አብን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከ100 በላይ አባላቶቼ ታስረዋል አለ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አርማ Image copyright NAMA

ሰኔ 15 አመሻሽ ላይ በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና በከፍተኛ የመከላከያ ጄነራሎች ላይ ግድያ ከተፈፀመ በኋላ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰዎች እየታሰሩ መሆናቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናገሩ።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ "አባላቶቻችንና አመራሮቻችን በተለያዩ አካባቢዎች እየታሰሩብን ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የጅምላ እስር የሚመስል ነገር ነው ያለው" ያሉት አቶ ክርስቲያን "የአብን አባሎችና አመራሮች ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ንቃተ ህሊናቸው ከፍ ያሉ ናቸው ተብለው የሚገመቱ ግለሰቦችንና ነዋሪዎችንም ጭምር ዝም ብሎ የማሰር ሁኔታ ነው የሚታየው" ሲሉ ተናግረዋል።

"መደናገጥ ባለበት ወቅት ስህተቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ" አቶ ንጉሱ ጥላሁን

በቤንሻንጉል ክልል በሽፍቶች በደረሰ ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ

የኤርትራ መንግሥት፡ 'የካቶሊክ ጤና ተቋማትን መውሰዴ ትክክል ነው' አለ

56 የሚደርሱ የክፍለ ከተማና የወረዳ አባላትና አመራሮች በአዲስ አበባ ታስረውብናል ያሉት አቶ ክርስቲያን ወደ 50 የሚደርሱ ደግሞ ወለጋ ላይ መታሰራቸውን ይናገራሉ።

አዳማ አንድ፣ ጅማ ሰባት ወለንጪቲና ሱሉልታ አካባቢዎች ደግሞ 25 የሚደርሱ አባላት፣ አመራሮች እንዲሁም ንፁሃን ዜጎች ታስረዋል ያሉት አቶ ክርስቲያን ይህ መረጃ እስከ ትናንት ምሽት ድረስ ብቻ የተጠናቀረ ነው በማለት የታሳሪዎች ቁጥሩ ከዚህም ሊጨምር ይችላል ብለዋል።

አባላቶቻቸው የታሰሩባቸውን ምክንያቶች ለማጣራት ስላደረጉት ሙከራ አቶ ክርስቲያን ሲገልጹ አዳማ የታሰረው የአብን ቅርንጫፍ አስተባባሪ ፍርድ ቤት መቅረቡንና ክሱ "ምንጃር አረርቲ ላይ የነበረውን ግጭት በገንዘብ ደግፈሀል" የሚል እንደሆነ አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ በተለምዶ ሦስተኛ የሚባለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ታስሮ የሚገኘው የብሔራዊ ምክር ቤት አባላችን ያሉት ግለሰብ ደግሞ ከሰሞኑ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ግንኙነት አላችሁ በሚል መታሰሩ እንደተነገረው አስረድተዋል።

በአጠቃላይ በተለያየ አካባቢ የታሰሩ አባላቶቻቸውና አመራሮች "ለሰላምና ደኅንነት እንዲሁም መረጋጋት ስጋት ናችሁ" የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው እንደነገሯቸው አቶ ክርስቲያን ገልጸዋል።

ወለጋ ላይ የአብን አባል ያልሆኑ፣ ድሬዳዋ ላይ የአብን አባላት ብቻ ሳይሆኑ የአዴፓ አባላት የአብን ደጋፊ ናችሁ በሚል ተይዘዋል ያሉት አቶ ክርስቲያን አንዳንዶቹ ከሌሎች እስረኞች በተለያ ስፍራ መታሰራቸውን ሰምተናል ይህ ደግሞ ስጋት ውስጥ ይከተናል ብለዋል።

"በመሰረታዊነት ሕግ መተላለፍ ካለ ለማንኛቸውም ወንጀለኛ አብን መደበቂያ ዋሻ እንዲሆን አንፈልግም" የሚሉት አቶ ክርስቲያን ንፁሀን ዜጎችና አባሎቻቸው በምን ምክንያት እንደታሰሩ ሳይነገር ለሰላምና ደህንነት ስጋት ናችሁ ብሎ ማሰር "አንድም ወንጀል ነው አንድም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ፓርቲ በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ እንዲህ አይነት ነገር መፈጠሩ ምናልባትም እዚያ አካባቢ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማጥበብና በተለይም አማራ መደራጀት እንዳላስደሰታቸው የሚያመላክት ሆኖ አግኝተነዋል" ብለዋል።

ከአንድ አባላቸው በስተቀር ሌሎች የታሰሩ አባላትና አመራሮች ላይ ምንም አይነት ክስ አልቀረበም ያሉት አቶ ክርስቲያን አባላቶቻችን ከህግ አግባብ ውጪ በፖለቲካ አባልነታቸው ብቻ ማሰር የማሸማቀቅ ተግባር እየተፈፀመ ነው ሲሉ ይከስሳሉ።

ሰሞኑን በሃገሪቱ ያጋጠመውን ችግር በተመለከተ መግለጫ የሸጠው የፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረ ኃይል ትናንት ባወጣው መግለጫ በአማራና በአዲስ አበባ ውስጥ ከድርጊቱ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ በርከታ ሰዎች እንደተያዙ አመልክቷል።

ተያያዥ ርዕሶች