ከ43 ዓመት በኋላ የተገናኙት ኢትዮጵያዊ እናትና ስዊድናዊ ልጅ

ሀሊማ ሀሰን እና ማንስ ክላውዘን ከ43 ዓመት በኋላ ሲገናኙ

የፎቶው ባለመብት, Mans Clausen

የምስሉ መግለጫ,

ሀሊማ ሀሰን እና ማንስ ክላውዘን ከ43 ዓመት በኋላ ሲገናኙ

ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ፣ ስድስት ኪሎ አካባቢ

[የዛሬ 43 ዓመት ገደማ ነው። ሊማ ሀሰን በ20ዎቹ እድሜ ክልል የምትገኝ ወጣት ሳለች ከአጋሯ ጋር ልጅ ወለዱ። ሀሰን የሚባል። ጥንዶቹ ብዙም ባይጣጣሙም ሁለተኛ ልጅ ወለዱ። ኑኑ ተባለ። ኑኑ አሁን የሚጠራው ማንስ ክላውን ተብሎ ነው። ሀሊማ ታሪኳን እንዲህ አካፍላናለች።]

ማንስ የልጅነት ልጄ ነው። በእኔና በአባቱ መካከል ችግር ነበር። ሥራ ፈቶ የሚረዱት አባቱ ነበሩ። ቤተሰቦቼ የልጆቼን አባት ስላልወደዱት ተጣልተን ነበር። ሲቸግረኝም ወደ ቤተሰቦቼ ለመመለስ አፍሬ ብቻዬን ተጋፈጥኩ።

ማንስን አርግዤ የእለት ጉርስና አንገት ማስገቢያ አጣሁ። ሀሰንን አዝዬ ማንስን በሆዴ ይዤ በጣም የምቀርባቸው ጓደኞቼ ቤት አድር ጀመር። ዛሬ አንዷ ጋር፤ ትንሽ ቀን ሌላዋ ጋር አሳልፍ ነበር። ከነችግሩ እርግዝናዬ እየገፋ መጣ. . . ሁለት ወር፣ አምስት ወር. . . ስምንት ወር. . . እንደቸገረኝ መውለጃዬ ደረሰ።

ምጤ የመጣው እንኳን ለሰው ለእንስሳም የማይመች ቦታ ነበር። ሰው ከማጣቴ የተነሳ ሆስፒታል የሚወስደኝ አልነበረም። ጠዋት 12 ሰዓት ምጥ የጀመረኝ እስከ ምሽት 12 ሰዓት ብቻዬን አምጬ ቤት ውስጥ ወለድኩ።

ስወልድ እትብት የሚያትብ ሰው እንኳን ጠፋ። ልጄን በልብሴ ታቅፌ ደሜ ላይ ቁጭ አልኩ። የገዛ ደሜን በእጄ አፈስኩ። ምን ልብላ? ምን ልጠጣ? ለእግዚአብሔር ያሉ ሰዎች ቡና አፍልተው ባዶ ቡና ቁርስ ሰጡኝ።

የነበርኩበት ቦታ ከራስጌዬ እሳት ይነድ ነበር። ለመኖር አይመችም። የልጆቼን አባት እህት 'እባክሽ ከዚህ ቦታ አንሽኝ፤ ወይ ውጪ ልውደቅና ዘመድም ይስማኝ' ብዬ ሳለቅስባት ቀበና አካባቢ ያለ ቤታቸው ውስጥ አንድ ክፍል ይሰጣት ብላ አዘዘች።

ወቅቱ ዝናብ ነበር። የሦስት ቀን አራስ ሆኜ በታክሲ ወደቤታቸው ወሰዱኝ። የልጆቼ አባት፣ አባቱ ብር ሲሰጡት ወይ ያመጣዋል ወይ ይጠጣበታል። አንዳንዴ እንደ እብድ ሆኖ ይመጣል።

ሦስት ዓመት ከእሱ ጋር ስቀመጥ የነበረኝ የሦስት ወር ፍቅር ብቻ እንጂ ስለ ሕይወት የማውቀው ነገር የለም። እህቱ ቤት እያለሁ ሲሰጡኝ መብላት ካጣሁኝም መተው. . . አቤት የልጆቼ ስቃይ. . . እንደ ውሻ ደረቅ ጡቴን ጎትቼ ልጄን አጠባ ነበር።

የልጆቼ አባት ከእህቶቹ ጋር አልተስማማም፤ ከእኔጋም ተለያየን። ከዚያ አንድ የወታደር ጊቢ ውስጥ ተከራየሁ። አንድ ቀን ልጆቼን በጣም ሲያምብኝ የካቲት 12 ሆስፒታል ወሰድኳቸው። በሰው በሰው የማውቀው ጆንሰን የሚባል ዶክተርን አገኘሁ።

ልጆቼን ሳሳክም 'መንታ ናቸው?' አለኝ። በተቀራራቢ ጊዜ ስለተወለዱ ነው እንጂ መንታ አይደሉም አልኩት። በዚያው እንዲህ ሆኜ፣ እንዲህ ሆኜ እያልኩ ችግሬን ነገርኩት። 'ልጆችሽ በምንም አይነት አያድጉም፤ ከሚሞቱብሽ ጥሩ ቦታ [በማደጎ] ይሂዱ' ብሎ አምስት ኪሎ ማርኪ የምትባል ስዊድናዊት ጋር እንድሄድ መከረኝ።

ቢሮዋ ሄድኩ። ባለቤቷ ኢትዮጵያዊ ነበር። ተቀበለችኝና ለህጻናቱ የታሸገ ጡጦ፣ ወተትና ለታክሲ ብላ 20 ብር ሰጠችኝ። በዚያ ጊዜ 20 ብር ትልቅ ነው። 'ልጆቹ የጤና ምርመራ ያስፈልጋቸዋል' ስላለችኝ ለሁለቱም ምርመራውን ጀመርኩ። ትልቁ ልጄ ቶሎ በእግሩ አልሄደም ነበር። ራጅ ላይ 'ልቡ ትልቅ ሆኗል፤ ሌላ ሆስፒታል ይታይ' ተባለ። ሌላ ሆስፒታል ሲታይ ደግሞ ጤናማ ነው አሉ። የማንስ ምርመራ ግን ፈጠኖ አለቀለት።

ማንስ 'ጡትሽን እንዲተው የህጻናት ማቆያ ይግባ' ተባለ። ከዚያ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ቀጠሮ ተሰጠኝ። አንድ የማርኪ ተወካይ 'ሁለቱም እኮ አይሄዱም' አለኝ። ተናድጄ 'ሁለቱም እኮ እቃ አይደሉም! ስለቸገረኝ ነው እንጂ ሁለቱም እንዲሄዱ ፍቃደኛ አይደለሁም' አልኩ። ፍርድ ቤት ወሰደኝና 'ለ18 ዓመት' ብለው አስፈረሙኝ።

በወቅቱ አባቴ በጣም ታመው ሆስፒታል ነበሩ። ትንሽ ቆይተው አረፉ። ልጄ 'ጡት እንዲተው' ሰባ ደረጃ አካባቢ ያለ ማቆያ ያስገባሁት አባቴ ከማረፋቸው ከአንድ ሳምንት በፊት ነበር። የአባቴን ለቅሶ ሦስት ቀን ተቀምጬ ልጄን ልይ ብዬ ወደ ማቆያው ሄድኩ።

ማቆያው ውስጥ የሚሠሩት ሞግዚቶች 'ታቀፊው' ብለውኝ ልጄን ሳቅፈው የአልጋ ብረት መቶት ክፉኛ ማልቀሱን መቼም አልረሳውም። በጣም አዝኜ አብሬው አለቀስኩ። አባብዬው፣ ጡጦ ሰጥቼው ወደ ለቅሶ ቤት ተመለስኩ።

በስንተኛ ቀን ወደ ማቆያው ስሄድ 'ልጅሽ ሄዷል' አሉኝ። እህህህ! ምድር ልሁን ሰማይ ልሁን አላውቅም። በጣም ሀዘን ውስጥ ገባሁ፤ ጭንቅላቴ ተረበሸ። ከአባቴ ሀዘን ጋር ተደራረበብኝ። ትልቁን ልጄን ይዤ ቀረሁ።

በሦስተኛው ወር የልጄ ፎቶግራፍ ተላከልኝ። ልጄን ይዛ የሄደችው ሚስስ ኢንግሪንድ የምትባል ሴት ናት ተባለ። ኢንግሪንድ ትኖር የነበረው አፍንጮ በር ነበር። ባለቤቷ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ነበር የሚሠራው።

በሌላ ወር ቤቷ ስሄድ ባዶ ነው። ደነገጥኩ። እንደኔ ከየአቅጣጫው የመጡ ሌሎች ወላጆችም ነበሩ። እሷ ግን የለችም። ከዚያ በኋላ በቃ! የልጄ አድራሻው ጠፋኝ! ጠፋኝ! ጠፋኝ! የማይበጅሽ ይጥፋ. . .

ከዚያማ ማልቀስ ነው. . . መሰቃየት ነው. . . ማልቀስ ነው. . . መሰቃየት ነው!

የፎቶው ባለመብት, Mans Clausen

የምስሉ መግለጫ,

ሀሊማ ሀሰን ከልጆቿ ጋር

ስዊድን፤ ጎተንበርግ

[የሀሊማ ልጅ በማደጎ ስዊድን ሄዶ ማንስ ክላውዘን ተብሎ ከአሳዳጊ ቤተሰቦቹ ጋር መኖር ጀመረ። ልጅነቱን፣ ወጣትነቱን እንዲህ ያወሳል።]

ያደኩት ከእናቴ፣ ከአባቴ፣ ከወንድምና እህቴ ጋር ነው። የማደጎ ልጅ እኔ ብቻ ነበርኩ። ቤተሰቦቼ ይወዱኛል። አያቶቼም ተቀብለውኝ ነበር። የማደጎ ልጅነቴ እምብዛም ተሰምቶኝ አያውቅም። በቃ አንድ የቤተሰቡ አካል ነበርኩ።

በአካባቢው ብዙ ጥቁር ልጆች አልበሩም። ክፍል ውስጥ፣ የእግር ኳስ ቡድናችን ውስጥም ብቸኛው ጥቁር ነበርኩ። ብዙ ጥቃት ባይደርስብኝም በነጮች ተቀባይነት ለማግኘት 'ስዊድሽ' አቀላጥፌ እናገር ነበር። ገና በዘጠኝ ዓመቴ ነጮችን 'ምቾት ላለመንሳት' ምን አይነት ልጅ መሆን እንዳለብኝ ተማርኩ።

እያደግኩ ስሄድ ጓደኞቼ ስለ ትውልድ ቤተሰቦቼ ይጠይቁኝ ነበር። 'ቤተሰቤ ይህ ነው፤ ወንድሜና እህቴም እነዚህ ናቸው' መልሴ ነበር። ብዙ ሰዎች ግን ስለ እኔ መጠየቅ አላቆሙም። አይኔን፣ ፀጉሬን፣ ቆዳዬን ያደንቃሉ። 'ከየት መጣህ?' እባላለሁ። 'ከኢትዮጵያ' ስላቸው፤ 'ኦ ኢትዮጵያ!' ይላሉ በመገረም።

ኢትዮጵያ ሰው ሁሉ የሚራብበት አገር ነው የሚመስላቸው። የአባቴ እናት ስለ ኢትዮጵያ አንዳንድ መጻሕፍት ብታነብልኝም ስለ አገሪቱ ብዙ አላውቅም ነበር።

አድጌ ቤተሰቦቼን ስለ ወላጆቼ ስጠይቅ ብዙ መረጃ እንደሌላቸው ነገሩኝ። እርግጠኛ ባይሆኑም እናቴ ተቸግራ እንደነበር ያውቃሉ። በየወሩ በባንክ ገንዘብ ይልኩላት ነበር። ከስድስት ወይም ከሰባት ወር በኋላ ገንዘቡን ማንም እንዳልወሰደው ባንኩ ለአባቴ ነገረው። ቤተሰቦቼ እናቴን የት ያግኟት? ምናልባት ከአዲስ አበባ ወጥታለች ወይም ሞታለች ብለው እንዳሰቡ ነገሩኝ።

ከዚያ በኋላ መጠየቅ አቆምኩ። ስለእሷና ስለተቀረው ቤተሰብም አላሰብኩም። ለብዙ ዓመታት ስዊድናዊ መሆኔን አምኜ ኖርኩ። ጓደኞቼ 'ወደ ኢትዮጵያ መሄድ አትፈልግም?'፣ 'እናትና አባትህን ማግኘት፣ እህት፣ ወንድም ካለህ ማወቅ አትፈልግም?' ቢሉም ያን ማድረግ እንዳለብኝ አልተሰማኝም።

ቤተሰቦቼ ኢቫና እና የንስ ናቸው! ጥሩ ልጅነት ነበረኝ። የተለየ የቆዳ ቀለም ስላለኝ ብቻ 'ወላጆቼን' መፈለግ አለብኝ የሚለው ሀሳብ ትርጉም አልሰጠኝም። አንዳንዴ ግን ለምን ቤተሰቤን መፈለግ እንዳለብኝ አልተሰማኝም? እልና ሀፍረት ይሰማኛል። አዲስ አበባ ባድግ ምን ይፈጠር ነበር? ብዬ ማሰቤም አልቀረም።

የማንነት ጥያቄ የሚረብሻቸው በማደጎ ያደጉ ጓደኞች ነበሩኝ። በጣም ይከፉ ነበር። እንደ ጓደኞቼ ያልተወዛገብኩት ምናልባትም በፍቅር ስላደኩ ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, Mans Clausen

የምስሉ መግለጫ,

ማንስ ክላውዘን ወጣት ሳለ

ከጥቁር ጓደኞቼ ጋር ሂፕ ሀፕ እና ሬጌ እሰማለሁ፤ ቅርጫት ኳስ እጫወታለሁ. . . ከነጭ ጓደኞቼ ጋር ሻምፓኝ ወይም ወይን እየጠጣሁ እራት እበላና ማታ ደግሞ ከጥቁር ጓደኞቼ ጋር ሬጌ ክለብ እሄዳለሁ። ሁለቱንም ሳደርግ ምንም ችግር አልነበረብኝም። ጎን ለጎን አስኬዳቸዋለሁ። አጣጥማቸዋለሁ።

18 ዓመቴ አካባቢ ጠበቃ መሆን እፈልግ ነበር። ለምን እንደሆነ እንጃ። ግን የሕግ ትምህርት ቤት አልገባሁም። አንድ ጓደኛዬ እስኪ የትወና ትምህርት ቤት እንሞክር ሲለኝ ተስማማሁ።

ትምህርቱ ደስ አለኝ። አስከትዬም ዩኒቨርስቲ ገብቼ ቴአትር አጠናሁ። አሁን ተዋናይ ነኝ። በብዛት የመድረክ ቴአትር እሠራለሁ። አልፎ አልፎ ደግሞ የራድዮ ድራማ።

በአባቷ ኢትዮጵያዊት በእናቷ ስዊድናዊት የሆነች ጓደኛ ነበረችኝ። ኢትዮጵያዊ ልጅ በማደጎ ታሳድግም ነበር። ወደ 30 ዓመቴ አካባቢ ቴአትር ቤቷ ውስጥ ቀጠረችኝ። ስዊደን ውስጥ ጥቁር ሆኖ መኖር ምን ማለት እንደሆነ፣ ስለ ኢትዮጵያም ብዙ እናወራ ነበር። ከእሷ ጋር ለ12 ዓመት መሥራቴ ስለ ታሪኬና ባህሌ አበክሬ እንድጠይቅ አደረገኝ።

ጨዋታችንን ተመርኩዤ የማንነት ጥያቄዎቼን የሚያንጸባርቅ መነባንብ ሠርቻለሁ። ያዘጋጀችው እሷ ነበረች። 'ብለድ ኢዝ ቲከር ዛን ወተር' [ትንሽ ሥጋ እንደ መርፌ ትወጋ] ይባል የለ? ቴአትሩ የሚያሳየውም ይህንን ነው።

አሁን የምኖረው ስቶኮልም ውስጥ ከልጆቼ ኦሊቪያና ቻርሊ ጋር ነው። ያው የትወና ሥራ ማግኘት ቢከብድም አለሁ. . .

የእውነት ኢትዮጵያዊነት ተሰምቶኝ አያውቅም. . . ይህን ስልሽ ትንሽ አፍራለሁ. . . ስለ ኢትዮጵያ ማንበብ የጀመርኩትም በቅርቡ ነው። አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያዊ እንደሆንኩ አይሰማኝም። እንዲህ ማሰቤ ችግር አለው ብዬም አላስብም።

ኢትዮጵያ፤ አዲስ አበባ

[ሃሊማ ልጇን ካጣችበት ጊዜ አንስቶ መፈለግ አላቆመችም። ከሁለቱ ልጆቿ አባት ጋር ከተለያዩ በኋላ ሞተ። እሷም ከሌላ ሰው ጋር ትዳር መሰረተች። አራት ልጆችም አፈሩ።]

ከአራቱ ልጆቼ አባት ጋር ጅጅጋ እንተዋወቅ ነበር። 'እድገት በሕብረት ዘመቻ ጨርሼ ከመጣሁ አብረን እንኖራለን' ይለኝ ነበር። ጌታ ምስጋና ይግባውና ዘመቻውን ጨርሶ መጣ። ከእሱ ጋር ኑሮ ቀጠልኩ። በጣም ጥሩ ሰው ነው። ልጄን ስናፍቅ ያጽናናኝ ነበር።

ወዳጅ ዘመዶቼ ሲመክሩኝ፤ እኔ ሳለቅስ፤ አስከመቼ ነው እንዲህ የምኖረው? ስል ዓመታት ተቆጠሩ። 'የ40 ቀን ልጅ እንኳን ውጪ ሄዶ ይመለሳል' እያሉኝ እንዳይኖሩት የለም መቼም፤ ኖርኩ።

የማንስ ጉዳይ በጭንቅላቴ ስላለ ቶሎ አልወለድኩም። ወሊድ መከላከያ ለሁለትና ለሦስት ዓመት ብቻ መውሰድ ሲገባኝ ለሰባት ዓመት ወሰድኩ። መድሀኒቱን ሳቆም አረገዝኩና አራት ልጆች አከታትዬ ወለድኩ። መሀል ላይ መንታ ልጆች አስወርዶኛል።

የዘወትር ሥራዬ ስዊደን ኤምባሲ መመላለስ ሆነ። ቤታችን ስዊድን ኤምባሲ አጠገብ ነበር። 'የወሰደው ድርጀት ስም ማን ነው?' ይሉኛል። ስነግራቸው 'አናውቀውም' ይላሉ። ማኅበራዊ ጉዳይ ስመላለስም 'የምናውቀው ነገር የለም' አሉኝ።

አንድ ወቅት ላይ ስዊድን ኤምባሲ የምትሠራ የሩቅ ዘመድ አገኘሁ። አያቷ የአክስቴ ልጅ ናቸው። የማርኪን ኢትዮጵያዊ ባል አድራሻ አገኘችልኝ። እሱ 'ከሚስቴ ከተለየሁ 23 ዓመት ሆነኝ እኮ' አለን። እኔና ዘመዴ አድራሻዋን ስጠን እያልነው ሳንገናኝ ሦስት ዓመት አለፈ።

ከዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ህጻናት ድርጅት ስሄድ ማኅበራዊ ጉዳይ ላኩኝ። ፋይል ክፍል ገብተን አገላበጥን። የአደራ የተባሉት ሰዎች እንኳን ፋይላቸውን ሲያገኙ እኔ ግን የልጄን ፋይል ላገኝ አልቻልኩም። ጭንቅላቴን አዙሬ፣ አልቅሼ የማታ ማታ ቤት ገባሁ።

ሲነሳብኝ እንደ ጉድ አለቅሳለሁ። እቃ እሰብራለሁ። ወይ ሞተ ብዬ አልተወው። አንዳንዴ ስናደድ 'ይሄ ሰው 18 ዓመት ከሞላው፤ ኢትዮጵያ መጥቶ በጋዜጣ አያሳውጅም? በሬድዮ አይናገርም?' እላለሁ። እኔም ዘመዶቼም እያንዳንዱን ሚድያ እንከታተል ነበር።

በእሱ ምክንያት ሳልማር፣ ደረጃዬንም ሳላሻሽል ቀረሁ።

የፎቶው ባለመብት, Husein Feisel

የምስሉ መግለጫ,

ሀሊማ ሀሰን ወጣት ሳለች

ማንስን ፍለጋ የምወጣው ከልጆቼ ጋር ነበር። የመጨረሻ ልጄ ሁሴንን ከትምህርት ቤት ይዤው እወጣና ፍለጋ እንሄዳለን። ሁሴን አድጎ ስልክ መያዝ ከጀመረበት እድሜ አንስቶም ወንድሙን መፈለግ ቀጠለ።

ልጄን ፍለጋ ያልሄድኩበት ድርጅት የለም። በሬድዮ 'አንድ ሰው ልጁን ከ40 ዓመት በኋላ ስዊድን አገኘ' ሲሉ እሱ ጋር ሄድኩ። 'ልጁ የስዩም ቻቻ ነው፤ ስሙ ኑኑ አይደለም' አሉኝ።

ከጉጉቴ የተነሳ የውጪ አገር ኳስ ጨዋታ ከባለቤቴ ጋር ቁጭ ብዬ አያለሁ። ከጭንቀቴ የተነሳ ነው እንጂ የዘጠኝ ወር ልጅ ውጪ ሄዶ ኳስ ይጫወት፣ ንጉሥ ይሁን አላውቅም። በሕይወት መኖሩንም አላውቅም። እንዲሁ ጠይም ሰው ሳይ ሆዴ ይባባል።

በልጅነቱ ፀጉሩ ረዥም መሆኑን አስታውሳለሁ። ፀጉረ ረዥም ኳስ ተጫዋች ሳይ እሱ ይሆን? እላለሁ። የእናት ነገር፤ ሆዴ እየዋለለ። ማነው እሱ. . . ሮናልዲንሆ. . . ልጄ ይመስለኝ ነበር. . . እንዲያውም ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር. . .

ልጆቼን እንኳን ወለድኳቸው እላለሁ። ግን ማንንም ከማንስ በላይ አላደርግም። ማንስ ታሪኬ ነው። ልጅነቴን የሰበርኩበት ልጄ ነው። በሕጋዊ መንገድ ፍርድ ቤትን ተገን አድርጌ ነበር የላኩት። ነገር ግን ፍርድ ቤት ምላሽ አልሰጠኝም።

ያጽናናኝ የነበረው ባሌ ከ28 ዓመት ትዳር በኋላ በሞተ በሦስት ዓመቱ የመጀመሪያ ልጄ [ሀሰን] በሁለት ቀን ህመም ሞተ። ሀሰን ሞተብኝ፤ ማንስም ከአገሩ ወጥቶ ይሙት ይኑር ሳላውቅ. . . ስቃዬ በረታ። ሆኖም እግዚአብሔር የሰጠኝን ነፍስ በእጄ አላጠፋም ብዬ ትምህርት ቤት ውስጥ የህጻናት ክፍል እየሠራሁ በማገኘው ብር ሌሎቹን ልጆቼን ለብቻዬ ማሳደግ ቀጠልኩ።

ኢትዮጵያ፤ አዲስ አበባ

[የሀሊማ የመጨረሻ ልጅ ሁሴን ፈይሰል ከልጅነቱ ጀምሮ ወንድሙ ማንስን መፈለግ ጀመረ። ፍለጋውን እንዲህ ይተርካል።]

በጣም ልጅ ሆኜ እናቴ ማንስን ስትፈልገው አስታውሳለሁ። ቤታችን ስዊድን ኤምባሲ አካባቢ ነበርና ሁሌ አርብ አርብ ቪዛ ከሚጠብቁ መንገደኞች ጋር ትሰለፋለች። ተራ ሲደርሳት ስለልጇ ትጠይቃለች። ጥሩ መልስ አይሰጧትም። ያጉላሏታል። 'ምንም መረጃ የለንም?' 'አንቺስ ምን መረጃ ይዘሽ ነው?' ይሏታል። እሷ ግን ሳትታክት ተመልሳ ትሄዳለች።

ለእናቴ ቅርብ ነኝ። ብዙ ችግር ስታይም ከጎኗ ነበርኩ። በየሄደችበት የምትጠይቃቸው ሰዎች ሲያመናጭቋት፣ ሲሰድቧት ጭምርም አይቻለሁ።

ሁሌም ወሬዋ ስለሱ ነው። ትልቁ ምኞቷ እሱን አይታ አፈር መቅመስ ነበር። ላገኘችው ሰው፣ ላገኘችው 'ኤንጂኦ' ፎቶውን ትሰጣለች። ከጭንቀቷ ብዛት ፎቶውን ለአንድ መንገደኛ መስጠቷን አልረሳውም። ሴትየዋ ፎቶውን ይዛባት ሄደች. . . አቤት እናቴ ያኔ የተሰማት ሀዘን. . .

በልጅነቴ 'ፍለጋ እንሂድ' ስትለኝ ትዝ ይለኛል። ለተወሰነ ሰዓት እናፈላልግና ቤት እንገባለን። 'ውጪ ዘመድ አለኝ' ያላትን ሁሉ ፈልጉልን ትላለች። የእናቴ ጭንቀት እኔንም ያስጨንቀኝ ነበር። በሞባይል 'ዳታ' ካገኘሁ ጊዜ ጀምሮ ኢንተርኔት መጎርጎር አላቆምኩም።

'አፍሮ ስዊድሽ' ድረ ገጾች ላይ የጉዲፈቻ ልጆች እፈልጋለሁ። ጥቁር ስዊድናዊያን ሁሉ ወንድሜ ይመስሉኛል። ድንገት ኢትዮጵያ ከመጣ እንዲያገኘን 'ስዊድናዊ ኢትዮጵያዊያን' የሚል ገጽ አውጥቼም ነበር።

የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ እስኪ 'ቤተሰብ ፍለጋ' [Ethiopian Adoption Connection] ላይ ፎርም ሙላ አሉኝ። ሞላሁ። አንድርያ [መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገና የተጠፋፉ ቤተሰቦችን የሚያገናኘው ድርጅት መስራች] እና ብሌን የምትባልን ልጅ አገኘሁ። ስለተወለደበት፣ ስለታከመበት አካባቢ ብዙ ይጠይቁኝ ነበር። ሲያዋሩኝ ወንድሜን በነጋታው እንደማገኘው ይሰማኝ ነበር። በአምላኬ እተማመናለኋ!

ቤት ውስጥ የነበሩ የማንስ ፎቶዎች ጠፍተው ያገኘሁት አንድ ብቻ ነበር። እሱን ለማንም አልሰጠሁም። [ይህ የማንስ የልጅነት ፎቶ ቅጂ ማንስም ነበረው]። እናቴ ማንስ የሚገኝ ስላልመሰላት ብዙ ጥያቄ ስጠይቃት ትሰላች ነበር። እነ ብሌን የሚደውሉልኝ ማታ ማታ ነበር። 'ኧረ አንተ ልጅ ለምን አተኛም?' ትለኛለች። እናቴ በዚያ ወቅት ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ነበረች።

የፎቶው ባለመብት, Mans Clausen

የምስሉ መግለጫ,

ከግራ ማንስ ክላውዘን፣ ሀሊማ ሀሰንና ሁሴን ፈይሰል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም

ስለ ወንድሜ መረጃ እየሰጠኋቸው ሲያፈላልጉ ወራት ተቆጠረ። የሆነ ቀን ደወሉና ጥሩም መጥፎም ዜና ነገሩኝ። 'ጥሩው ዜና ወንድምህ ተገኝቷል። መጥፎው ዜና ነገሩን እንደሰማ ድንጋጤ ውስጥ ስለገባ ትንሽ ይረጋጋና እናገናኝሀለን' አሉኝ።

ተርበተበትኩ፤ እግሬ ተያያዘ፤ ፈራሁም።

እናቴን የሚያስከፋ አይነት ሰው ቢሆንስ? ደስታ ስናስብ ሀዘን ቢጠብቀንስ? ከእኛ ጋር ስላላደገ አናውቀውም። እናቴን ቢያስከፋብኝ ሌላ ህመም ነው የሚሆንብኝ። ለቤተሰባችንም ሌላ ተጨማሪ ህመም! በድጋሚ መጸለይ ጀመርኳ. . . አምላኬ እዚህ እድርሰኸናልና መጨረሻውን አሳምርልን ብዬ።

ስዊድን፤ ስቶኮልም

[ማንስ ወላጅ እናቱ እየፈለገችው እንደሆነ ያወቀው 'ቤተሰብ ፍለጋ' የተባለው የተጠፋፉ ቤተሰቦች አገናኝ ድርጅት ኢ-ሜል ሲልክለት ነው። ወቅቱንም እንዲህ ያስታውሳል።]

'ጤና ይስጥልን ሚስተር ማንስ ክላውስ፤ በዚህ ጽሁፍ ላይ የተገለጸው ሰው አንተ ልትሆን ትችላለህ' የሚል ኢሜል ደረሰኝ። ኢሜሉን ከፍቼው በ10 ሰከንድ ውስጥ ልቤ በፍጥነት ይመታ ጀመር።

'ከ1970ዎቹ እስከ 75 ባለው ጊዜ የተወለደ ልጅ እየፈለግን ነው' ይላል። የተወለድኩበትን ዓመተ ምሕረት በትክክከል ካላወቁማ የሚፈልጉት ሰው እኔ አይደለሁም አልኩ። ምንም እንኳ በተባለው ዓመት ገደማ ብወለድም ማመን አልፈለኩም። ልቤ ግን መምታቱን ቀጠለ። ድው ድው ድው. . .

እኔ ልሆን እችላለሁ. . .

የተጻፈውን ስም አነበብኩ። የእኔ ነው! በመጨረሻ የሀሊማን ፎቶ አየሁ። ቤት አንድ ፎቶዋ ነበረኝ። የተላከልኝ ሌላ ፎቶ ቢሆንም ፎቶዎቹ ላይ ያለችው ሴት አንድ ናት።

የልጆቼ እናት እውነት ሊሆን ይችላል አለችኝ። ከዚያ ለእናቴ ደወልኩ። [አሳዳጊ] እናቴ [ወላጅ] እናቴ እንደሞተች ነበር የምታስበው። አንድ ሰው ገንዘብ ፈልጎ ያደረገው ቢሆንስ? ብዬ አሰብኩ። ይሄንን ሁሉ ዓመት እየፈለጉኝ ከነበረ እንዴት አላገኙኝም? እኔን ማግኘት ያን ያህል ከባድ ሊሆን አይችልም። ስዊድን ኤምባሲ ወይም በማደጎ የሰጠኝ ድርጅት መደወል ይችሉ ነበር እያልኩ አወጣሁ አወረድኩ. . .

እየተፈለገ ያለው ሰው እኔ መሆኔን ልቤ ቢያውቅም ተጨማሪ ማስረጃ ላኩልኝ አልኩ። ተጨማሪ የሀሊማ ፎቶዎች ደረሱኝ። ከተላኩት ፎቶዎች አንዱ እኔ ከድሮም ጀምሮ ከነበረኝ ፎቶ ጋር ተመሳሳይ ነበር።

ግራ ገባኝ. . . ትንሽ ቆይቼ በኤጀንሲው [ቤተሰብ ፍለጋ] በኩል ለቤተሰቡ መልዕክት ላኩ። ሀሊማ ብዙም እንግሊዘኛ ስለማትችል በቀጥታ ለእሷ መጻፍ አልቻልኩም።

ከሥራ እረፍት ሳገኝ የአውሮፕላን ትኬት ገዛሁ። ከመሄዴ ከአንድ ሳምንት በፊት የአክስቴ ልጅ ሙና ደወለችልኝ። እንግሊዘኛ ስለምትችል የሚጠብቀኝን ነገር አስረዳችኝ። ቀለል አለኝ።

ቤተሰቦቼ ለብቻዬ አዲስ አበባ እንድሄድ አልፈለጉም ነበር። ፈሩ፣ ተጨነቁ፣ ተጠራጠሩ። አብረውኝ ለመሄድም ፈልገው ነበር። እኔ በተቃራኒው የተሰማኝ ፍርሀት ሳይሆን ጉጉት ነበር። ወደ ኢትዮጵያ ብቻዬን እንደምሄድ ለቤተሰቦቼ ነገርኳቸው።

ጉዞው የእኔና የእኔ ብቻ ነበር. . .

የፎቶው ባለመብት, Mans clausen

የምስሉ መግለጫ,

ማንስ ክላውዘን ከኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቹ ጋር የተነሳው ፎቶ

ኢትዮጵያ፤ አዲስ አበባ፤ ሀያት አካባቢ

[የዛሬ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ገደማ ላይ ሀሊማ ከ43 ዓመት ፍለጋ በኋላ ልጇ እንደተገኘ የሰማችበት ቀን ምን ይመስል ነበር?]

ጥቅምት 18 ለ19 አጥቢያ ሌሊት 11 ሰዓት ለፀሎት ተነስቼ ነበር። ፀሎት አድርጌ ለልጄ ልጆች ሻይ ጣድኩ። 'ኪችን' ውስጥ ቆሜ ስልክ ተደወለ።

'እናት፣ እናት፣ እናት' እያለ ሁሴን ጠራኝ። ምንድነው? ስለው 'ወንድምህ ተገኝቷል አሉኝ' አለ።

ከዚያማ. . . ምን ልበልሽ ኡኡታ. . . እልልታ ቀለጠ። በዚያች ሌሊት ልጆቼ አቅፈውኝ ጮህን! ሰላት ከመስገዳችን በፊት ሽንት ቤት ለመግባት 'እኔ ልቅደም፤ እኔ ልቅደም' እያልን ከሁሴን ጋር ተጣላን።

አንድ ልጅ አምስት ሰዓት ላይ ደብዳቤ ይዛ ትመጣለች ተባልኩ። ሰዓቱ እንዴት ይድረስልኝ። እንደገና ተደውሎ የምትመጣው ዘጠኝ ሰዓት ነው ተባለ። ይሁን አልኩ። ልጅቷን ለመጋበዝ ምግብ ሠራን፤ ወጣሁ ወረድኩ. . . መጣች።

የልጄን ፎቶ ከደብዳቤ ጋር ሰጠችኝ። አቤት ደስታዬ! ከዚያም ፎቶ አነሳችኝ። 'የቤተሰብ ፎቶ አዘጋጂ' አለችኝ። ወንድም እህቶቹን ሰብስቤ ፎቶ ተነስተን ለማንስ ተላከ።

ወዲያው ወደየዘመዱ ተደወለ። አንዱ ከአንዱ ተቀባበለ። ድህነቴን ልትቀርፍ ሪያድ የሄደች ልጅ አለችኝ፤ ወደእሷ ተደወለ። አንድ ከርታታ ወንድምም ካናዳ አለኝ። ተደወለለት። የማንስ ፎቶ ወደ እንግሊዝ፣ ወደ አሜሪካ ተበተነ።

አንዷ ዘመዴ ትራፊክ እስከሚከሳት መሀል መንገድ ላይ መኪና አቁማ ኡኡኡ ነው ያለችው። እልል አይደለም። ኡኡ! 'ምን ሆነሻል ሙና?' ስትባል 'የአክስቴ ልጅ ተገኘ' ብላ ለቅሶና ሳቋ ድብልቅልቁ ወጣ።

ደስታችን ወደር አልነበረውም፤ ዛሬም የለውም።

ፎቶ ከላኩለት በኋላ በአስተርጓሚ 'አቅም አጥቼ ነው እንጂ ወዲያው መጥቼ አይህ ነበር' አልኩት። 'እናቴ ፈቃደኛ ከሆነች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እፈልጋለሁ' ብሎ መልስ ሰጠ።

ደስታውን አልቻኩትም። ወንዝ እንዳይገባብኝ በሰላም ይምጣ ስል ልጆቼ ይስቁ ነበር።

ኢትዮጵያ፤ አዲስ አበባ፤ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ሀያት

[ማንስ]

አዲስ አበባ ደረስኩ። የሆነ የእውነት የእውነት የማይመስል ነገር ነው። አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ሀሊማ፣ ሁሴን፣ ሙናና እስክንድርን ሳገኛቸው እየጮሁ፣ እያለቀሱ ነበር፤ ግራ ገባኝ። ምን ይሰማኝ? እነዚህን ሰዎች አላውቃቸውም እኮ!

በእርግጥ ሀሊማን አውቃትለሁ። ግን አላስታውሳትም። እየፈለኳትም አልነበረም።

ሀሊማ በጣም ተደስታ ነበር። እኔም ልጄ ቢጠፋብኝ መላ ሕይወቴን ስለምፈልገው ስሜቷ ገባኝ።

ሀሊማ አስሩንም ቀን ስታቅፈኝ፣ ስትስመኝ፤ እኔ እንዴት ይህ አልተሰማኝም? ብዬ ተጨንቄ ነበር። ጥፋተኛነትም ተሰምቶኝ ነበር። ምን እንደተሰማኝ፣ ምን አይነት ስሜት ሊሰማኝ እንደሚገባ ማወቅ አልቻልኩም።

አዲስ አበባ አንድ ኢትዮጵያዊ አግኝቼ ነበር። ምን አለኝ መሰለሽ? 'ለራስህ ጊዜ ስጠው!'

ወንድሙና እህቱ በማደጎ ስዊድን ውስጥ 30 ዓመት ኖረው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ነበር። ወንድሙ ኢትዮጵያ ግራ አጋባችው። 'እኔ ስዊድናዊ ነኝ' ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ሳይመለስ ቀረ። እህቱ ኢትዮጵያን ወዳት እዛው መማር ጀመረች። የኢትዮጵያና የስዊድኑ ቤተሰብ በቅጡ ለመተዋወቅና ለመግባባት 25 ዓመት እንደወሰደባቸው ነገረኝ። 'በተለያየ ዓለም ነው የምንኖረው፤ እንዲህ ይሰማኝ! ብለህ አትጣደፍ' አለኝ።

ይህንን ስሰማ ጫናው ቀለለልኝ። ሁሉም ነገር ቀስ በቀስ እንደሚሆን ተረዳሁ። ወደ 40 ዓመት ምናምን ተጠፋፍተን ነበር እኮ! ለሀሊማም ጊዜ እንደሚወስድብኝ ነግሬያታለሁ። ትረዳኛለች ብዬ አስባለሁ።

የሆነ ሰው ለዓመታት ሲፈልግሽ፣ ሲናፍቅሽ እንደነበረ ማሰብ የተለየ ስሜት ይሰጣል። ምናልባትም ቤተሰቤን መፈለግ ነበረብኝ እንዴ? ስሜቴን ደብቄ ነበር የኖርኩት? እንጃ. . . አሁን 'ቴራፒስት' [የሥነ ልቦና አማካሪ] ጋር እየሄድኩ ነው።

ጎድሎኝ እንደነበረ ያላወኩት ክፍተት እንደተሞላ አስባለሁ። በመጠኑም ቢሆን ሁለት አገር እንዳለኝ ተሰምቶኛል። ቢያንስ ለልጆቼ ስለ ታሪኬና ባህሌ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ።

ከሀሊማ ጋር ደብዳቤ እንጻጻፋለን። በቋንቋ ችግር ምክንያት ትስስራችን እንዳይላላ እሰጋለሁ። ግን ደግሞ ሁለት ቤተሰብ አግኝቻለሁ። አንድ ቀን ስዊድንዊ እና ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቼን አገናኛቸው ይሆናል. . . እናያለን. . .

የፎቶው ባለመብት, Husein Feisel

የምስሉ መግለጫ,

ሀሊማ ሀሰን ለልጇ ማንስ ክላውዘን አቀባበል ስታደርግ

[ሀሊማ]

ጥር 6 ኢትዮጵያ ገባ።

ፈረንጅ፣ መንገደኛ፣ ሕዝብ ሁሉ እስከሚያለቅስ በእልልታ ልጄን ተቀብዬው ቤቴ ይዤው መጣሁ። እናትና ልጅ ጠበቃ የለውም። ዳኝነት የለውም። በቃ ችግራችን አበቃ። አላህ ልጄን ጉያዬ ስር ከተተልኝ።

እሱን ካረፈበት ሆቴል እኔ ቤት የሚያመጣ እኔንም የሚወስድ መኪና ተከራየልኝ። 'ከቤተሰብ ርቀው የሚኖሩ ልጆች ብር ሲጠይቋቸው ይበረግጋሉ' ብለው መከሩኝ። አሄሄ. . . እኔ ግን ብር የምል ሰው አይደለሁም።

የመጀመሪያ ቀን 'ኢንተርቪው አደርግሻለሁ' ብሎ ታሪኬ በአስተርጓሚ ሲነገረው ብድግ ብሎ እያለቀሰ ጉልበቴ ላይ ተደፍቶ 'ይቅርታ እናቴ፤ እኔን ብለሽ ነው። የትም አልተጣልኩም። ጥሩ ቦታ፣ በጣም ጥሩ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደኩት። በጣም አመሰግንሻለሁ እናቴ' አለኝ።

ልጄ ሽቁጥቁጥ ነው። ውስጤን አንብቧል። እሱን ያሳደገ ቤተሰብ ለዘለዓለም ይኑር። ላሳደገው ቤተሰብ በአንድ እግሬ ቆሜ ነው የምጸልየው።

መቼም እንግሊዘኛዬን ተይው. . . እሰባብረዋለሁ። ግን እንኳን እናትና ልጅ አንደበቱ የተዘጋም ይግባባል። እናትና ልጅ መካከል ጌታ ከባድ ስልጣን አለው።

አብሮኝ የቆየበትን አስር ቀን እንደ አስር ሰዓት ነው የቆጠርኩት። አጠረብኝ። ናፍቆቱ አልወጣልኝም።

ልጄ ሳይለየኝ ቤተ ዘመድ መጥቶ አየልኝ። የታከመበት የካቲት 12 ሆስፒታል ወሰድነው። የማርኪ ቢሮ የነበረውንም አሳየነው። ሙዝየምም አብረን ገባን። አዲስ አበባን እንደ ልቡ ዞራት። እራት አከሌ ጋር. . . ምሳ. . . ምናምን ስንል ቀኗ ሄደችብን። አለቀች።

ሻንጣውን ጎትቶ ቤቱ ሳይገባ 'ደርሻለሁ' ብሎ ደወለልን። አላህ ምስጋና ይግባውና አሁን ከልጄ ጋር እጅና ጓንት ሆነን አለን። ደብዳቤ እንጻጻፋለን። ፖስታ ሲልክልኝ ከፖስታ ቤት ደብዳቤውን እየሳምኩ ነው የምወጣው። እግሬን ስለሚያመኝ ዳገትና ፎቅ አትውጪ እባላለሁ። የእሱን ፖስታ ሳገኝ ግን ያ ያመመኝ እግር ይፈወሳል። ኃይል አገኛለሁ!