በሐዋሳ ለግርግሩ ተጠያቂ የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆናቸው ተገለፀ

ሀዋሳ የነበረው አለመረጋጋት Image copyright Reuters

ዛሬ ረፋድ ላይ በሐዋሳ ከተማ አለመረጋጋቶች ቢኖሩም አሁን አንፃራዊ መረጋጋት እንዳለ የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ተጠባባቂ ቢሮ ሃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በሁሉም ከተማይቱ አካባቢ የተፈጥረውን ግጭትና ሁከት ለመቆጣጠር እንደተቻለ ገልፀው ለግርግሩ ተጠያቂ የተባሉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል መጠናከሩንም ጨምረው ተናግረዋል።

ግጭቱ የተነሳው ሐምሌ 11፣2011 ዓ.ም የሲዳማ ክልልነት መታወጅና በዞኑ ምክር ቤት ተወስኖ ይፋ መሆን አለበት በማለት በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሰንደቅ አላማና ታፔላዎችን መትከል አለብን በሚል ኃሳብ የተነሱ ወጣቶች ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመጋጨታቸው እንደሆነ ኃላፊው ይናገራሉ።

ለሲዳማ ክልልነት 'ይሁንታ ተሰጠ' በሚል በርካቶች ደስታቸውን እየገለጹ ነው

በሐዋሳ ውጥረት ነግሷል ተባለ

ስጋት ያጠላበት የሲዳማ የክልልነት ጥያቄና የሀዋሳ ክራሞት

በርከት ያሉ ከከተማም ሆነ ከገጠር የመጡ ወጣቶች ወደ ባህላዊ ስፍራ መሰብሰቢያና ሌሎች አካባቢዎች በጥዋት ሲንቀሳቀሱ እንደነበርና በኋላም ስብስቡ እንደጨመረ ይናገራሉ።

በተለይም በተለምዶ አቶቴ፣ ዲያስፖራ፣ አዲሱ ገበያና ዶሮ እርባታና በሚባሉ አካባቢዎች ላይ ሰፋ ያለ ግጭት ነበር ይላሉ።

የፌደራል ፖሊስ፣ መከላከያ፣ የክልሉ ኃይልና እንዲሁም መደበኛ ፖሊስ በጋራ በመቀናጀት እነዚህ አካባቢዎች ላይ እንደተረባረበ ገልፀው በተለይም የመንገድ መዝጋት ስራዎች በስፋት እንዳይቀጥሉ እንደተሰራም ኃላፊው አስረድተዋል።

Image copyright Reuters

በዚህም ውስጥ ለውስጥ ባሉ መንገዶች ላይ ጎማ የማቃጠል መንገድ የመዝጋት ስራዎችም ቢኖሩም አሁን መንገዱን የመክፈት ስራም እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል።

አንዳንድ የአይን እማኞች የተኩስ ልውውጥ ነበረ ቢሉም ኃላፊው በበኩላቸው "ከተኩስ በመለስ በትዕግስት ሰራዊቱ ይሄንን ግርግርና ግጭት ለማረጋጋት ጥረት እያደረገ ነው እስካሁን የቆየው፤ በዚህ ቦታ ላይ የተፈጠረ ተኩስ አለ የሚል ሪፖርት የለንም። " ብለዋል።

ዝርዝሩ በቀጣይ ቀናት የሚታወቅ ይሆናል በማለት "በተጨባጭ ግን በአብዛኛው ሊባል በሚችል ሁኔታ ወደ ከፋ እርምጃ ሳይሄዱ የተሰበሰቡና ግርግር የሚፈጥሩ ኃይሎችን ለመበተን ጥንቃቄ በተሞላ ሁኔታ ተሰርቷል" ብለዋል።

የተገደለ ሰው እንዲሁም በአካባቢው የቆሰሉ ሰዎች አሉ ቢባልም ኃላፊው እስካሁን ባለው ምርመራ የደረሳቸው መረጃ እንደሌለ ገልፀው ነገር ግን "በርካታ ግጭቶች ስለነበሩ መቁሰል ሊኖር ይችላል" ብለዋል። ዝርዝሩ በቀጣይ ምርምር እንደሚገለፅ ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች