ከሐዋሳ ተነስቶ በሌሎች አካባቢዎች ጉዳት ያደረሰው ሁከት

የሲዳማ ክልልነትን ሲያውጁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ትናንት ሐዋሳ ውስጥ ከተቀሰቀሰው ግርግር ጋር በተያያዘ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት አብቅቶ ዛሬ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

በሐዋሳ ከተማ ውስጥ የጸጥታው ስጋት እንዳለ ቢሆንም በዛሬው እለት አንዳንድ የንግድ ተቋማት መከፈታቸውንና የተወሰኑ ባጃጆች በመንገዶች ላይ እንደሚታዩ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከትናት ጀምሮ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን የዋይፋይ ኢንትርኔት አገልግሎትም መቋረጡን በከተማዋ ከሚገኙ ሁለት ሆቴሎች ለማረጋገጥ ችለናል።

የተፈጠረውን ችግር ተከትሎም ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ተይዘው መታሰራቸውን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የከተማዋ ፖሊስ አባል፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ትናንትና ማታ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ወጣቶችን ለማስፈታት ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ የተናገሩት አንድ የሀገር ሽማግሌ ትናንት ከነበረው የተሻለ ሰላም በከተማዋ እንደሚታይ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የተፈጠረውን ችግር ለመቆጣጠር በከተማዋ ውስጥ ከወትሮው በተለየ የተሰማሩት የክልሉ ልዩ ኃይል፣ መከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት በብዛት እንደሚገኝ የተናገሩት ነዋሪዎች ውጥረቱ እንዳለ መሆኑን አልሸሸጉም።

ክስተቱ ከሐዋሳ ከተማ ባሻገር በሌሎች ቦታዎችም ጉዳትን አስከትሏል። ከእነዚህም መካከል ይርጋለም፣ አለታወንዶ፣ በንሳና ለኩ አካባቢዎች ችግር እንደነበረ ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በንግድ ሥራ ለረዥም ዓመት በአለታ ወንዶ ይተዳደሩ የነበሩ አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ትናንትና ከተማዋ ላይ የተፈጠረውን ሲያስረዱ "አላታ ወንዶ የሆነውን አይደለም ተነግሮ በቪዲዮ ብታየው አታምነውም" ይላሉ።

በአለታወንዶ በተለምዶው አረብ ሰፈር በሚባለው አካባቢ በሚገኙ የጣቃ ጨርቅ መሸጫ ሱቆች ላይ እንዲሁም ታእዋን ሰፈርና መናኽሪያ አካባቢ የሚገኙ ሱቆች እንዲሁም ከመናኽሪያ ጀርባ ባሉ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ንብረቶች መውደማቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ከከተማዋ አጎራባች ቀበሌ የመጡ ወጣቶች ከተወሰኑ የከተማዋ ወጣቶች ጋር አንድ ላይ በመሆን የነጋዴዎችን የስም ዝርዝር ይዘው ንግድ ቤታቸውና መኖሪያ ቤታቸው ላይ ጥቃት አድርሰዋል ይላሉ።

ግለሰቡ አክለውም የተደበደበ ወይንም የሞተ ሰው መኖሩን ባያውቁም እያንዳንዱ ከሌላ አካባቢ የመጣ ነጋዴ ቤትና የንግድ ስፍራ እየተገባ ንብረቱ፣ ገንዘቡ እየወጣ ሲቃጠል እንደተመለከቱ ተናግረዋል።

ወጣቶቹ ንብረት ከማቃጠል ውጪ ዘረፋ እንዳልፈጸሙ ገልፀው በከተማዋ አሉ የሚባሉ ንግድ ቤቶች ላይ በአጠቃላይ ጉዳት መድረሱን አብራርተዋል።

የአስናቀ ገብረኪዳን ሆቴል የመኝታ ክፍሎችና የግለሰቡ መኪና መቃጠሉን እንዲሁም በተለምዶ ታይዋን የሚባለው አካባቢ የሚገኙ የንግድ ሱቆች ንብረት በአጠቃላይ መቃጠሉን ይናገራሉ።

የከተማዋ ወጣቶች ከቀኑ አራት ሰዓት ጀምረው ንብረት ማውደም መጀመራቸውን በማስታወስ ቀኑን ሙሉ የከተማዋ ፖሊስ ምንም እንዳልረዳቸው በምሬት ያስረዳሉ።

ማታ ተኩስ እንደነበርና ዛሬ ማለዳ ግን የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት ወደከተማዋ መግባቱን፣ የከተማዋ እንቅስቃሴም ሙሉ በሙሉ መገታቱን ገልጸው፤ የከተማዋ ፖሊስም እየተዘዋወረ ሰዎች ከቤት እንዳይወጡ እያሳሰበ እንዳለ ተናግረዋል።

የአለታወንዶ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ፍሬው ዓለሙ ትንናት በከተማዋ አለመረጋጋት ተከስቶ እንደነበር ለቢቢሲ አረጋግጠው በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመድረሱንና ዛሬ የመከላከያ ሠራዊት ስለገባ ዛሬ ከተማዋ በአንጻራዊነት ሰላም መሆኗን ገልፀዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የይርጋለም ነዋሪ ከተማዋ ትላንት ከረፋድ ጀምሮ ሰላም እንደራቃት ተናግረዋል። "ትላንት ከአራት ሰዓት በኋላ ነገሮች ቀስ በቀስ እየተለወጡ መጡ፤ ሰዎች ተደብድበዋል፣ የተዘረፉና የተቃጠሉ ቤቶች አሉ፣ ሁለት የከተማ አስተዳደር መኪናዎችና አንድ የዱቄት ፋብሪካም ተቃጥሏል" ሲል የተፈጠረውን ገልጿል።

በይርጋለም ከተማ የክልሉ ገዢ ፓርቲ ደኢህዴን ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ባጢሶ ባቲሶ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በከተማው ከትናንት ማለዳ ጀምሮ አለመረጋጋት ተፈጥሮ እንደነበር አረጋግጠዋል።

በዚህም አራዳ በሚባል አካባቢ የሰባት ግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች፣ በሌላ ስፍራ ደግሞ ሦስት ቤቶች መቃጠላቸውን፣ የዱቄት ፋብሪካ መቃጠሉን፣ የከንቲባውና የድርጅት ጽህፈት ቤቱ መኪኖች፣ የበጎ አድራጎት ድርጅት መኪና፣ የአረጋሽ ሎጅ ሦስት መኪኖች መቃጠላቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

ዛሬ ረብሻ ባይኖርም ውጥረቱ እንዳልረገበ ያነጋገርነው ነዋሪ ተናግሯል። አክሎም በከተማዋ ውስጥ የመከላከያ ሠራዊት እንደሚገኝም ገልጿል።

በከተማዋ ውስጥ የመጓጓዣ አገልግሎት ካለመኖሩ ባሻገር የንግድ ተቋማትም መዘጋታቸውን ነዋሪው የተናገረ ሲሆን፤ "ባንክ ዝግ ነው፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም እንደተዘጉ ናቸው" ብሏል።

ትላናት በነበረው ተቃውሞ አንድ ሰው መሞቱ እና ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን መስማቱም ነዋሪው ገልጿል። የሞተው ግለሰብ የተቃውሞው አካል የነበረ ሳይሆን ለንግድ ከገጠር ወደ ከተማ የሄደ ሰው መሆኑንም አክሏል።

ለዓመታት ሲንከባለል የመጣው የክልልነት ጥያቄ ሐምሌ 11/ 2011 ዓ. ም ምላሽ ያገኛል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅትና የሃገር ሽማግሌዎች ከመንግሥት ጋር ሲደራደሩ ቆይተው ሳለ ምርጫ ቦርድ፣ የክልሉ ፕሬዝዳንትና የዞኑ አስተዳዳሪ በስተመጨረሻ የሰጡት መግለጫ የፈጠረው ፍጥጫ የግጭቱ መንስኤ እንደሆነ ነዋሪው ተናግሯል።

ነዋሪው እንዳለው፤ ትላንት "ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ይከበር"፣ "መንግሥት ለጥያቄያችን መልስ ይስጥ" የሚሉ መፈክሮች ወደ ጉዳና ከወጡት ሰልፈኞች ይሰሙ ነበር።

የድርጅት ኃላፊው በግጭቱ ከገጠር ቀበሌ የመጣ ነው የተባለ ግለሰብ ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት መሞቱን አረጋግጠው አስክሬኑ ወደ መኖሪያ አካባቢው መሸኘቱንም ጨምረው አረጋግጠዋል።

በከተማዋ ቤት ንብረታቸው የተቃጠለባቸው ከሌላ አካባቢ የመጡ ሰዎች ናቸው ይባልል ተብለው ማብራሪያ የተጠይቀው ሲመልሱ፤ ንብረታቸው ያልተነካባቸው የሌላ ብሔር ተወላጆች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ባጢሶ ቤታቸው የተቃጠለባቸው ሰዎች ክልል እንዳይሰጠን ያደረጉ ሰዎች ናቸው የሚሉ ሰዎች መኖራቸውን መስማታቸውን ተናግረው በርግጥም ጥቃት አድራሾቹ መርጠው ማቃጠላቸውን ተናግረዋል።

ከትናንትና ማታ ጀምሮ ወደ ከተማው ተጨማሪ የመከላከያ ኃይል መግባቱን የተናገሩት ኃላፊው ትናንት ጥፋት ካደረሱ ወጣቶች መካከል የተያዙ ስለመኖራቸው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

ከሐዋሳ እስከ ዲላ ያለው አንዲሁም እስከ አለታ ወንዶ የሚወስደው መንገድም ስለተዘጋ የመከላከያ ሠራዊት አንደልብ መንቀሳቀስ አልቻለም ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ናቸው። የድርጅት ኃላፊውም መንገዶች ዝግ መሆናቸውን አልሸሸጉም።

"ይርጋለም ዛሬ በአንፃራዊነት ሰላም ናት" ያሉት ኃላፊው ከገጠር ከተሞች ወደ ከተማዋ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከመከላከያና ከቀበሌ አስተዳደሮች ጋር በመነጋገር ለጊዜው መገታታቸውን ገልጠዋል።

በአጠቃላይ በሲዳማ ዞን ስላለው ሁኔታ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የደወልንላቸው የሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት በሥራ መደራረብ ምክንያት ለጥያቄያችን ምላሽ ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጠውልናል።

በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ሁከት መጠኑ በውል ያልታወቀ ንብረት መውደሙን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችና የአካባቢ ባለስልታናት ያረጋገጡ ሲሆን በሰው ላይ ደረሰን ጉዳት በተመለከተ አሃዞች ከተለያዩ ወገኖች እየወጡ ቢሆንም ለማረጋገጥ አዳጋች ሆኗል።