ምክር ቤቱ ትራምፕን ክፉኛ አወገዘ

ዶናልድ ትራምፕ Image copyright Getty Images

የአሜሪካ የሕዝብ እንደራሴዎች ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕን የሚያወግዝ ውሳኔ አስተላለፉ። ፕሬዘዳንቱ አራት የኮንግረስ አባላት ላይ በዘረኛ ንግግራቸው ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ፤ ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምፅ ፕሬዘዳንቱን የሚያወግዝ ውሳኔ አሳልፏል።

በውሳኔው ላይ "በአሜሪካውያን መካከል ፍርሀትና ጥላቻን የነዛ ዘረኛ ንግግር" በሚል ንግግራቸው ተተችቷል።

ፕሬዘዳንቱ አራቱን የኮንግረስ አባላት "አገሪቱን ለቅቃችሁ ሂዱ" ካሏቸው ጀምሮ በርካቶች እያብጠለጠሏቸው ነው።

"ትራምፕን ከቁብ አትቁጠሩት" አራቱ የኮንግረስ አባላት

ትራምፕ በበኩላቸው በትዊተር ገጻቸው "ዘረኛ አይደለሁም" ብለዋል።

ዴሞክራቶች የበላይነቱን በያዙበት ምክር ቤት በተካሄደው ድምፅ አሰጣጥ፤ ፕሬዝዳንቱን ያወገዘው ውሳኔ በ240 ድጋፍ ና በ187 ተቃውሞ አልፏል።

ትራምፕ ባሳለፍነው እሁድ ራሺዳ ቲላብ፣ አያና ፕረስሊ፣ ኤልሀን ኦማር እና አሌክሳንድያ ኦስካዝዮ-ኮርቴዝ የመጡባቸው አገራት "የተመሰቃቀሉ ናቸው" ብለው፤ የኮንግረስ አባላቱ "ወደየአገራቸው ይመለሱ" ሲሉ ትዊት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ትራምፕ በትዊታቸው አራቱን የኮንግረስ አባላት በስም ባይጠቅሱም፤ ንግገራቸው ሴቶቹ ላይ የተቃጣ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

"ዘ ስኳድ" በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩት አራቱ የኮንግረስ አባላት አሜሪካውያን ናቸው። ከኤልሀን ኦማር ውጪ ሦስቱ የተወለዱትም አሜሪካ ውስጥ ነው።

ሰኞ እለት አራቱ የኮንግረስ አባላት የፕሬዘዳንቱን ንግግር ችላ ብሎ ፖሊሲ ላይ መማተኮር የተሻለ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

'ከሕግ ውጪ' የተዋሃዱት አምስቱ ክልሎች

ድምፅ አሰጣጡ ሲካሄድ ዴሞክራቱ ጆን ልዊስ፤ "በከፍተኛ የመንግሥት አስተዳደር ለዘረኛነት ቦታ የለንም" ብለው ነበር።

ከምርጫው በኋላ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይ አል ግሪን፤ ዶናልድ ትራምፕ በሕግ እንዲጠየቁ አሳስበዋል። ጥያቄው ለብዙ ወራት ሲንከባለል የመጣ ቢሆንም ፓርቲው እምብዛም ሊገፋበት አልፈለገም።

ፕሬዘዳንቱ በምክር ቤቱ ቢወቀሱም፤ በትዊተር ገጻቸው በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ሪፐብሊካኖች እርሳቸውን ለመደገፍ ያሳዩትን ጥምረት አወድሰዋል።

በሲዳማ ክልልነት ጉዳይ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የምርጫ ቦርድ ወሰነ

ምክር ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ፤ አሜሪካ በስደተኞች ጀርባ ላይ የቆመች አገር እንደሆነች ያመለክታል። ከቀደምት የአሜሪካ ነዋሪዎች (ኔቲቭ አሜሪካንስ) ውጪ ያለው ዜጋ በቅኝ ግዛት፣ በስደት ወደ አገሪቱ የሄደ ነው።

ውሳኔው እንደተገለጸው፤ አገር ወዳድነት የሚገለጸው ሕግ መንግሥት በማክበር እንጂ ሰዎችን በዘራቸው ምክንያት በማንቋሸሽ አይደለም።

የምክር ቤቱ ቃል አቀባይ ናንሲ ፒሎሲ፤ የፕሬዝዳንቱን ንግግር "ዘረኛ፣ ክብረ ነክና አስቀያሚ" ብለውታል።

ሪፐብሊካኖች በበኩላቸው የናንሲ ፒሎሲ አስተያየት የምክር ቤቱን ደንብ የተላለፈ ነው ብለው ተችተዋቸዋል።