ባለ አምስት ኮከቡ የኖርዌይ እስር ቤት

የጸሎት ቤት Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ በሀልደን እስር ቤት የጸሎት ቤት

የዮጋ አስተማሪዋ ከፊት ለፊት ቆማ «አሁን ደግሞ እስኪ የእግራችሁን አውራጣቶች ሰብሰብ በማድረግ መቀመጫችሁን ወደ ኋላ...1...2...3...በጣም ጥሩ...አሁን ደግሞ ....» ትላለች። 20 የሚሆኑ እስረኞች የዮጋ ምንጣፋቸው ላይ ናቸው። ጥሞና ላይ።

ይህ የዮጋ ሥልጠና በአንድ ሀብታም ሰፈር የተከፈተ ጂም ውስጥ አይደለም ያለው። በኖርዌይ እጅግ ነውጠኛ የሚባሉ ታሳሪዎች የሚቀፈደዱበት ሀልደን ማረሚያ ቤት ውስጥ ነው። 'የሚቀፈደዱበት' የሚለው ቃል ለዚህ ታሪክ እንደማይመጥን የምትረዱት ይህንን ታሪክ አንብባችሁ ስትጨርሱ ነው።

እነዚህ ታሳሪዎች ዮጋ ብቻ ሰርተው ወደየክፍሎቻቸው አይሄዱም። ከዮጋው በኋላ ደግሞ ገና ሳውና ባዝ ይገባሉ። እንዲህ የሚቀማጠሉት ታዲያ ሴት የደፈሩ፣ የሰው ነፍስ ሲጥ ያደረጉ፣ አደገኛ እጽ ያዘዋወሩ የአገር ጠንቅ የነበሩ መሆናቸው ነው።

አብረዋቸው ከሚሰሩት መሀል ደግሞ ጠባቂዎቻቸው ይገኙበታል።

"ዮጋ ሲሰሩ ይረጋጋሉ" ይላል ሆይዳል የተባለው የእስር ቤቱ አለቃ።

"እዚህ ቦታ ቁጣና ነውጥ አንሻም፤ እዚህ ሰላምና እርጋታ ነው የሚያሻን፤ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው" ይላል።

ሰላምና መረጋጋት እንዲሁ ዝምብሎ የሚመጣ ነገር አይደለም። ዋጋ ያስከፍላል። የዚህ የኖርዌይ እስር ቤት ዓመታዊ ወጪ ለምሳሌ እጅግ ውድ ነው። 98 ሺህ ፓንድ። ይህ ብዙ ቁጥር ነው። በእንግሊዝ የአንድ እስር ቤት ዓመታዊ ወጪ በአማካይ ከ40ሺህ ፓውንድ አይበልጥም።

በግቢው ስንዘዋወር አንድ የእስረኞች ጠባቂ ስኩተር የምትባለዋን ብስክሌት እየነዳ ሲያልፍ ፈገግታን መገበን። ከርሱ ጎን ደግሞ ሁለት እስረኞች በቁምጣ ዱብ ዱብ ይላሉ። በፍጹም የአዳኝ ታዳኝ ወይም የወንጀለኛና የጠባቂ ግንኙነት የላቸውም።

እስር ቤቱን እያስጎበኘን የነበረው የግቢው አለቃ በኔ የመደነቅ ፊት ተደንቆ ሳቁን ለቀቀው። እኔ ግን የማየው ሁሉ አግራሞትን ፈጥሮብኝ ፈዝዤ አለሁ።

አጭር የምስል መግለጫ የእስር ቤቱ አለቃ

"ይህንን ዳይናሚክ ጥበቃ ብለን እንጠረዋለን" አለኝ። ምን ማለት ነው?

እስረኞችና ጠባቂዎቻቸው በሁሉም እንቅስቃሴዎች አብረው ናቸው። ጓደኛሞች ወዳጆች ናቸው። አብረው ይበላሉ። የእጅ ኳስ እና ቅርጫት ኳስ አብረው ይጫወታሉ፤ ስፖርት አብረው ነው የሚሠሩት ወዘተ። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንዲቀራረቡ ያደርጋቸዋል።

የጄል ኦጋዴን እስር ቤት ኃላፊ ተይዞ ለኢትዮጵያ ተሰጠ

የእስር ቤቱ አለቃ ሆይዳል ሥራ የጀመረው በ1980ዎች አካባቢ ነበር። ያኔ ነገሮችን እንዲህ እንዳልነበሩ ያስታውሳል። "ያኔ ይገርመኻል በጉልበት ነበር የምናምነው። ታራሚዎችን እንደ ወንጀለኛ ነበር የምንቆጣጠራቸው፤ እናም እስረኞች ከተፈቱ በኋላም በሌላ ወንጀል ተመልስው ጥፋተኛ የመሆን አዝማሚያቸው ከ60 እስከ 70 በመቶ ደረሰ። ልክ እንደ አሜሪካ።"

የእስር ቤቱ አለቃ ነገሮችን መቼ መቀየር እንደጀመሩ ይናገራል።

ከ1990ዎቹ ወዲህ አዲስ ፍልስፍና መከተል ጀመረች ኖርዌይ። ጥፋተኞችን ከመቅጣትና ከመበቀል ወደ ማለዘብና ማረም ተሸጋገረ። ቀድሞ አንድ ክፍል ውስጥ ተቆልፎባቸው ይውሉ የነበሩ እስረኞች ለተከታታይ መዝናኛ፣ ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲጋበዙ መልካም ዜጋ መሆን ጀመሩ።

በዚህ እስር ቤት የእስረኛ ጠባቂዎችም ራሳቸውን እስረኛ አዳኝና ተቆጣጣሪ አድርገው አያስቡም። ወዳጆች ናቸው። ልክ እንደ ሆስፒታል ነርስ ጠባቂ እስረኛን ይንከባከባል። "እኛ ምሳሌ መሆን ነው የምንፈልገው። እውነተኛ ወዳጅና አማካሪዎቻቸውም ነን" ይላል የእስረኞቹ አለቃ።

Image copyright Reuters

የዪኒቨርስቲ ካምፓስ ወይስ እስር ቤት?

የእስር ቤቱ ሥነ ሕንጻ ገጽታም ቢሆን ከኑሮና ከኅብረተሰቡ የተገለለ፣ ማጎሪያ እንዳይመስል ብዙ ተለፍቷል። እስረኞቹ ራሳቸውን ታሳሪ አድርገው እንዳያስቡ ከአንድ ሰፈር ጋ ጎረቤት ሆነው ነው ያሉት። እንዲያውም እስር ቤቱን ዲዛይን የሰራው ድርጅት 138 ሚሊዮን ፓውንድ ቢያስከፍልም ቀላልና ምቹ እስር ቤት በማነጹ ተከታታይ ዓለማቀፍ ሽልማቶችን አግኝቷል።

በእንጆሪ ዛፎች፣ በውብ አበቦች፣ በወይን ተክል የተከበበው ይህ እስር ቤት ያሳሳል። ኑሩብኝ ኑሩብኝ ይላል። ከእስር ቤትነት ይልቅ ለዪኒቨርስቲ ካምፓስነት ይቀርባል።

"ያሻችሁን ብሉ፣ ጠጡ፣ አጭሱ" ጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ

በግላጭ የሚታይ አንድም የኤሌክትሪክ አጥርም ሆነ አዳኝ ካሜራ የለም። የእስረኞችን እንቅስቃሴ የሚከታተል ሴንሰር ዲቴክተር ግን አለ። የእስር ቤቱ አለቃ እንደነገረኝ አንድም ሰው ለማምምለጥ ሞክሮ አያውቅም።

የእስረኞች ማደሪያም ቢሆን መጠነኛ የሆቴል ክፍል እንጂ ማጎሪያን አይመስልም። የራሱ ሻወር-ሽንት ቤት፣ ቅንጡ ቴሌቪዥን ጠረጴዛና ወንበር እንዲሁም ወደሚያምረው ለምለምና አረንጓዴ መስክ የሚያሳየው መስኮት ይገኛል። በጋራ መጠቀሚያ ኮሪደሩ በኩል ደግሞ ሁሉን የሟላ ማብሰያ ክፍል አላቸው።

"ይሄ ቅንጦት ግን አልበዛም?" አልኩት፤ የእስረኞቹን አለቃ

"የበዛ ሊመስልህ ይችላል። ሆኖም ነጻነትን መነጠቅ ቀላል ነገር አድርገህ አትየው። በኖርዌይ ትልቁ ቅጣት ነጻነትን መነጠቅ ነው። ሌሎች መብቶችህ ግን አብረውህ ይኖራሉ። ለምሳሌ የመምረጥ፣ ትምህርትና ጤና አቅርቦት እና ማንኛውም ኖርዌጂያዊ የሚያገኛቸውን ጥቅሞች እስረኞችም ያገኛሉ። አጥፍተው በመታሰራቸው የሚያጡት ነጻነትን ብቻ ነው። ይህ ቅጣት ደግሞ ለሰው ልጅ ትልቁ ቅጣት ነው።"

አጭር የምስል መግለጫ እስረኞች የሚሰሩበት ጋራዥ

ጋራጅ፣ የሙዚቃ ስቱዲዮና ዲዛይን ክፍሎች

ጋራዥ ስገባ ሁለት እስረኞች የጋራጅ ቱታቸውን ለብሰው ተፍ ተፍ ይላሉ። አንዲት ፔዦ መኪናን ይፈታታሉ። ብሎን ያጠብቃሉ፤ ያላላሉ። እንደ ሁሉም እስረኞች ከክፍላቸው ወደ ሥራ የሚወጡት ጠዋት 1፡30 ላይ ነው። ከዚያ በኋላ ለአንድ ሰዓት እረፍት ወደ መኝታቸው ይሄዳሉ። ከዚያ በኋላ ተመልሰው ጋራዥ ውስጥ መሥራት ነው። እስከ ማታ 2፡30 ድረስ። በቃ ልክ ውጭ የሚኖሩትን ዓይነት ሕይወት ነው የሚመሩት። እዚህ ጋራጅ ብቻ ሳይሆን እንጨት መሰንጠቂያ፥ የቢሮና የቤት እቃ ማምረቻ ዎርክሾፕ፣ የሙዚቃ ስቱዲዮ፣ የግራፊክስ ስቱዲዮና ሌሎችም በርካታ የሥራ መስኮች አሉ።

"ከኅብረተሰቡ የሚቀላቀሉበትን ሁኔታ ማሰብ የምንጀምረው ገና ተፈርዶባቸው ወደ እስር ቤት የመጡ እለት ነው" ይላል የእስር ቤቱ አለቃ።

በኖርዌይ የሞት ቅጣት የለም።

ሁሉም ታሳሪ ፍርዱን ሲጨርስ ይፈታል። ስለዚህ ከእስር ቤት ወጣሁ የሚል ስሜት የለም። ወደ ጎረቤት የመሄድ ያህል ነው የሚሰማቸው። "ታሳሪዎቹን ልክ እንደ እንሰሳ ብናንገላታቸው ሲወጡም እንደዚያው ነው የሚሆኑት፤ ስለዚህ እንደ ሰው እንከባከባቸዋለን፤ ሰው ሆነው ኀብረተሰቡን ይቀላቀላሉ" ይላል።

አጭር የምስል መግለጫ ፍሬድሪክ እስር ቤቱ ሆኖ ለጻፈው መጽሐፍ እስር ቤት ዲዛይን ትምህርት ወስዶ የሰራው የሽፋን ገጽ

15 ዓመት የተፈረደበት ፍሬድሪክ በዲዛይን ክፍል ቁጭ ብሎ በቅርቡ ለሚያሳትመው የምግብ አበሳሰል መጽሐፍ የሚሆን የሽፋን ዲዛይን ሰርቷል። የእስር ቤት ቆይታዬ ከራሴ ጋር እንድታረቅ አድርጎኛል ይላል። በግራፊክ ዲዛይን ዲፕሎማውን ያገኘው እዚሁ እስር ቤት ውስጥ ነው።

አጭር የምስል መግለጫ የእስረኞች የጋራ ክፍል

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ