"ትራምፕን ከቁብ አትቁጠሩት" አራቱ የኮንግረስ አባላት

ከግራ ራሺዳ ቲላብ፣ አያና ፕረስሊ፣ ኤልሀን ኦማር እና አሌክሳንድያ ኦስካዝዮ-ኮርቴዝ Image copyright AFP/Getty

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዘረኛ የትዊተር መልዕክት ጥቃት ያደረሱባቸው አራቱ የኮንግረስ አባላት የፕሬዘዳንቱን ንግግር አጣጥለዋል።

አራቱ ሴት የኮንግረስ አባላት የትራምፕ ንግግር "የሰዎችን ትኩረት ከጠቃሚ ነገር ለማሸሽ ያለመ ነው" ብለዋል።

ራሺዳ ቲላብ፣ አያና ፕረስሊ፣ ኤልሀን ኦማር እና አሌክሳንድያ ኦስካዝዮ-ኮርቴዝ ትላንት በሰጡት መግለጫ፤ አሜሪካውያን የትራምፕን ንግግር ከቁብ እንዳይቆጥሩት አሳስበዋል።

ትራምፕ አራቱ ሴት የኮንግረስ አባላት አሜሪካውያን ቢሆኑም "አገሪቱን ለቀው መሄድ ይችላሉ" ማለታቸው ይታወሳል። በርካቶች ፕሬዘዳንቱን በንግግራቸው ቢያብጠለጥሏቸውም፤ ትራምፕ "ንግግሬ ዘረኛ አይደለም" ሲሉም አስተባብለዋል።

በባህር ዳሩ የተኩስ ልውውጥ ሦስት ሰዎች ሞቱ

"ዘ ስኳድ" በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩት አራቱ ሴቶች፤ የአሜሪካውያን ትኩረት ፖሊሲ ላይ እንጂ የፕሬዘዳንቱ ንግግር ላይ እንዳይሆን አሳስበዋል።

"ርህራሄ አልባና ሙሰኛ የሆነ አስተዳደሩ ላይ ሰዎችን ትኩረት እንዳያደርጉ ፈልጎ ነው" ብለዋል አያና ፕረስሊ።

ራሺዳ ቲላብ እና ኤልሀን ኦማር ትራምፕ በሕግ ተጠያቂ ይደረጉ የሚለውን ጥያቄ አስተጋብተዋል።

ሦስቱ ሴቶች የተወለዱት አሜሪካ ውስጥ ሲሆን፤ ኤልሀን ኦማር ሶማሊያ ውስጥ የተወለዱ አሜሪካዊ ናቸው። ትራምፕ ያሳለፍነው እሁድ "ወደ መጡበት ተመልሰው በወንጀል የተመሳቀለ አገራቸውን ያሻሽሉ" ሲሉ ዘረኛ ትዊት ማድረጋቸው ይታወሳል።

"የመጀመሪያውን ድራማ አንተ፤ ሁለተኛውን እኔ እፅፈዋለሁ" ኤርሚያስ አመልጋ

አያና ፕረስሊ፤ የኮንግረስ አባላቱን ለማግለልና ድምጻቸውን ለማፈን የተቃጣ ንግግር እንደሆነ ገልጸው፤ "እኛ ከአራት ሰዎች በላይ ነን፤ ቡድናችን ፍትህ የሰፈነበት አገር ለመገንባት የሚሹትን ሁሉ ያካትታል" ብለዋል።

የኮንግረስ አባላቱ፤ ሜክሲኮ ድንበር ላይ ስደተኞች እየደረሰባቸው ስላለው እንግልት እንዲሁም የመሣሪያ ቁጥጥርና የህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ማተኮር የተሻለ ነው ብለዋል።

ኤልሀን ኦማር በበኩላቸው "ድንበር ላይ ሰብአዊ መብት ሲጣስ፣ ሰዎች ሲታጎሩም ታሪክ እየታዘበን ነው" ብለዋል። አራቱ ሴቶች ላይ የተቃጣው ዘረኛ ጥቃት "አገሪቱን ለመከፋፈል ያለመ፤ የነጭ የበላይነት ሻቾች አጀንዳ" ብለውታል።

ራሺዳ ቲላብ፤ ንግግሩን "ከፕሬዘዳንቱ ዘረኛ አመለካከት የተቀዳ" ብለውታል። የአገሪቱን ሕግ ተመርኩዘው ፕሬዘዳንቱን ተጠያያቂ ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳማይሉም አክለዋል።

ኢህአዴግን ያጣበቀው ሙጫ እየለቀቀ ይሆን?

አሌክሳንድያ ኦስካዝዮ-ኮርቴዝ፤ ከተሞክሯቸው ተነስተው "ታዳጊዎች 'ይህ ፕሬዝዳንት ምንም አለ ምን፣ ይህ አገር ያንተ ነው፤ ያንቺ ነው' መባል አለባቸው" ብለዋል።

"የምንወደውን ነገር ትተን የትም አንሄድም" ያሉት የኮንግረስ አባሏ፤ አዕምሯቸው ያልበሰለ መሪዎች ፓሊሲ ላይ ማተኮር እንደሚሳናቸውም ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት ራሺዳ ቲላብ፣ አያና ፕረስሊ፣ ኤልሀን ኦማር እና አሌክሳንድያ ኦስካዝዮ-ኮርቴዝ የስደተኞች ማቆያ ጎብኝተው ምስክርነታቸውን ሰጥተው ነበር።

ዴሞክራቶች ድንበር ላይ የስደተኞች ሰብአዊ መብት እየተጣሰ ነው ሲሊ የትራምፕን አስተዳደር ይተቻሉ።

ትራምፕ ግን ድንበር ላይ የሰብአዊ መብት እንዳልተጣሰ ተናገረው፤ የኮንግረስ አባላቱን "ደስተኛ ካልሆናችሁና የምታማርሩ ከሆነ መሄድ ትችላላችሁ" ብለዋል።

አራቱ ሴቶች ትላንት ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጡ ሳለም ትራምፕ ተመሳሳይ ነገር ትዊት አድርገዋል። "እዚህ ደስተኛ ካልሆናችሁ መሄድ ትችላለእሀ። ምርጫው የናንተ ነው" ብለዋል።

ከበለስ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የምትመራመረዋ ኢትዮጵያዊት

ፕሬዘዳንቱን እያወገዙ ያሉት ዴሞክራቶች ብቻ ሳይሆኑ ሪፐብሊካኖችም ጭምር ናቸው።

ሴናተር ሚት ሮምኒ የፕሬዘዳንቱን "ከፋፋይና ጠቃሚ ሆነው ጉዳይ የሚያስገነግጥ" ብለውታል። ሰዎች የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ቢኖራቸውም አሜሪካውያንን "ወደመጣችሁበት ተመለሱ" ማለት መስመር ያለፈ ነው ብለዋል።

የአሜሪካ ወዳጅ አገራትም ፕሬዘዳንቱን እየተቹ ነው። የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ጃሲንዳ አርደርን እንዲሁም የካናዳ ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሮዶ ንግግሩን ነቅፈዋል።