የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ፕሬዝዳንት መረጠ

ተመራጯ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱሉ ቮን ዴር ሌይን Image copyright Reuters

ጀርመናዊቷ ኡርሱላ ቮን ዴር ሌይን በጠባብ የድምጽ ልዩነት ተመርጠው የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሆነዋል።

አዲሷ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ከግማሽ በላይ የአውሮፓ ፓርላማ አባላትን ድጋፍ ማግኘት ችለዋል።

ኮሚሽኑ የአውሮፓ ሕብረት ሕጎችን ያረቅቃል፤ ያስፈፅማል፤ አስፈላጊ ከሆነ አባል አገራት ላይ ቅጣት ይጥላል።

የምርጫው ውጤት እንደታወቀ "የጣላችሁብኝ እምነት በአውሮፓ ላይ ያላችሁ መተማመን ውጤት ነው" በማለት ንግግር ያደረጉት ተመራጯ ፕሬዝዳንት፤ ቮን ዴር ሌይን ለአውሮፓ ኮሚሽን የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ናቸው።

'ከሕግ ውጪ' የተዋሃዱት አምስቱ ክልሎች

በኢትዮጵያ ካምፕ ውስጥ ባለ2 ፎቅ መኖሪያ የገነባው ስደተኛ

"ትራምፕን ከቁብ አትቁጠሩት" አራቱ የኮንግረስ አባላት

"ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከደቡብ እስከ ሰሜን በአንድነት በቆመችው አውሮፓ ያላችሁ መተማመን ያሳያል" ያሉት ተመራጯ "ትልቅ ኃላፊነት ነው፤ ሥራዬም አሁን ይጀምራል" ካሉ በኋላ "ለተሻለ ውጤት አብረን እንሥራ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ብራስልስ ውስጥ የተወለዱት ቮን ዴር ሌይን፤ የሰባት ልጆች እናት ሲሆኑ ወደ ፖለቲካ ከመግባታቸው በፊት የማህፀንና ፅንስ ዶክተር ነበሩ።

ለዚህ ቦታ ከመወዳደራቸው በፊት የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን፤ በአስተዳደር ዘመናቸው የጀርመን ጦር ተከታታይ የሆነ የመሣሪያ እጥረት ገጥሞታል በሚል የሰላ ትችት ይቀርብባቸው ነበር።

አዲሷ ፕሬዝዳንት የአውሮፓ ሕብረት ለማህበራዊ ደህንነት እንደሚታገል ቃል የገቡ ሲሆን፣ ድህነትን ለመቅረፍ እንዲሁም ለሴቶች መብት መከበር ጠንክረው እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል።

በንግግራቸው ላይ ዩናይትድ ኪንግደም ከአውሮፓ ሕብረት ለመውጣት በቂ ጊዜ ሊሰጣት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

በፕሬዝዳንቷ መመረጥ የተለያዩ ወገኖች ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ተሰናባቹ ኮሚሽነር በትዊተር ገፃቸው "ይህ ኃላፊነት ትልቅና ተግዳሮት ያለበት ነው። እጅግ በጣም የተሻለች ፕሬዝዳንት እንደምትሆኚ እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል።

የጀርመኗ ቻንስለር አንግላ መርኬል በበኩላቸው የቀድሞዋ መከላከያ ሚኒስትራቸውን "ለሥራዋ የተሰጠችና አውሮፓውያን እምነት የሚጥሉባት" ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።

"ምንም እንኳ ዛሬ ለረዥም ጊዜ በሚኒስትርነት ያገለገሉትን ሴት ከአጠገቤ ባጣም በብራስልስ ግን አዲስ ወዳጅ አግኝቻለሁ" በማለት ለወደፊትም በሥራቸው እንደሚጣመሩ ገልጸዋል።