"ኢትዮጵያዊነቴን ያገኘሁት ሙዚቃ ውስጥ ነው" አቨቫ ደሴ

አቨቫ Image copyright Alamy

ከ35 ዓመት በፊት ወደ ሱዳን ከተሰደዱ ብዙ ሺህ ኢትዮጵያዊያን መካከል አራት ልጆች ያሏቸው ጥንዶች ይገኙበት ነበር። ሱዳን ውስጥ ወደሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ለመድረስ ለሳምንታት በእግር ተጉዘዋል። መጠለያው ውስጥ በቂ ምግብና መድሀኒት አልነበረም።

ውጣ ውረዱ የብዙዎችን ሕይወት እንደዋዛ ቀጥፏል። ጥንዶቹም በስደት ላይ ሳሉ ከልጆቻቸው ሁለቱን በሞት ተነጥቀዋል። ኢትዮጵያዊያኑ መጠለያ ውስጥ ለወራት ከቆዩ በኋላ "ኦፕሬሽን ሞሰስ" [ዘመቻ ሙሴ] በተባለ ዘመቻ ወደ እስራኤል ተወሰዱ። ይህም ኢትዮጵያዊያን አይሁዶች ወደ እስራኤል ከተወሰዱባቸው ዘመቻዎች አንዱ ነበር።

ተፈራ ነጋሽ፡ "በነገራችን ላይ ሙዚቃ አልተውኩም"

ጥንዶቹ ይመኟት የነበረውን የእስራኤል ምድር ከረገጡ በኋላ ሕይወትን 'ሀ' ብለው ጀመሩ። ናዝሬት ከተማ ውስጥ። እስራኤል በደረሱ በአራተኛው ዓመት አቨቫ የተባለች ልጅ ተወለደች።

አቨቫ ደሴ።

"በፀጉሬ ይስቁብኝ ነበር"

አቨቫ ያደገችው ኢትዮጵያዊያን በብዛት በሚኖሩበት መንደር ነው፤ ጓደኞቿም ኢትዮጵያዊያን ነበሩ። እስራኤል ለኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ለሌሎች ጥቁሮችም ምቹ አገር አለመሆኗን የተገነዘበችው ትምህርት ቤት ስትገባ ነበር።

Image copyright Ilya Melnikov

የምትማርበት ክፍል ውስጥ የነበሩት ተማሪዎች ነጮች ብቻ ነበሩ። በቆዳ ቀለሟ ይጠቋቆሙ፣ በባህሏ ይሳለቁ፣ በፀጉሯም ይስቁ ነበር። በእስራኤላዊያን ዘንድ ተቀባይነት ባለማግኘቷ ኢትዮጵያዊ ማንነቷን ጠላችው። እስራኤላዊያንን ለመምሰል ትጣጣርም ጀመር።

"አሁን ስናገረው ያሳፍረኛል፤ ግን ልጅ ሳለሁ በቤተሰቦቼ አፍር ነበር፤ የቤተሰቤን ጉዞና ታሪክ ረስቼ ነበር" ትላለች።

አቨቫ እንጀራ አትበላም ነበር። ጓደኞቿ በኢትዮጵያዊነቷ የሚሳለቁባት ስለሚመስላት ወደ ቤቷ ልትጋብዛቸው አትፈልግም።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ከነበሯት መምህራን አንዷን እንዲህ ታስታውሳታለች።

የኤርትራ ዘፈኖች በኢትዮጵያዊ አቀናባሪ

"ከነጭ ጓደኞቼ ጋር ስሆን መምህርቷ በጣም በትህትና ሰላም ትለናለች። ከኢትዮጵያዊያን ጓደኞቼ ጋር ስታየኝ ግን እንደ ነጮቹ በትህትና አታዋራንም፤ ትጮህብን ነበር።"

"ወደ ማንነቴ የተመለስኩት በሙዚቃ ነው"

አቨቫ ሙዚቃ ነፍሷ ነው።

ከአራት ታላላቅ እህቶቿ አንዷ የአርኤንድቢ እና ሶል ሙዚቃ ቪድዮ ካሴቶች ታሳያት ነበር። ቤት ውስጥ ታንጎራጉራለች፤ ትደንሳለች። አይን አፋር ስለነበረች ከቤት ውጪ ባታደርገውም። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ሙዚቃ መጻፍ ጀመረች፤ ነገር ግን ለማንም አታሳይም ነበር።

የእስራኤል ወጣቶች ወታደራዊ ግዴታ መወጣት ይጠበቅባቸዋልና አቨቫም ድንበር አካባቢ ተመደበች።

Image copyright Harel Dahari

"የተሳሳተ ቦታ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። አገሪቱን ከወታደራዊ አገልግሎት በሌላ መንገድ ማገልገል እንደምችል አምናለሁ። በእርግጥ በወቅቱ ስለ ራሴ ተምሬያለሁ።"

ያኔ ሙዚቃ እንዲሁ የሚያስደስታት ነገር እንጂ፤ ከዚያ በዘለለ የሕይወቷ ጥሪ እንደሆነ አታስብም ነበር። እንዲያውም ሥነ ልቦና ማጥናት ነበር ምኞቷ። ሆኖም አንድ ክፉ አጋጣሚ ሕይወቷን እስከወዲያኛው ቀየረው።

ከባድ የመኪና አደጋ!

ከአደጋው ለማገገም ወደ ሁለት ዓመት ገደማ ወስዶባታል። በእነዚያ ዓመታት ስለ ሕይወት ስታሰላስል "መኖር ያለብኝ የምወደውን ነገር እየሠራሁ ነው" ከሚል ውሳኔ ላይ ደረሰች።

''አዝማሪዎቻችን የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ናቸው"

"ዘ ቮይስ" የተባለው ታዋቂ የሙዚቃ ውድድር እስራኤል ውስጥ ሲጀመር ተቀላቀለች። ውድድሩ ላይ የአንድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ኃላፊ ተዋውቃ ነበር። ትምህርት ቤቱ ገብታም የጊታርና የድምፅ ትምህርት መውሰድ ጀመረች።

በሙዚቃ ትምህርት ቤቱም ስለ "አፍሮ ፖፕ" ስልት ስትማር ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃም ሰማች።

ችላ ካለችው ኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር በሙዚቃ ታረቀች።

"ወደ ማንነቴ ያደረኩት ጉዞ የተጀመረው በሙዚቃ ነው። ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ መማር ጀመርኩ። ስለ ኢትዮጵያ ባህል ማጥናትና አማርኛ መለማመዱንም ተያያዝኩት። ጊዜ ቢወስድብኝም ቤቴ የምለው አገር እንዳለኝ ተገነዘብኩ። የወላጆቼን ሙዚቃ ወደድኩት።"

አቨቫ አሁን 31 ዓመቷ ነው። ሦስት አልበሞች አሳትማለች። "ኢን ማይ ቶውትስ" [በሀሳቤ]፣ "ሁ አም አይ" [ማነኝ?]፣ "አይ አም አቨቫ" [አቨቫ እባላለሁ] የተሰኙ።

ሙዚቃዎቿ ዘረኝነትን የሚያወግዙ፤ ፍቅርና ሰላምን የሚሰብኩ ናቸው።

"የሚያክሙን ሙዚቃዎች እንዳሉ ሁሉ የሚያውኩንም አሉ" ዶ/ር መልካሙ

ከኢትዮጵያ ሙዚቃና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከሆነ ነገር ጋር በፍቅር ወድቄያለሁ የምትለው አቨቫ፤ በሙዚቃዋ የአማርኛ ስንኞች ታካትታለች፤ ዘፈኖቿን በመሰንቆና ክራር ታጅባለች። ቪድዮ ክሊፕ ስትሠራ የአገር ባህል ልብስ ለብሳ፣ ሹሩባ ተሠርታም ነው።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ጎብኝታለች። ሸራተን አዲስ በነበረ የሙዚቃ ትርዒትም ተሳትፋለች።

የጥላሁን ገሠሠ፣ የመሀሙድ አህመድ፣ የጂጂ (እጅጋየሁ ሽባባው) እና የቴዲ አፍሮ (ቴዎድሮስ ካሳሁን) ሙዚቃዎችን ታቀነቅናለች።

በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ሳለች የጂጂን ዘፈን ዳግመኛ ሠርታ እንጦጦ ተራራ ላይ ቪድዮ ክሊፕ ሠርታለች። "ፍቅሬ ሆይ እኔ አንተን መውደዴን እንዴት ብዬ ልተው. . . " አቨቫ ራሷን በጊታር አጅባ የምታዜመው ዘፈን ነው።

ሶል፣ አርኤንድቢና የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሦስት የምትወዳቸው ስልቶች ናቸው። ሶል እና አርኤንድቢ ውስጥ መሰንቆና ክራር ብዙም አለመለመዱ ሥራዎቿን ተወዳጅ እንዳደረጋቸው ታምናለች።

"ጥቁር ስለሆንሽ እልወድሽም"

ዘረኛነት በተንሰራፋበት ማህበረሰብ ውስጥ መኖር፣ የራስን ማንነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባትና በስተመጨረሻም ከራስ ጋር መታረቅ ለአቨቫ ሙዚቃ ግብዓት የሆኑ የሕይወት ተሞክሮዎች ናቸው።

ከተሞክሮዎቿ አንዱን እንዲህ ታወሳለች።

"ከጥቂት ዓመታት በፊት መዋዕለ ህጻናት ውስጥ ሠርቼ ነበር። ሁሉም ህጻናት ነጭ ነበሩ። ልጆቹን ባጠቃላይ ወድጃቸው ነበር። አንድ ቀን አንድ አስተማሪ ልጆቹ ወደ ክፍል እንዲገቡ እንድጠይቃቸው ነገረኝ። ተማሪዎቹን ስጠራቸው አንድ ልጅ ወደ ውስጥ መግባት አልፈለገም ነበር። ከዚያ አናገርኩት. . . 'እንደምወድህ ታውቃለህ አይደል?' ስለው 'እኔ ግን አልወድሽም' አለኝ? 'ለምን?' ስለው 'ጥቁር ስለሆንሽ' አለኝ። ልጁ አምስት ዓመቱ ነበር፤ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን አልተዋወቀም። ግን ጥላቻን ተምሮ ነበር። ከጥቂት ወራት በኋላ ከልጁ ጋር ወዳጆች ሆንን። የተናገረውን ነገር ትርጉሙን ተረድቶና ሆነ ብሎ እንዳላላው አውቃለሁ።"

ይህ ማህበረሰቡ እንዴት እንደሚያስብ ካየችባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ነበር። ከማርቲን ሉተር ኪንግ ንግግሮች አንዱን እንደ መነሻ አድርጋ "ብላክ" [ጥቁር] የተሰኘ ሙዚቃ የጻፈችውም በዚህ ምክንያት ነበር።

"ራሴን የምፈርጀው የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው" አሊ ቢራ

በሙዚቃዎቿ ስለ ቤተሰቦቿ ሕይወትም ታወሳለች። ልጅ ሳለች እናቷ ይነግሯት ከነበረው ታሪክ ተነስታ ስለ ቤተሰቦቿ የትውልድ ቀዬ እንፍራዝ ዘፍናለች።

"ሙዚቃ ሕክምና ነው"

ሀሳቧን፣ ቢሆን ብላ የምትመኘውንም በሙዚቃዎቿ ታስተላልፋለች።

"ውስጤ የሚንቀለቀሉና ማውጣት እንዳለብኝ የሚሰሙኝ ስሜቶችን በሙዚቃ እገልጻቸዋለሁ። ሙዚቃ መጻፍ ሕክምና ነው። ብዙዎቹ ዘፈኖቼ ስለ ውጣ ውረድ ይናገራሉ። መልስ ለማግኘት ያለሙም ናቸው።"

"አይ ዋነ ጎ" [መሄድ እፈልጋለሁ] እናቷን አጥታ ግራ ስለተጋባች ትንሽ ልጅ ይተርካል።

በፍቅር ከፍታ ውስጥ ሳለሁ የጻፍኩት የምትለው "ማይ ኸርት" [ልቤ] የተሠራው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ምት፣ እስክስታ ተጨምሮበት ነው።

Image copyright Teddy Afro

አቨቫ ማየት የምትፈልገውን እኩልነት የሰፈነበት ዓለም በሙዚቃዎቿ ታስተጋባለች።

"ሰውን በአካል ማጥቃት ብቻ ሳይሆን ዘረኛ ንግግርም ያማል። 'ኢትዮጵያዊያን ባጠቃላይ ጥሩ ናችሁ' ይባላል። ነገር ግን እኛ አንድ ሰው አይደለንም። የተለያየ ባህሪ አለን። በሙዚቃዬ ማሳየት የምፈልገውም ይህንን ነው።"

"ከለር" [ቀለም] የተባለ ዘፈኗ ሁለት የተለያዩ ሰዎች፤ አንዳቸው ሌላቸውን ለመቀየር ሳይሞክሩ በመቻቻል ስለሚኖሩበት ዓለም ይተርካል።

የእስራኤል ማህበረሰብ ኢትዮጵያዊያንን እንዳሉት ባለመቀበሉ ራሷን ለመቀየር መሞከሯን ታስታውሳለች።

"እስራኤላዊ ከመሆንና ኢትዮጵያዊ ከመሆን መካከል መምረጥ እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር። ሁለቱንም መሆን እንደምችል፣ መደበቅ ሳይሆን መኩራት እንዳለብኝ ለመረዳት ዓመታት ወስዶብኛል። እስራኤል የብዙ ባህሎች አገር ናት። ይህም ውብ ነው። ሰዎችን ለመቀየር መሞከሩን ትተን በመከባበርና በመፈቃቀር መኖር አለብን።"

"መንግሥት ለኛ ቅድሚያ አይሰጥም"

ኢትዮጵያዊያን በእስራኤል ፖሊሶች የሚደርስባቸውን ጥቃት በመቃወም በርካታ ሰልፎች ተደርገዋል። በትምህርትና በሥራው ዘርፍ ያለውን መድልዎ በመቃወምም በርካቶች ድምጻቸውን አሰምተዋል። ሆኖም ይህ ነው የሚባል ለውጥ የመጣ አይመስልም።

ከሳምንታት በፊት ሰለሞን ተካ የተባለ ቤተ እስራኤላዊ ሥራ ላይ ባልነበረ ፖሊስ መገደሉ ይታወሳል። ከዚህ ቀደም ከታዩ የተቃውሞ ሰልፎች በተለየ ጠንካራ ተቃውሞ ተካሂዶ ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች ተዘግተውም ነበር።

"የተቃውሞ ሰልፍ ሲካሄድ 'ወደ ኢትዮጵያ መልሷቸው የሚሉ አሳዛኝ መልዕክቶች አያለሁ። በጣም የከፋ ደረጃ ላይ እንደደረስን ይሰማኛል። ህመሙና ተስፋ መቁረጡን እረዳለሁ። በፖሊስ ጭካኔ ምክንያት በተለይ ኢትዮጵያዊያን ወንዶች መንገድ ላይ ለመሄድ እንኳን ይፈራሉ። ለሕይወታቸው እየታገሉ ነው። ለብዙ ጊዜ የታመቀ ቁጣ ነው የገነፈለው" ትላለች ሙዚቀኛዋ።

መዋዕለ ህጻናት ኢትዮጵያዊያን ህጻናትን መቀበል አይፈልጉም። በሥራ ቦታም ኢትዮጵያዊያን እንደሚገለሉ ትናገራለች።

ሁሌም የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ መንግሥት 'ለውጥ ይመጣል' ብሎ ቃል ቢገባም አንዳችም መሻሻል እንዳላዩ ትገልጻለች። መንግሥት ለጥያቄዎቻቸው መልስ የማይሰጠው ለኢትዮጵያዊያኑ ጉዳይ ቅድሚያ ስለማይሰጥ እንደሆነም ታክላለች።

"ቤተሰቦቼ እስራኤል ከመጡ ጀምሮ ስለዚህ ነገር ይወራል። ያኔም ተቃውሞ ነበር፤ አሁንም አለ። የተለወጠ ነገር ግን የለም።"

ሆኖም ተስፋ አልቆረጠችም። ነገሮች የተሻሉ እንደሚሆኑም ትጠብቃለች።

"ሙዚቃዬ ሩስያ መድረሱን አላወኩም ነበር"

እስራኤል ውስጥ ኢትዮጵያዊያን ሙዚቀኞች መበራከታቸው ማህበረሰቡ ስለ ቤተ እስራኤላዊያን ባህል እንዲረዳ እንደሚያግዝ ታምናለች። ሙዚቃቸው አሁን ካለበት በላይ እንደሚያድግም ተስፋ ታደርጋለች።

ከኢትዮጵያዊያንና ከእስራኤላዊያን አድማጮቿም ጥሩ ምላሽ እያገኘች እንደሆነ ትናገራለች።

"ራሴን የምፈርጀው የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው" አሊ ቢራ

"ማኅበራዊ ጉዳዮችን ስዳስስ ድምፅ እየሆንኳቸው እንደሆነ አምናለሁ። ቤተሰቦች 'ለልጆቻችን አርዓያ ነሽ' ሲሉኝ በጣም እኮራለሁ። ምክንያቱም በኔ ትውልድ ብዙም ስኬታማ ጥቁር ሴት አርዓያ የለንም።"

አቨቫ በሙዚቃ ሕይወቷ እጅግ ከኮራችባቸው ቅጽበቶች አንዱ የገጠማት ሩስያ ሳለች ነው።

አንድ ፌስቲቫል ላይ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች ነበሩ። የድምፅ ሙከራ ስታደርግ ሰዎች አብረዋት ይዘፍኑ ነበር. . .

"ምን?!. . . በጣም ነው የገረመኝ. . . ሙዚቃዬ ሩስያ መድረሱን አላወኩም ነበር". . .

ሙዚቃ ስትጀምር ቤተሰቦቿ እምብዛም አይደግፏትም ነበር። ዛሬ ግን ከትርዒቶቿ አይቀሩም። ልጅ ሳለች እናቷ ያንጎራጉሩላት እንደነበር ታስታውሳለች። አንድ ቀን ከእናቷ ጋር በጥምረት የመሥራት ምኞትም አላት።

Image copyright Aveva

በአንድ ወቅት ኢትዮጵያዊነት ትርጉም የማይሰጣት አቨቫ ዛሬ ትልቁ ህልሟ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙዚቃዎቿን ማቅረብ ነው።

እናቷ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ከአንድም ሁለት ሥራ እየሠሩ እንዳሳደጓቸው ታስታውሳለች። በአንድ ወቅት ይህንን ባትገነዘብም አሁን ላይ ተቀይራለች።

"አሁን ትልቅ ሴት ሆኜ ሳየው ቤተሰቦቼ ጀግኖቼ ናቸው። እናቴ ጀግናዬ ናት። በጣም እኮራባታለሁ።"

እስራኤል ውስጥ ያለውን መደልዎ በመቃወም ሰልፍ ሲካሄድ እናቷን ተመሳሳይ ጥያቄ ትጠይቃለች።

"እዚህ በመምጣታችሁ ደስተኛ ናችሁ?"

እናቷ ሁሌም የሚሰጧት መልስ ተመሳሳይ ነው።

"ቦታዬ እዚህ ነው፤ ሌላ ቦታ መኖር አልፈልግም፤ ብዙ ውጣ ውረድ ቢኖርብንም እዚህ በመኖሬ እኮራለሁ።"

ተያያዥ ርዕሶች