ትራምፕ የሰሜን ኮሪያን ምድር የረገጡ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆኑ

ትራምፕ እና ኪም ተገናኝተዋል Image copyright Reuters

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮሪያው አቻቸው ኪም ጆንግ ኡን ተገናኝተዋል።

ዶናልድ ትራምፕ እና ኪም ጆንግ ኡን የተገናኘት 'ዲሚሊታራይዝድ ዞን' [ከጦርነት እና መሰል ኹነቶች ነፃ የሆነ ቦታ] በመባል በሚታወቅ በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ባለ ሥፍራ ነው።

«ድጋሚ ስለተገናኘን ደስ ብሎኛል» በማለት ነው ኪም ጆንግ ኡን ትራምፕን የተቀበሏቸው።

ኪም፡ 'እብዱ' ትራምፕ ለንግግሩ ዋጋ ይከፍላል

ትራምፕ በበኩላቸው አቻቸውን አመስግነው 'ጠለቅ ያለ ጓደኝነት ነው ያለን' ሲሉ ተደምጠዋል። «መጀመሪያ ከተያየንባት ቀን ጀምሮ ነው 'ዓይነ ውሃችን' የገጠመው» ሲሉ ነው ትራምፕ የሁለቱን መሪዎች ግንኙነት የገለፁት።

አጋራቸው ኪም ጆንግ ኡንን ለመጨበጥ ሲሉ ወደ ሰሜን ኮሪያ ድንበር የዘለቁት ትራምፕ፤ የሰሜን ኮሪያን ምድር የረገጡ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝደንት በመሆን ታሪክ ሰርተዋል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ትራምፕ የሰሜን ኮሪያን ምድር የረገጡ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝደንት በመሆን ታሪክ ሰርተዋል

የሲኦል ዩኒቨርሲቲው ተንታኝ ጆን ዴሉሪ ኪም ከሌላው ጊዜ በተሻለ ከትራምፕ ጋር ሲገናኙ ፈታ ብለው መታየታቸው መልካም ምልክት ሳይሆን አይቀርም ይላሉ።

የአሜሪካ ነጩ ቤተ-መንግሥት አማካሪ የሆኑት የፕሬዝደንቱ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ በሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ላይ ከነበሩ ስመ-ግዙፍ ሰዎች አንዷ ናቸው።

ትራምፕ ለቡድን 20 ሃገራት ስብሰባ ደቡብ ኮሪያ ነበሩ። ከዚያ ሲመለሱ ነው በድንገት የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪምን የማግኘት ሃሳብ እንዳላቸው ያሳወቁት።

ያልተጠበቀው የሁለቱ ሃገራት መሪዎችን ግንኙነት ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ቢያዳግትም መልካም ነው የሚሉ ይበዛሉ።

ኪም ሌሎች አማራጮችም አሉ ሲሉ አስጠነቀቁ

ሁለቱ መሪዎች ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች አጠር ያለ ምላሽ ከሰጡ በኋላ ደቡብ ኮሪያ ድንበር ውስጥ በሚገኝ ቤት ውይይት አካሂደዋል።

ትራምፕ አቻቸው ኪም ጆንግ ኡንን አሜሪካን እንዲጎበኙ እጋብዛቸዋለሁ ሲሉም ለጋዜጠኞች ቃል ገብተዋል።

ለአንድ ሰዓት ያክል የቆየው የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ተጠናቆ ትራምፕ ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት ሙን ጋር ወደ ሴዑል ሲመለሱ ኪም ደግሞ ወደ ሰሜን ኮሪያ አቅንተዋል።

ትራምፕና ኪም ተጨባበጡ