"በዚህ መንገድ መገደላቸው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መኖሩን ያሳያል" ጄነራል ፃድቃን

ጄነራል ፃድቃን Image copyright Geez media
አጭር የምስል መግለጫ ጄነራል ፃድቃን

ቢቢሲ፦ በሃገሪቱ ከፍተኛ ስልጣን ላይ ያሉና፤ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠበቁ እንደ ጄነራል ሰዓረ መኮንን እንዲሁም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንንና የሌሎቹም ግድያ ስለ ኃገሪቱ የፀጥታና ደህንነት ጉዳይ የሚናገረው አለ። እርስዎ ይህንን እንዴት ነው የሚረዱት ?

ጄኔራል ፃድቃን፦ ጄኔራል ሰዓረ መኮንን፣ ጄኔራል ገዛኢ አበራና ዶ/ር አምባቸው መኮንን ሌሎቹም በስራ ቦታቸው ላይ እያሉ መገደል በጣም ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ችግር እንዳለ ያሳያል። ኢንተለጀንስ አሰባሰብ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ነው የሚያሳየው፤ ከዚህ ቀደም እኔ የማውቀው እንኳን ይሄን ያህል ሴራ እየተሸረበ አይደለም በግለሰብ ደረጃ የሚደረጉ ትንንሽ ነገሮች ፈጥኖ ይታወቅ ነበር። ቀላል ያልሆነ የፀጥታ ችግር መኖሩን፣ በፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ መታየት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ነው የሚያሳየው።

ጄኔራል ሰዓረን የገደለው የራሱ የጥበቃ ኃይል ነው። መከላከያ ውስጥ የመከላከያን ተቋም የሚጠብቅ ፀረ-መረጃ የሚሉት ኃይል አለ። ለእንደነዚህ አይነት ትልልቅ ባለስልጣናት የሚመደብ ሰው የሚመደበው በዚህ አካል ከተጣራ በኋላ ነው። ይህ አለመሆኑ ቀላል ያልሆነ የፀጥታ ችግር እንዳለ ያሳያል። የፀጥታ ችግሩ ከፖለቲካዊ ሁኔታም ጋር ይያያዛል።

ቢቢሲ፦ክልላዊ "መፈንቅለ መንግሥት" አይደለም ፤ በከፍተኛ አመራሮች ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው የሚለው አከራካሪ ሆኖ እንዳለ፤ በአንድ ክልል ፤ በአንድ ፓርቲ ውስጥ በአመራሮች መካከል የልዩነት መካረር ነው ነገሮችን ወደዚህ ያመራው የሚለው ሃሳብ ጎልቶ እየወጣ ነው። የፖለቲካ ልዩነቶች መጨረሻቸው እንዲህ የሚሆን ከሆነ፤ ስለ ፖለቲካውም የሚለው ነገር አለ። እዚህስ ላይ ምን ይላሉ?

ጄኔራል ፃድቃን፦ "መፈንቅለ መንግሥት" ነው አይደለም የሚለው ክርክር ውስጥ መግባት አልፈልግም። ጉዳዩ በጣም አስቀያሚ ነው። ከህግ ውጭ ነው። ግን አንድ ግልፅ መሆን ያለበት ነገር አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የፌደራል ስርዓት አንድ ክልል እንኳን ሙሉ በሙሉ ቢቆጣጠሩ ኖሮ፤ አንደኛ አንድን ክልል የመቆጣጠር አቅማቸው አነስተኛ ነበር ብዬ ነው የምወስደው፤ ሁለተኛ ያ እንኳን ቢሳካ በሃገር አቀፍ ደረጃ ሊኖር የሚችለው ተፅኖ የተወሰነ ነበር ብዬ ነው የምወስደው።

ብጥብጥ አይፈጥርም፤ ችግር አይፈጥርም ማለት ሳይሆን የአገር የፖለቲካ ስልጣንን ከመያዝ አንፃር ግን በእኩል ደረጃ የነሱን ያህል አቅም ያላቸው ክልሎች አሉ። እነዛ ክልሎች ደግሞ የራሳቸው የፀጥታ መዋቅርም አላቸው። የራሳቸው ህገ መንግሥታዊ አወቃቀር አላቸው። ከዛ በላይ ፣ አንድ ክልል ውስጥ ከሚፈጠር ችግር በላይ የሚያልፍ አይሆንም ነበር ብዬ ነው የማስበው። ያም ሆነ ይህ ግን ከህገ መንግሥቱ ውጭ የሆነ በጣም አረመኔያዊ እርምጃ ነው። ከዚህ በመለስ ያለው "መፈንቅለ መንግሥት" ነው አይደለም የሚለው ክርክር አሁን ለተፈጠረው ነገር ብዙ ጠቀሜታ ያለው መስሎ አይሰማኝም።

ቢቢሲ፦አገሪቷ ለውጥ ላይ ነች እየተባለ ቢሆንም ከፍተኛ የብሔር ውጥረቶችና ጥቃቶችንም እየተመለከትን ነው። አሁን እያየነው ያለውን የፖለቲካ ባህል እንዴት ያዩታል?

መፈንቅለ መንግሥቱና የግድያ ሙከራዎች

ራሱን አጥፍቷል የተባለው የጄነራል ሰዓረ ጠባቂ ሆስፒታል እንደሚገኝ ተገለፀ

ጄኔራል ፃድቃን፦ አገራችን ውስጥ የፖለቲካ ችግር እንዳለ ይታወቃል። በተደጋጋሚም የሚነገር ጉዳይ ነው። በተለይም አማራ ክልል ውስጥ ፅንፍ የያዙ አንዳንድ ችግሮች ያጋጥሙ እንደነበር ይታወቃል። እነዚህ ችግሮች በእኔ አመለካከት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ ፈንድተው መውጣታቸው አይቀርም የሚል አመለካከት ነበረኝ። አሁን የሆነው የሚመስለኝ ይሄ ነው።

በጣም ፅንፈኛ የሆነው በኃይል ፍላጎቱን ለመጫን ሲሞክር የነበረው በአማራ ክልል ላይ ብቻ ሳይሆን በሃገር አቀፍ ደረጃ ይህንን ለማድረግ ሲያስብ የነበረው ግልፅ ሆኖ ወንጀል በመፈፀም ደረጃ ወጥቷል። አሁን የሚጠረጠሩት ፤ ተይዘዋል የሚባሉት፤ ተገድለዋል የሚባሉት ላይ ማተኮር ብቻ ሳይሆን መንግሥት ይሄን ሁኔታ እንደ 'ኦፖርቹኒቲ' እንደ እንደ እድል አይቶ ችግሮችን ለመፍታት አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮለታል ብየ አስባለሁ። በብልሃትና በብቃት ከተመራ ችግሩን ለመፍታት ጥሩ መነሻ ይሆነዋል ብየ አስባለሁ።

በሌላ በኩል ደግሞ በደንብ ካልተያዘ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ሊሄዱ የሚችሉበት እድልም መኖሩን የሚያሳይ ምልክትም አለ። ይሄንን ተግባር የፈፀሙ የተወነሱ ስብስቦች ፣ በአንድ የፀጥታ መዋቅር ብቻ የሰራ አይደለም። ከዛ በላይም ሌላ ስብስብ ይኖራል። ይህ ነገር በተፈጠረበት ክልልም ሌሎች የመንግሥት ተቋማትም አደጋው እስከምን ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ያሳየ ነው።

የተከፈለው ዋጋ በጣም ከፍተኛ ነው። ይህንን ዋጋ ከፍለን፤ መከፈል ያልነበረበት ዋጋ ነው። ግን ደግሞ የመጣውን አጋጣሚ ለጥሩ ነገር ተጠቅመን ችግሮቹን አንዴ ለመፍታት ጥሩ መነሻ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። ይህ ግን ዝም ብሎ የሚመጣ አይደለም። ብልሃት ያለው ሰከን ብሎ ከጥላቻ ፖለቲካ ወጥቶ በአማራጭ የፖለቲካ ሃሳቦች በማመን የአመራር ፖለቲካ ይጠይቃል። ይህ ጠንከር ያለ ስራ ይጠይቃል። ያ ካልሆነ የቀደመውን የጥላቻ ፖለቲካን እያራገቡ የሚኬድ ከሆነ ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል።

ቢቢሲ፦የፌደራሉ መንግሥት በአማራ ክልል የተፈጠረውን "መፈንቅለ መንግሥት" ብሎታል። "መፈንቅለ መንግሥት" በክልል ደረጃ ይደረጋል ወይ? ግቡስ ምን ሊሆን ይችላል?

ጄኔራል ፃድቃን፦ አሁን ባለው የኢትዮጵያ አወቃቀር በክልል ደረጃ እንዲህ አይነት ነገር ሲፈፀም አላውቅም። አልነበረም ማለት አይደለም፤ ኖሮ ሊሆን ይችላል እኔ ግን አላውቅም። በኢትዮጵያ አሁን ባለው የመንግሥት አወቃቀር ደረጃ አንድ ክልል ውስጥ ስልጣን እንኳን ቢያዝ አንደኛ ክልሉ ላይ ያለውን ኃይል ሁሉ አጥፍቶ ስልጣን የመያዝ እድሉ አነስተኛ ነው።

ነገር ግን ስልጣን ቢያዝና የክልሉን ኃይል ቢቆጣጠሩ በሃገር አቀፍ ደረጃ አበቃለት የሚባል አይደለም። ዋናው ኃይል የፌደራል ስርአቱ ነው። የፌደራል ስርአቱ ደግሞ የህዝብን ምርጫ ምንም ግምት ውስጥ ሳያስገባ በጉልበት የክልሉን ስልጣን ይዞ አስተዳድራለሁ ሊል አይችልም።ይህ ለክልሉ ህዝብ ስድብ ነው የሚመስለኝ። የክልሉን ህዝብ ፖለቲካዊ አስተሳሰብና ባህል መናቅ ነው። የሚመስለኝ ግን ይህንን ለጊዜው ትተን ቢሳካለት እንኳን ከክልሉ ያለፈ ችግር አይሆንም።

በክልሉ ላይ ያለውን ችግር ደግሞ የፌደራል መንግሥቱ ከሌሎች ክልሎች ጋር በመሆን ሊፈታው ይችል የነበረ ነው የሚመስለኝ። እኔ ምን ሊባል እንደሚችል የያዝኩት ቃል የለኝም፤ የክልል "መፈንቅለ መንግሥት" ነው የሚሆነው፤ ነገር ግን በክልል ብቻ የተቃጣ አይደለም። ከክልል በላይ አልፎ በመከላከያም ውስጥ የተቀናጀ ስራ እንዲሰራ አድርገዋል። ግን ደግሞ ይሄ ያመጣው ውጤት የሚታወቅ ነው። ስለዚህ ያም ሆነ ይህ በሃገር አቀፍ ደረጃ ስልጣን ለመያዝ አስበው ከሆነ እሱን የሚያሳይ ምልክት የለም ።

በክልል ደረጃ ስልጣን ለመያዝ አስበው ነው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት፤ መከላከያ ላይ የነበሩትንም ባለስልጣናት እርምጃ የወሰዱባቸው በክልላቸው ለሚደረግ ስራ እንቅፋት እንዳይፈጥሩባቸው ነገሮችን ለማዛባት አስበው የሰሩት ነው የሚመስለው። እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ፤ ይሄ ደግሞ ክልሉ ላይ ለሚሰራው ስራ ማሳለጫ ነው እንጂ ስልጣን ለመያዝ የታሰበ አይመስልም።

አማራ ክልል ላይ ቢሳካላቸው ኖሮ የሚሄደው ርቀት አነስተኛ ነው።አማራ ክልሉም የመሳካት አቅሙ አነስተኛ ነበር ፤ የታየውም ይሄ ነው። ፍላጎት አልነበራቸውም ማለት አይደለም፤ ስላልቻሉ ነው የወደቀው፤ የአገር ውስጥ ጉዳት በጣም ከፍተኛ ቢሆንም ከዚያ በላይ መሄድ የሚችል አልነበረም ብየዬነው የምወስደው።

የሰኔ 16ቱ ጥቃትና ብዙም ያልተነገረላቸው ክስተቶች

ተያያዥ ርዕሶች