በክረምት ሲዘንብ የመሬት ሽታ ለምን ያስደስተናል?

የዝናብ ጠብታ Image copyright Science Photo Library

ክረምትም አይደል? አገሪቱ በዝናብ ርሳለች። ለመሆኑ ዝናብ ሲጥል ያለው ሽታ ለምን ደስ እንደሚልዎ ያውቃሉ?

ለወራት ዝናብ አጥቶ የደረቀ መሬት በዝናብ ሲርስ ደስ የሚለንና ሽታው የሚያውደን ያለምክንያት አይደለም። ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ ባክቴሪያ፣ እፅዋትና ብርሀን ተደማምረው ዝናብ ሲጥል ደስ የሚል ሽታ እንዲፈጠር ያደርጋሉ።

ደስታን አጥብቀን ስለፈለግን ለምን አናገኘውም?

ዝናብ ሲጥል ያለው አስደሳች መአዛ 'ፐትሪኮር' ይባላል። ሽታው ዘለግ ላለ ጊዜ ይቆያል። ይህም የተመራማሪዎችና የሽቶ አምራቾችንም ቀልብ ገዝቷል።

'ፐትሪኮር' የሚለውን ስም ያወጡት ሁለት አውስትራሊያውያን ተመራማሪዎች ናቸው። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1960ዎቹ ገደማ።

ባክቴሪያ

ዝናብ ደረቅ መሬት ሲነካ የሚፈጠረው ሽታ ምክንያቱ ባክቴሪያ ነው።

ፕሮፌሰር ማርክ በተር እንደሚሉት፤ ዝናብ ሲዘንብ ብዙዎች በተለምዶ "መሬቱ ሸተተኝ" የሚሉት ባክቴሪያ ሞለኪውል ሲሠራ ያለውን ጠረን ነው።

የዓለማችን 'ጭንቀታም' እና 'ደስተኛ' ሃገራት ደረጃ ይፋ ሆነ

ይህ ሞለኪውል (ጂኦዝሚን) ጤናማ አፈር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ ጸረ ባክቴሪያ (አንቲባዮቲክ) ለመሥራትም ያገለግላል።

ጠብታ ውሀ መሬት ሲነካ ጂኦዝሚን አየር ውስጥ ይለቀቃል። ዝናብ ሲዘንብ ደግሞ የሽታው መጠን ይንራል። ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ሰዎች በቀላሉ ሽታው ያውዳቸዋል።

በ1960ዎቹ ሕንድ ውስጥ እጣን ለመሸጥ ይህ ሽታ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። አሁንም ሽቶ አምራቾች ከጂኦዝሚን ሽቶ ይሠራሉ።

ሽቶ አምራቿ ማሪና ባርሴኒላ "ዝናብ ደረቅ መሬትን ሲነካ ያለው ሽታ ድንቅ ሽቶ ይወጣዋል፤ ከብዙ ንጥረ ነገር ጋር ቢዋሀድ እንኳን ሰዎች ሽታውን ይለዩታል" ትላለች።

ፍየሎችም «ከፍትፍቱ ፊቱ» ይሉ ይሆን?

'ፐትሪኮር' በግሪክ ቋንቋ በአማልክት የደም ሥር የሚዘዋወር ፈሳሽ የሚል ትርጓሜ አለው።

Image copyright Science Photo Library

እፅዋት

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ የእፅዋት መአዛ ከጂኦዝሚን የሚመነጭ ሊሆን ይችላል። ዝናብ ሲዘንብም ሽታው ጎልቶ ይወጣል።

ፕሮፌሰር ፊሊፕ ስቴቨንሰን የተባሉ ተመራማሪ እንደሚሉት፤ እፅዋት ጥሩ ሽታ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ንጥረ ነገር የሚመነጨው በእፅዋት ቅጠል ውስጥ ነው። ዝናብ ይህንን ንጥረ ነገር የሚያጠፋበት እድል እንዳለ ሁሉ፤ የደረቁ እፅዋትን አርሶ ኬሚካል እንዲያመነጩ ያደርጋል።

ዝናብ ሲጠፋ የእፅዋት ሜታቦሊዝም ይጓተታል። ሲዘንብ ሂደቱ ይታደስና እፅዋቱ አስደሳች ሽታ ይፈጥራሉ።

ብርሀን

በዝናብ ወቅት የሚከሰት መብረቅ፤ ልዩ ሽታ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል። ከመብረቁ የሚወጣው ብርሀን የሚፈጥረው ንጥረ ነገር አየር ውስጥ ሲሰራጭ የሰው ልጆችን የሚያስደስት ሽታ ይፈጥራል።

ፕሮፌሰር ማርቢት ስቶልዝበርግ፤ መብረቅ፣ ከመብረቅ የሚፈጠረው ብርሀንና ዝናቡ በጋራ የአየሩን ሽታ ይለውጡታል። አቧራ ተወግዶም በንጹህ አየር ይተካል።

እንግዲህ ተመራማሪዎች ዝናብ ሲዘንብ የሚፈጠረው ሽታ የሚያስደስታችሁ በባክቴሪያ፣ በእፅዋትና በብርሀን ምክንያት ነው ብለዋል። ይህን መረጃ ካገኙ በኋላ ክረምትን በተለየ ሁኔታ ያጣጥሙት ይሆን. . .