የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ600ሺህ ተማሪዎች የደንብ ልብስ ሊያሰፋ ነው

ተማሪዎች Image copyright SEAN GALLUP

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የደንብ ልብስ በነፃ ለማቅረብ በያዘው ዕቅድ መሠረት ተስማሚ የደንብ ልብስ ለማቅረብ ፋሽን ዲዛይነሮች አንዲሳተፉበት አድርጓል።

በዚህም መሰረት በባለሞያዎቹ በቀረቡ የደንብ ልብስ ዲዛይኖችን ለተማሪዎች፣ ለመምህራን፣ ለወላጆች፣ ለሥነ ልቦና ባለሞያዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ ሃሳብ እንዲሰጥበት መደረጉን ከከንቲባው ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከመጪው ዓመት ጀምሮ ወደ 600 ሺ የሚጠጉ ከ400 በላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች የደንብ ልብስ፣ ደብተርና ሌሎች ለትምህርት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ወጪ በከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፈን ተገልጿል።

''የትምህርት ሥርዓቱን ለማገዝ፣ ለነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ለመገንባትና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በማሰብ ነው ይህንን እቅድ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ያስጀመሩት''ብለዋል የከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ፌቨን ተሾመ።

ከዚህ በመነሳት በተለይ በመንግሥት ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች ቤተሰቦችን ሸክም ለመቀነስና ችግራቸውን ለመጋራት የከተማ አስተዳደሩ መወሰኑም ተገልጿል።

አራት ህጻናትን በአንዴ ያገኘው ቤተሰብ ተጨንቋል

በዚህም መሰረት በከተማዋ ያሉት ትምህርት ቤቶች ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ አራት አይነት የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) የሚኖራቸው ሲሆን የአፀደ ህጻናት፣ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል፣ ከአምስት እስከ ከስምንት እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በሚል ተከፋፍሏል።

"ሙሉ ወጪውን የከተማ አስተዳደሩ የሚሸፍነው ከሆነ ወጥ የደንብ ልብሶች መዘጋጀታቸው ሥራውን እንደሚያቀለውና በከተማዋ የሚስተዋለውን የተዘበራረቀ የትምህርት ቤቶች የደንብ ልብስ ለማስተካከል ይረዳል" ብለዋል ፕሬስ ሴክሬታሪዋ።

በሌሎች ሃገራት የሚገኙ ከተሞች ተሞክሮም ከግምት ውስጥ መግባቱንም አክለዋል።

የደንብ ልብሶቹን ተማሪዎች የሚወድዋቸውና ደስ ብሏቸው የሚለብሷቸው እንዲሆኑ ከኢትዮጵያ ፋሽን ዲዛይነሮች ማህበር ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል።

መጠቀም ያቆምናቸው ስድስት የአካል ክፍሎች

''የዲዛይንና የቀለም ምርጫው ባለሙያዎቹ እንዲወስኑት ያደረግነው ከዘመኑ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል እንዲሆን ነው'' በማለት ፌቨን ትናገራለች።

ለአንድ ተማሪ በአማካይ ምን ያህል ብር ያስፈልጋል የሚለው ገና ዲዛይኖቹ ተጠናቀው ሲቀርቡ የሚታወቅ ሲሆን በከተማዋ ላሉት ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎች የደንብ ልብስ ለማሰፋት ትክክለኛ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን እስካሁን ባይታወቅም በግምት እስከ 300 ሚሊዮን ብር ድረስ ሊያስወጣ እንደሚችል ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ይናገራሉ።

ተማሪዎችና ወላጆች የደንብ ልብስ ምርጫቸው የተለያየ የመሆኑ ጉዳይ ከግምት ውስጥ ገብቷል ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ሲመልሱ የእነዚህን ሁሉ ሰዎች ሃሳብ ሊያስታርቅ የሚችል ነገር ይዘው መቅረብ የሚችሉት የዘርፉ ባለሙያ የሆኑት ዲዛይነሮች ስለሆኑ ከባለሙያዎቹ ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

"ሃላፊነቱን ለእነሱ የሰጠነው ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው" ብለዋል።

ለብዙ ዓመታት ማገልገል የሚችል፣ ተማሪዎች የሚወዱትና ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል አይነት ደንብ ልብስ እንደሚሆን የከተማ አስተዳደሩ ተስፋ ያደረገ ሲሆን በመጪዎቹ ሳምንታት የዲዛይን ሥራው ተጠናቆ ለእይታ ይቀርባል።

የከተማዋ የትምህርት ቢሮም ከወላጆች ጋር ውይይት እያደረገ ሲሆን ዲዛይንና ቀለሙ ላይ አስተያየት በመሰብሰብ አብዛኛውን ተማሪና ወላጅ ፍላጎት የሚያሟላ የደንብ ልብስ ይመረጣል።

የሰዎችን ማንነት የሚለየው ቴክኖሎጂ እያከራከረ ነው

''ከዚህ በመቀጠል የሚሆነው የተመረጠውን የደንብ ልብስ በብዛት የማስመረትና ለተማሪዎች የማከፋፈል ሥራ ነው። ይህንን ሥራ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጠናቀን ለመጪው የትምህርት ዘመን ዝግጁ ለማድረግ እየሰራን ነው'' ብለዋል።

''በቀን በመቶ ሺዎች ማምረት የሚችሉ ትልልቅ ፋብሪካዎች ስላሉ ዲዛይኑ ተጠናቆ ተቀባይነት ሲያገኝ ወዲያው አምርቶ መጨረስ ይቻላል'' ብለዋል።

ምንም እንኳን ሃሳቡን ያመጡት ምክትል ከንቲባው ቢሆኑም ሥራው ቀጣይነት እንዲኖረውና በሚቀጥሉት ዓመታት ተግባራዊ ማድረግ እንዲቻል በማሰብ ተቋማዊ መዋቅር ለመዘርጋት እየተሰራበት መሆኑን ፕሬስ ሴክረተሪዋ ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት በከተማ አስተዳደሩ የበጎ ፈቃደኞች ማስተባበሪያ ቢሮ የተቋቀመ ሲሆን ገንዘብ ማሰባሰብና የግሉን ዘርፍ በዚህ አይነት ሥራዎች ውስጥ እንዲሳተፍ የማድረግ ሥራውን ቢሮው በበላይነት የሚመራው ይሆናል።

ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ ለሚገኙ ከ600 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የደብተር ወጪ ለመሸፈን የከተማ አስተዳደሩ ባቀደው መሰረት ከሰባት ሚሊየን በላይ ደብተሮች የሚያስፈልጉ ሲሆን በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ በጎፈቃደኞች፣ ባለሃብቶችና ድርጅቶችን በማስተባበር 3.5 ሚሊየን ደብተሮች ማሰባሰብ ተችሏል።

በቀጣይ ሳምንታት ደግሞ ቀሪዎቹን ደብተሮች በማሰባሰብ ለተማሪዎች የማዳረስ ሥራ እንደሚጀመር ገልጸዋል ፕሬስ ሴክሬታሪዋ።

በአሁኑ ወቅት በጣም ተፈላጊ የሆኑ የዲጂታል ዘርፍ ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?

ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ሲመለሱ ደስ ብሏቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና እንዲነሳሱ በማሰብ ትምህርት ቤቶቹን እንዲታደሱ እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ በመንግሥት የሚተዳደር አዳሪ ትምሀርት ቤት ስለሌላት የቀድሞው እቴጌ መነን ትምህርት ቤት አሁን የካቲት 12 ተብሎ የሚጠራውን ተመልሶ የአዳሪ ትምሀርት ቤት የሚሆን ሲሆን ለሴት ተማሪዎች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል።

አቃቂ የሚገኘው ኢትዮ ጃፓን ትምሀርት ቤት ደግሞ እድሳት ከተደረገለት በኋላ በተመሳሳይ ወንድ ተማሪዎችን ብቻ የሚያስተናግድ አዳሪ ትምህርት ቤት ይሆናል ተብሏል።

በሁለቱም አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ምርጥ 500 ሴትና 500 ወንድ ተማሪዎች የሚማሩባቸው እንደሆነም ታውቋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ