የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (የአብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ከእስር ተፈቱ

 ክርስቲያን ታደለ
Christian Tadele FB
"አብረውን ከታሰሩት አባሎቻችን መካከልም ደሳለ ገበየሁ የተባለውን አንዱን የዞን አመራራችንን ለይተው በመውሰድ ድብደባ ፈጽመውበታል፤ ይህም የሚያሳየው የግል ቂም በቀልን መሰረት ያደረገ ጥቃት መሰንዘሩን ነው"
ክርስቲያን ታደለ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (የአብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ከእስር ተፈቱ። አቶ ክርስቲያን ትናንት በምዕራብ ጎጃም ሰከላ ወረዳ ከስምንት የአብን አባሎች ጋር ነበር የታስሩት።

አቶ ክርስቲያን ዛሬ ጠዋት ለቢቢሲ እንደገለጹት ትናንት በሰከላ ወረዳ አንድ አባላቸው በመታሰሩ የእርሱን ጉዳይ ለመከታተል ወደ ስፍራው በማምራት ላይ እያሉ የአካባቢው ፖሊስ ከሕዝብ ትራንስፖርት ላይ በማስወረድ "እንደሚፈለጉ" ነግረዋቸው በአምቡላንስ ሊወስዷቸው እንደነበር ገልጸዋል።

"ነገር ግን አምቡላንስ ለወላድ እናቶች እንጅ ለሌላ አገልግሎት መዋል የለበትም፤ ከጠረጠራችሁን በፖሊስ መኪና ልትወስዱን ትችላላችሁ" በማለት እንደመለሱ የሚናገሩት አቶ ክርስቲያን በመጨረሻም ከፖሊስ አባላት ጋር ተስማምተው መጀመሪያ ይጓዙበት በነበረው የሕዝብ ትራንስፖርት በጋራ በመሄድ ፖሊስ ጣቢያ ከደረሱ በኋላ "ጠርጥረናችኋል" በሚል እንዳሰሯቸው ነግረውናል።

አብን ከ100 በላይ አባላቶቼ ታስረዋል አለ

ዛሬ ጠዋትም ለመታሰራቸው ምክንያቱ "ለፍተሻ አልተባበራችሁም" በሚልና "የእናንተን መምጣትን ተከትሎ ሕዝቡ ወደ አለመረጋጋት እንዳይሄድ በማሰብ ነው" የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸው አምስቱም ከእስር እንደተፈቱ አቶ ክርስቲያን ተናግረዋል።

"ነገር ግን ሁለት የወረዳና አንድ የክልል አመራር አሁንም በዚያው ወረዳ እንደታሰሩ ናቸው" ያሉት አቶ ክርስቲያን የታሰሩበት ምክንያትም የተለየ የፖለቲካ አስተሳሰብን ሰበብ በማድረግና ከግል ቂም ጋር የተያያዙ ናቸው ብለዋል።

"አብረውን ከታሰሩት አባሎቻችን መካከልም ደሳለ ገበየሁ የተባለውን አንዱን የዞን አመራራችንን ለይተው በመውሰድ ድብደባ ፈጽመውበታል፤ ይህም የሚያሳየው የግል ቂም በቀልን መሰረት ያደረገ ጥቃት መሰንዘሩን ነው" ሲሉ ይከሳሉ።

በአጠቃላይም ሰከላ ወረዳ ሦስት፣ ቋሪት ወረዳ ሁለትና ደብረታቦር አንድ በድምሩ ስደስት አባላትና ደጋፊዎቻቸው በአማራ ክልል መታሰራቸውን ተናግረዋል።

ጄኔራል አደም የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆነው ተሾሙ

በታንዛኒያ እስር ቤቶች በተደረገ አሰሳ 743 ኢትዮጵያውያን ተገኙ

"ባለፈው ሳምንት በተከሰተው ነገር ሁላችንም እንደሕዝብ ተጎድተናል አንዱ የበለጠ ተቆርቋሪ ሌላው የማይቆረቆር የሚሆንበት ምክንያት የለም" ያሉት አቶ ክርስቲያን በአዲስ አበባና በኦሮሚያ የታሰሩት አባሎቻቸውን በተመለከተ ለጊዜው የደረሳቸው አዲስ መረጃ አለመኖሩን ተናገረዋል።

ከትናንት በስቲያ አቶ ክርስቲያን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአዲስ አበባና በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ከአንድ መቶ በላይ አባሎቻቸው እንደታሰሩ መግለፃቸው ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች