኔታ እየፈተሸ የወታደሮቹን ቁጥር እንደአስፈላጊነቱ ይወስናል ብለዋል።

የተሰማሩት ተጨማሪ ወታደሮች የት አካባቢ እንደሚመደቡ ይፋ የተደረገ ነገር የለም።

ሰኞ እለት የተጨመሩት ወታደሮች ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ካሰማሯቸው 1500 ወታደሮች በተጨማሪ መሆኑ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፒዮ እሁድ እለት አሜሪካ ከኢራን ጋር ጦርነት መግጠም ባትፈልግም "ያሉትን አማራጮች በአጠቃላይ ግን ታያለች" ብለው ነበር።

አክለውም ማክሰኞ እለት የመካከለኛው ምስራቅ ጦር አዛዦችን የሆኑትን እንደሚያገኙ ገልፀዋል።

በ2015 ኢራን የኒውክለር ማበልፀግ ፕሮግራሟን ለመቀነስ ከአሜሪካና አውሮጳ ሀገራት ጋር ስምምነት ላይ ደርሳ ነበር።

ነገር ግን ባለፈው አመት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ የገባችውን ስምምነት ሰርዘው ዳግመኛ ኢራን ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።

ይህ ውሳኔያቸው የኢራንን ምጣኔ ሐብት ያሽመደመደው ሲሆን ኢራን በምላሹ የገባችውን ስምምነት በመተላለፍ የዩራኒየም ማበልፀግ ፕሮግራሟን ከፍ አድርጋዋለች።

የአቶሚክ ኢነርጂ ባለስልጣኑ ይህንን በተናገሩበት መግለጫቸው አሁንም የአውሮጳ ሀገራት የአሜሪካን ማዕቀብ ማስቀረትና ኢራንን መታደግ ይችላሉ ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጀርመን ኢራንን በ2015 የገባችውን ስምምነት እንዳትጥስ ያስጠነቀቁ ሲሆን አሜሪካ ግን ኢራንን "ኒውክለርን ተጠቅማ ማስፈራሪያ የምታደርግ ሀገር" ብላታለች።