ኤርትራ፡ የሚስዮን እምነት ተከታዮችን አሰረች

አሥመራ ከተማ Image copyright DEA / A. TESSORE
አጭር የምስል መግለጫ አሥመራ ከተማ

በኤርትራ የፌዝ ሚሽን ቤተክርስቲያን ተከታዮች በመንግሥት የጸጥታ ኃይል በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጋቸው ተነገረ።

ባለፈው እሁድ በኤርትራ መንግሥት የጸጥታ አካላት የታሰሩት የፌዝ ሚሽን ቤተክርስቲያን ተከታዮች 'ሐሽፈራይ' ተብሎ ወደ ሚጠራው ስፍራ መወሰዳቸውን የታሳሪ ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

'ሐሽፈራይ' በተለምዶ የኤርትራ መንግሥት ሰዎችን ያለ ፍርድ የሚያስርበት ስፍራ እንደሆነ በስፋት ይነገራል።

ጡት የሚያጠቡ እናቶች ከጨቅላ ልጆቻቸው፤ እንዲሁም በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች ጨምር 'ሐሽፈራይ' እና ከረን ከተማ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ለእስር መዳረጋቸውን የቤተሰብ አባላት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

''ዕድሜያቸው ከሰማንያ በላይ የሆኑ አዛውንቶች አሉ፤ ጡት የሚጠቡ ህጻናትም ሁሉ ታስረዋል። ባል እና ሚንት ከእነ ልጆቻቸው ታስረዋል።'' ሲል ከታሳሪ ቤተሰቦች አንዱ ለቢቢሲ ገልጿል።

ለእስር የተዳረጉት የእምነቱ ተከታዮች ባሳለፍነው እሁድ ጠዋት ለአምልኮ በተሰበሰቡበት ስፍራ በጸጥታ አካላት ቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም በአከባቢው የነበሩ መገልገያ ቁሶች እና ጥሬ ገንዘብ በጸጥታ ኃይሎቹ መወሰዳቸው ተነግሯል።

''አብዛኞቹን የእመነቱ ተካታዮችን ወደ ሐሽፈራይ ወስደዋቸዋል። መሪዎች ናቸው ያሉዋቸው ደግሞ ከረን ከተማ ፖሊስ ጣብያ እንዲቆዩ ተደርጓል።''

ሚስዮን እምነት ቤተክርስትያን በኤርትራ ከተከለከሉት እምነቶች አንዱ ነው።

እንደ አዎሮፓውያኑ አቆጣጠር 2002 የኤርትራ መንግሥት ሁሉም የኢቫንጀሊካል እና ጵንጤቆስጣል አብያተ ክርስትያናት ካገደ በኋላ መሪዎቻቸው እና ተከታዮቻቸውን ሲያስር ቆይቷል።

የኤርትራ መንግሥት፡ 'የካቶሊክ ጤና ተቋማትን መውሰዴ ትክክል ነው' አለ

የኤርትራ መንግሥት በቅርቡ የካቶሊክ ቤተክርስትያን የጤና ተቋማትን የዘጋ ሲሆን፤ ይህንንም ተከትሎ በኤርትራ መንግሥት ላይ በርካቶች የሰላ ትችት ሲሰነዝሩ ነበር።

ትችቱን ተከትሎም ትናንት የኤርትራ መንግሥት «ማንኛውም የኃይማኖት ተቋም የሕክምና አገልግሎት ሊሰጥ አይገባም። . . . ይህ የእነርሱ ተከታይ ያልሆነ ላይ አድልዎ እንደማድረስ የሚቆጠር ነው» በማለት ምላሽ የሰጠ ሲሆን፤ ወደፊትም ሁሉም ኃይማኖታዊ ተቋማት ጤና ተቋሞቻቸውን ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የማስረከብ ግዴታ እንደሚኖርባቸው በመግለጫው አክሏል።

የኤርትራ የኦርቶክስ ቤተክርስቲያን፣ የኤርትራ ኤቫንጄሊካል ቤተክርስቲያን፣ የሮማን ካቶሊክ ቤተክስቲያን እና የእስልምና ዕምነቶች ብቻ ናቸው በኤርትረ ፍቃድ ያላቸው።