አዴፓ የከሸፈውን መፈንቅለ መንግሥት ያቀነባበሩትና የመሩት "የእናት ጡት ነካሾች" ናቸው አለ

የአዴፓ ሎጎ Image copyright Fana Broadcasting corporate

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰኔ 15 በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና በመከላከያ ሠራዊት ጄነራሎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ አስመልክቶ አስቸኳይ ስብሰባ በማካሄድ ባለስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫው ላይ ሰኔ 15/2011 ዓ.ም የተካሄደውን የከፍተኛ አመራሮች ግድያና መፈንቅለ መንግሥቱን ያቀነባበሩና በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትንም አውግዟል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፓርቲ ከታገለባቸው ጉዳዮች መካከል "የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲከበር" መሆኑን አስታውሶ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች ከታሰሩበት ነፃ እንዲወጡ በግምባር ቀደምትነት የታገሉትን አመራሮች "በግፍና በጭካኔ መግደል የእናት ጡት ነካሽነት እና ክህደት" ነው በማለት ድርጊቱን አውግዟል።

"ብ/ጄነራል አሳምነው በባጃጅ ለማምለጥ ሲሞክሩ ነው የተገደሉት''

በኢትዮጵያ የኤሊ አደን ለምን አየተበራከተ መጣ?

በፌስታል ተጥላ ለተገኘችው ልጅ የጉዲፈቻ ጥያቄዎች ጎረፉላት

አክሎም "በከሸፈው መፈንቅለ-መንግሥት የተፈፀመው ጥቃትና ወንጀል እንዲሁም የአመራሮቻችን የግፍ አገዳደል የአማራን ሕዝብ ያሳፈረና ያዋረደ ሆኖ ሳለ ወንጀሉን ለመሸፋፈን እና ለማሳነስ ሆነ ተብሎ አሉቧልታ በመንዛት ህዝባችንን ለማደናገር እና አቅጣጫ ለማሳት የምትሰሩ አካላት ከዚህ ዕኩይ ድርጊታችሁ ተቆጠቡ" ሲል አሳስቧል።

የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ በከሸፈው መፈንቅለ-መንግሥት እጃቸው ያለበትን ግለሰቦችና ቡድኖች በህግ ቁጥጥር ስር የማዋል ሥራው በሁሉም አካላት ርብርብ "በአጠረ ጊዜና በተሳካ ሁኔታ የተፈፀመ መሆኑን" ጠቅሶ "አሁንም ወንጀለኞችን ሙሉ በሙሉ በህግ ቁጥጥር ስር የማዋልና ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል" ሲል አስታውቋል።

በክልሉ በተደጋጋሚ የታዩ የሰላም መደፍረሶችን በማንሳትም የፀጥታ መዋቅሩን መልሶ ለማጠናከርና በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ "በልዩ ሁኔታ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ አስፈላጊው ሁሉ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል" ብሏል።

ድርጅቱ ውስጣዊ አንድነቱ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንደሚገኝ አስታውሶ የድርጅቱን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የክልሉንና የኢትዮጵያን ሕዝቦች፤ "ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት በመቆም የተፈጠረውን ፈተና" በብቃት ለማለፍና አገራችንን ለመታደግ በፅናት እንድትቆሙ" በማለት ጥሪውን አቅርቧል።

አክሎም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የተለያዩ አካላት መረጋጋትን፣ ሠላምና አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ በማተኮር በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው አስታውሷል።

በመጨረሻም የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት በአማራ ክልልና ሕዝብ ላይ ብቻ የተፈፀመ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈፀመ ጥቃት መሆኑን በመግለፅ በዚህ ወቅት ከጎኑ የነበሩትን በአጠቃላይ አመስግኗል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ