አርባ ምንጭ፡ የዶርዜ የሽመና ጥበብ መናኸሪያ

በቀለም ያሸበረቁ የዶርዜ የሽመና ውጤቶች

የሃገር ባህል ሽመና ድንቅ ጥበብ ሲነሳ የዶርዜ ማራኪ የአልባሳት ውጤቶች በቀዳሚነት ከሚነሱት መካከል ነው። 'ሽመና የዶርዜዎች እጅ ትሩፋት ነው' ብለን አፋችንን ሞልተን ብናወራ ማጋነን እንደማይሆንብን ሃገር ይመሰክራል።

የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ወቢቷ አርባ ምንጭ ደግሞ ለዚህ ምስክር ናት። እንደው አርባ ምንጭ ውስጥ ምርጡ ሸማኔ ማነው ብለን ስንጠይቅ ሁሉም መላሾች "ወደ ቶታል ሰፈር መሄድ ነው እንጂ ይሄማ ምን ጥያቄ አለው" ይሉናል።

ከታችኛው ሰፈር ወይም ሲቀላ እና ከላይኛው ሴቻ መካከል ላይ ሰፍሮ የሚገኘው በተለምዶ 'ቶታል' ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ከሰዓት ገደማ ደርስን . . . ዘሪሁን ዘነበን ፍለጋ. . . በእግሩ እና በእጁ ጣቶች ጥበብን የጥጥ ፈትል ላይ የሚቀምም ሸማኔ።

ሜድ ኢን ቻይና- የሀገር ባህል አልባሳቶቻችን

ዘሪሁን ከምሳ መልስ የሽመና ሥራውን ሊያጧጡፍ ሲዘጋጅ አገኘነው። «በጣም አሪፍ ምርጥ ሰዓት መጣችሁ. . .» ዘሪሁን በፈገግታ ተቀበለን።

ከሽመና ሥራ አድካሚውና ጊዜ የሚወስደው ክሮቹን በሸማ መሥሪያው ላይ ክሩን አስማምቱ ማስቀመጡ እንደሆነ የነገረን ዘሪሁን፤ ከምሳ በፊት እሱን ሲያሰናዳ ማርፈዱን ነገረን።

አሁን የተቀለሙትን ክሮች ከነጩ ጋር እያዋሃዱ ጥበብን ማፍለቅ ይሆናል ማለት ነው።

«ሙያውን 1999 ላይ ነበር ሥራዬ ብዬ የያዝኩት። ያው ከአባቶቼ እያየሁ የሠራሁት ነው እንጂ በትምህርት ያገኘሁት ነገር የለም። ከዚያ 2002 አካባቢ ነው ከዶርዜ ወደ አርባ ምንጭ ወርደን መሥራት የጀመርነው። ምክንያቱም ዶርዜ እያለን ከሠራነው በኋላ የሚቀበለን የለም። አርባ ምንጭ ግን ወዲያው ነበር ገበያ ያገኘነው።»

ዘሪሁንና ሌሎች አራት ወንዶሞቹ በጋራ በመሆን በማሕበር በመደራጀት 'ቶታል' አካባቢ የብረት ሱቅ ያገኛሉ። እዚህችው የብረት ሱቅ [ላሜራ] ውስጥ ነው ታድያ ዘሪሁን ሽመናውንም ንግዱንም የሚያጧጡፈው።

በእርጥብ ሳርና ቅጠል ጥቃትን ያስቆሙ አባቶች

«ጥጥ የምናገኘው ሲሌ ከሚባል ከአርባ ምንጭ ወጣ ብሎ ከሚገኝ ቦታ ነው። ከዚያ እዚህ መጥቶ ሴቶች ይፈትሉታል፤ ከእነርሱ ነው እኛ የምንገዛው። ባለቀለሞቹ የሚመጡት ግን ከአዲስ አበባ ነው። እዚያ ይነከሩና ይመጣሉ፤ ገበያ ወርደን እንገዛቸዋለን። እርግጥ ዶርዜ ላይም በባሕላዊ መንገድ ተነክሮ የሚመጡ አሉ።»

በዘሪሁን የላሜራ ሱቅ ውስጥ በቀለማት ያጌጡ በርካታ ባሕላዊ አልበሳት ይታያሉ፤ በርከት ያሉት ግን አንገት ላይ ጣል የሚደረጉ 'ስካርቮች' ናቸው።

ዘሪሁን አርባምንጭና አካባቢዋ ያሉ ብሔሮችን የሚወክሉ አምስት ዓይነት አልባሳትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ባንዲራ ጣል ያለበት 'ስካርቭ' እና የሚያሳሳ ቀለማት ያላቸው የአንገት ልብሶችን እንደጉድ ያመርታል።

«የጊዲቾ የምንለው ወይን ጠጅና ቀይ ቀለማትን በነጭ መደብ ላይ ስናዋህድ ነው፤ ጋሞ ደግሞ ቢጫ፣ ጥቁርና ቀይ ቀለማትን የያዘ ነው፤ ኦይዳ የምንለውን በአምስት ዓይነት መልኩ እንሠራዋለን። አልፎም የዘይሴ የምንለው አለ።»

በኦሮምኛና በትግርኛ አፋቸውን የፈቱ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ባለውለታዎች

ዘሪሁን እንደሚለው፤ እያንዳንዱ ቀለም እና አሠራር የሚወክለው ብሔር አለ። ያው ለውጭ ሰው ብዙም ትርጉም ላይሰጥ ወይም ልዩነት ላይኖረው ይችል ይሆናል፤ እኛ ግን ሁሉን ጠንቅቀን እናውቀዋለን ይላል።

የአልጋ ልብሶች [በተለይ ሆቴሎች ይወዷቸዋል ይላል ዘሪሁን]፣ ለሙሉ ልብስ የሚሆኑ ጥበቦች፣ ሰደርያ ላይ የሚውሉ ጥለቶች . . . ከዘሪሁን የሽመና ትሩፋቶች ጥቂቶቹ ናቸው።

«ቱሪስቶች ሥራዬን ይወዱታል»

አርባ ምንጭ እንግዳ ብዙ ናት። ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ ጎብኝዎችን ደፋ ቀና እያለች ስታስተናግድ ነው የምትውለው።

'ከትንሽ ብረት እና ከብዙ ጨርቅ የተሠራች ተሽከርካሪ' እንዲል ፀሐፊው፤ ከወዲያ ወዲህ ውር ውር የሚሉት ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች [ባጃጅ] እግርዎ ውስጥ እየገቡ ቢጠልፍዎ ብዙ አይደናገሩ።

አርባ ምንጭ፤ የውጭና የሃገር ውስጥ ቱሪስቶች ብቻ ሳይሆኑ ለስብሰባ ብለው የሚጎበኟት በርካቶች ናቸው። ይህ ደግሞ ለዘሪሁን ሠርግና ምላሽ ነው። «ብዙ ጊዜ በብዛት የምሠራው ስብሰባ ሲኖር ነው። ለሰስብሰባው ተካፋዮች የሚታደል ነው ተብዬ እንድሥራ ትዕዛዝ ይሰጠኛል፤ በዚያ መሠረት ሥሠራ እውላለሁ» ይላል።

«በርካታ ዓይነት የአንገት ልብስ ስለምሠራ ፈረንጆች ይመጡና አማርጠው ይገዛሉ። ቀለም በዛ ያለበት የሚወዱት እነሱ ናቸው። ለቱሪስቶች እና ለሃገር ውስጥ ገዥ የምንጠራው ዋጋም ትንሽ ልዩነት አለው። ፈረንጆቹ ግን ደስ ብሏቸው ነው የሚገዙኝ። ታድያ ከዓመት ወይም ከሁለት ዓመት በኋላ ሲመጡ ፈልገው ያገኙኝና በብዛት ነው የምንፈልገው ብለው ይገዙኛል።»

ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ ‘የ2017 የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ዲዛይነር’ ሆነች

አንድ ስካርቭ ቀሙቱ 1.70 ሜትር፤ ስፋት 30 ሴንቲ ሜትር ነው፤ በዘሪሁን ልኬት ማለት ነው። ከ70 ብር ጀምሮ እስከ 400 ብር ድረስ ለገበያ ይውላሉ። ያው ዋጋው እንደ ስፋቱና ወርዱ ይለያያል።

የሁለት ልጆች አባት ነው ሸማኔው ዘሪሁን። ቤተሰቤን በደንብ የማስተዳድርበት ጥበብ ነው ይላል፤ ሽመናን። «ዶርዜ ደሬ [ዶርዜ ሃገር] ቅርንጫፍ አለኝ፤ ወንድሞቼ እዚያ ይሠራሉ። እኔም አንዳንዴ እየሄድኩ አግዛቸዋለሁ።

ታድያ ገበያ እንዴት ነው?

«ኧረ ቆንጆ፤ በጣም አሪፍ ነው። ያው ዋናው ሥራ ነው እንጂ ቁጭ ካልክ ምንም የለም [ሳቅ. . .]»

ዶርዜ ...ሸማኔ....ቀጭን ፈታይ...የቤት ፈትል...ጥንግ ድርብ... እያሉ የሽመናንና የእጅ ጥበብ ማደናነቅና አማርጦ ለመልበስ እንግዲህ ወደ አርባ ምንጭ ብቅ ማለት ነው።