በሐዋሳ ውጥረት ነግሷል ተባለ

ሐዋሳ

ዛሬ ረፋድ ላይ በሐዋሳ ከተማ የተኩስ ድምጽ መሰማቱን ተከትሎ፤ ስጋትና ውጥረት መንገሱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች የሚኖሩ ሰዎች ተናገሩ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች እንዳረጋገጡትም ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ በከተማዋ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል።

ቀድሞውኑም በዛሬው ዕለት (ሐምሌ 11/2011 ዓ. ም) የሲዳማን ክልልነት ይታወጃል በሚል ከነበረው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ስጋት የነበረ ሲሆን፤ ረፋድ ሦስት ሰዓት ገደማ በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ በከተከሰተ ተቃውሞና በተሰማ የተኩስ ድምጽ ሳቢያ አብዛኛው የከተማዋ ክፍል ከተለመደው እንቅስቃሴ ውጪ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

"ነገ ክልል መሆናችንን እናውጃለን" የኤጀቶ አስተባባሪ

የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄን በተመለከተ ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ሃሳብ በተመለከተ የአገር ሽማግሌዎችና የዞኑ መስተዳደር ተወያይተው፤ ሕዝቡ ያቀረበውን ሃሳብ ተቀብሎ ሕዝበ ውሳኔውን እንዲጠብቅ መስማማታቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ሰዎች ቢቢሲ ለማወቅ ችሏል።

ነገር ግን ወጣቶች ውሳኔውን በመቃወም ዛሬ ረፋድ ላይ ጉዱማሌ ወደተባለው ስፍራ ተሰብስበው በሚሄዱበት ጊዜ መንገድ መዝጋታቸውንና መኪኖች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ በቦታው ነበርኩ ያለ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግሯል። በዚህም ጊዜ የጸጥታ ኃይሎች ወጣቶቹ እንዲበተኑ ማድረጋቸውንም ተናግሯል።

'ከሕግ ውጪ' የተዋሃዱት አምስቱ ክልሎች

ይህንንም ተከትሎ ስጋት ውስጥ የነበረው የከተማዋ ነዋሪ ከመደበኛ ተግባሩ መቆጠቡንና ሱቆችና ሌሎች የንግድ ተቋማት በራቸውን መዝጋታቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በአንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች ተኩስ መሰማቱን አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ቢናገርም፤ ሌላ ነዋሪ ግን የከተማዋ እንቅስቃሴ ተገቶ ጭር ማለቱን ተናግራ፤ ባለችበት አካባቢ ግን ተኩስ አለመስማቷን ገልጻለች።

ውጥረቱን ተከትሎ በሕዝብ እንቅስቃሴ የሚታወቁ የከተማዋ ክፍሎች መቀዛቀዛቸውን ያናገርናቸው ሰዎች የተናገሩ ሲሆን፤ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ይታዩ የነበሩት የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ እንደሚታዩም ተናግረዋል።

አቶቴ ተብሎ በሚታወቀው የከተማዋ አካባቢ ያሉ የንግድ ተቋማት መዘጋታቸውንም አንዳንዶች እየተናገሩ ነው።

ኢትዮጵያ ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር እንዴት ትውጣ?

በተጨማሪም አላሙራ በተባለው አካባቢ ወጣቶች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተፋጠው አንደነበረና እነሱን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ መጠቀማቸውንና ወጣቶቹም ድንጋይ ሲወረውሩ መመልከቱን አንድ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ይህንንም ተከትሎ በሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ አንዳንድ ሰዎች ቢናገሩም እስካሁን የተረጋገጠ ነገር የለም።

የሲዳማ ዞን አስተዳደር፣ የአገር ሽማግሌዎችና የፖለቲካ ቡድኖች ህብረተሰቡ የቀረበውን መፍትሄ እንዲቀበልና በትዕግስት እንዲጠባበቅ ጥሪ እያቀረቡ ነው።