ከጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ጋር አጭር ቆይታ

የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁን Image copyright EDUARDO SOTERAS

ቢቢሲ ትናንት የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁንን በስልክ ያነጋገራቸው የክልሉ አመራሮች የቀብር ሥነ-ስርዓት ለመካፈል ባህር ዳር ሳሉ ነበር።

አቶ ንጉሱ ትናንት በባህር ዳር በተካሄደው የቀብር ሥነ-ስርዓት ላይ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል የተወጣጡ እንግዶች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ዘመድ እና ቤተሰብ እንዲሁም የክልል እና የፌደራል መንግሥት አካላት እንደተገኙ እና የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ፕሮቶኮሉ በሚፈቅደው መሠረት መካሄዱን ተናግረዋል።

''ትልቅ ቁጭት እና ሃዘን የታየበት ሥነ-ሥርዓት ነበር። እንግዶች ንግግር ሲያደርጉ ሲቃ እየተናነቃቸው ነበር። ለክልላቸው እና ለሃገራቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት በማንሳት ከስማቸው በላይ ታሪክ ሠርተው ያለፉ መሆኑን የሚያመላክቱ መልዕክቶች በልጆቻቸው እና በሌሎች ተደምጧል'' ብለዋል።

የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈፀመ

የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈፀመ

በላሊበላም የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ሥርዓተ ቀብር መፈጸሙን በማስታወስ፤ በላሊበላ የነበረው ስሜት እና ሥነ-ሥርዓት ምን ይመስል ነበር ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ንጉሱ ሲመልሱ፤ ''በባህር ዳር የነበረውን ሥነ-ሥርዓት ነበር ስንከታተል ነው የነበርነው። እዚያ ስለነበረው ነገር መረጃው የለኝም። መረጃው እንደደረሰን እናደርሳችኋላን'' በማለት በደምሳሳው አልፈውታል።

የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው አሟሟት

ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ አሟሟትን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ እንዲሰጡን የተጠየቁት አቶ ንጉሱ ''ኦፕሬሽኑን ያከናወነው የጸጥታ መዋቅሩ ነው። ከባህር ዳር አቅራቢያ ዘንዘልማ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ነው ቦታው። ነገር ግን በዝርዝር የነበረውን ሂደት መረጃው ሲገኝ እናሳውቃለን። አሁን መረጃው የለኝም'' ብለዋል።

ጄነራሎቹን ገድሏል ስለተባለው የግል ጠባቂ

ቅዳሜ ሰኔ 15/2011 ምሽት ጠቅላይ ኤታማዦር ጄነራል ሰዓረ መኮንን ከአጋራቸው ጄነራል ገዛዒ አበራ ጋር በገዛ ጠባቂያቸው በመኖሪያ ቤታቸው ሳሉ በጥይት ተመትተው ሕይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።

በቀጣዩ ቀን የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት በሰጠው መግለጫ ጄኔራሉን እና ወዳጃቸውን በጥይት መትቶ ገድሏል የተባለው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ አስታውቆ ነበር።

ሰኞ ከሰዓት ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው ጄኔራሎቹን ገድሏል የተባለው ጠባቂ ራሱን ማጥፋቱን ተናገሩ። ሰኞ ምሽቱን ደግሞ ፌደራል ፖሊስ ቀደም ሲል ራሱ የሰጠውን መግለጫ አስተባብሎ ጠባቂው በሕይወት እንደሚገኝ አስታውቀ።

የባለአደራ ምክር ቤት አባላት ከ'መፈንቅለ መንግሥቱ' ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት ቀረቡ

እኛም እርስ በእርስ የሚጣረሱ መረጃዎች እንዴት ሊወጡ ቻሉ? ጄነራሎቹን ገድሏል የተባለው ጠባቂስ አሁን በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛል? ስንል ለጠቅላይ ሚንሰትሩ የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ አቶ ንጉስ ጥላሁን ጥያቄያችንን አቅርበንላቸዋል።

አቶ ንጉሱ የመረጃ ክፍተቱ እንዴት ሊፈጠር አንደቻለ ሲያስረዱ ''በአዲስ አበባም ይሁን በባህር ዳር የተፈጠረው ችግር ድንገተኛ ነው፤ አደናግጧል፤ አደናብሯል። ሁሉም መረጃ በአንድ ግዜ አይገኝም። በወቅቱ የሚደርሱ መረጃዎች ለመገናኛ ብዙሃን ሲሰጡ ነበረ። መረጃዎች የሚስተካከል፤ የሚታረም ነገር ሊኖራቸው ይችላል። ሰው ነው የሚሰራው፤ ሰው ነው የሚናገረው። መረጃው ደግሞ ታቅዶ፣ ተደራጅቶ፣ ተገምግሞ የሚሰጥ ዓይነት መረጃ አይደለም። እንደዚህ አስቸኳይ በሆነበት ሰዓት፣ ሕብረተሰቡ መረጃ በሚፈልግበት ሰዓት፣ መገናኛ ብዙሃን በሚያጣድፉበት ሰዓት እንዲህ ዓይነት ስህተቶች አያጋጥሙም ማለት አይደለም'' ይላሉ።

ተጠርጣሪው እንዴት በቁጥጥር ሥር እንደዋለ እና አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታ የተጠየቁት አቶ ንጉሱ፤ ''የግል ጠባቂው በጄነራሎቹ ላይ እርምጃ ከወሰደ በኋላ ተታኩሶ ነበረ። በዚህም የተኩስ ልውውጥ እሱም ላይ እርምጃ እንደተወሰደበት እና ወደ ህክምና ሥፍራ ተወስዶ ጥበቃ እየተደረገለትና የጤና ክትትል እያደረገ ነው'' ነው ሲሉ መልሰዋል።

''የጤንነቱን ጉዳይ ሃኪሞች፤ የጥበቃውን ሁኔታ ደግሞ የጸጥታ መዋቅሩ እየሰሩ ነው። ሌሎች ጉዳዮች ወደፊት የሚጠሩ ይሆናሉ'' በማለት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

'በመፍንቅለ መንግሥቱ ሙከራ' ጉዳት የደረሰባቸው እና በቁጥጥር ሥር የዋሉ ምን ያክል ናቸው?

''ጉዳዩ ከተከሰተ ወዲህ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ የተደረጉ ሰዎች አሉ። አሁንም ሥራው እየተሠራ ነው። ቁጥሩ በየጊዜው የሚለዋወጥ ስለሆነ በትክክል ይሄ ነው ብሎ መግለጽ አይቻልም። ሥራው የፖሊስ፣ የክልል ልዩ ኃይል እና የሃገር መከላከያ ሠራዊት ጥምር እንቅስቃሴ ነው። መረጃውም ያለው በጸጥታ መዋቅሩ እጅ ነው። የተደራጀ መረጃ ወደፊት ይሰጣል'' ሲሉ መልሰዋል።

የኢንተርኔት ጉዳይ

'የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን' ተከትሎ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል። የኢንተርኔት አገልግሎት ለምን እንዲቋረጥ ተደረገ? አግልግሎቱስ ክፍት የሚሆነው መቼ ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ደግሞ፤ ''በዚህ ጉዳይ ላይ መልስ መስጠት አልችልም። የምገኘው ባህር ዳር ነው። ወንድሞቻችንን እየሸኘን ነው። ሌሎች አካላትን በጉዳዩ ላይ መጠይቅ ይቻላል'' በማለት አልፈውታል።