ቦይንግ በ 737 ማክስ ምክንያት አምስት ቢልየን ዶላር ማውጣቱ ተገለጸ

ቦይንግ 737 Image copyright Reuters

የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በመላው ዓለም እንዳይበር መደረጉን ተከትሎ ቦይንግ ወጪዎቹን ለመሸፈን 4.9 ቢልየን ዶላር አውጥቷል።

የዓለም ትልቁ አውሮፕላን አምራች ቦይንግ፤ በሚቀጥለው ሳምንት የስድስት ወር ሪፓርት ሲያቀርብ ወጪው ከገቢው እንደሚበልጥም ተገልጿል።

ቦይንግ ባወጣው መግለጫ፤ አውሮፕላኖቹ በዚህ ዓመት መጨረሻ ሦስት ወራት ወደ ሥራ ይመለሳሉ ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ይፋ አድርጓል።

737 ማክስ ኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ ውስጥ ተከስክሶ 346 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

ቁጥር አንድ አውሮፕላን አምራች የነበረው ቦይንግ ታይቶ የማይታወቅ ውጥንቅጥ ውስጥ ገብቷል። አደጋዎቹን ተከትሎ አሁን ላይ አውሮፕላኖቹ በመላው ዓለም ታግደዋል።

ኢንዶኔዥያ፡ የሟቾች ቤተሰቦች በቦይንግ ካሳ ተጭበርብረናል አሉ

አደጋውን የመረመሩ ባለሙያዎች ችግሩ የነበረው የአውሮፕላኑ መቆጣጠሪያ ላይ እንደነበረ መናገራቸውን ተከትሎ፤ ቦይንግ ሶፍትዌሩን እያሻሻለ መሆኑን ተናግሯል።

አውሮፕላኖቹ እንዲበሩ ይለፍ በመሰጠቱ እየተወቀሰ ያለው አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ፤ አየር መንገዶች ምርቶቹን እየገዙ ስላልሆነ ወርሀዊ የምርት መጠኑን ከ52 ወደ 42 ለመቀነስ ተገዷል።

ቦይንግ 4.9 ቢልየን ዶላር ያመጣው የበረራ ሰዓት ለተስተጓጎለባቸው ደንበኞቹ ካሳ እንዲሁም ለዘገዩ አውሮፕላኖች ማካካሻ ነው።

የቦይንግ የፋይናንስ ኃላፊ ግሬግ ስሚዝ ድርጅታቸው ነገሮችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየሠራ መሆኑን ተናገረዋል።

ቦይንግ 737 ማክስ ሌላ ችግር ገጥሞታል

የቦይንግ ሊቀ መንበር ዴኒስ ሙለንበርግ "ቅድሚያ የምንሰጠው ለተሳፋሪዎቻችን እና የበረራ ሠራተኞች ደህንነት ነው" ብለዋል። ድርጅቱ የገጠመው ችግር በገቢው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩንም አክለዋል።

ቦይንግ 737 ማክስን ወደ በረራ ለመመለስ ከአቪየሽን ባለ ሥልጣኖች ጋር እየሠራ መሆኑን ይፋ አድርጓል። በያዝነው ዓመት ማገባደጃ አካባቢ አውሮፕላኖቹ በረራ እንደሚጀምሩም ተስፋ አድጓል።

ቦይንግ ባቀደው ጊዜ ማክስ 737 ካልበረረ የባሰ ኪሳራ ውስጥ እንደሚገባም ተናግሯል። ባለፈው ሀሙስ የአሜሪካ የትራንስፖርት አመራር ቦይንግ በዚህ ዓመት በረራ ስለመጀመሩ እርግጠኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል።

ቦይንግ "ችግሩ ተፈቷል" እያለ ነው

የፌደራል አቪየሽን አድሚንስትሬሽን ወይም ኤፍኤኤ ሂደቱን በአንክሮ እየተከታተለ መሆኑን ኤሌን ኤል ቻዮ ተናግረዋል። አውሮፕላኑ የደህንነት ስጋት እንደሌለበት ሲገራገጥ እግዱ እንደሚነሳለትም አስረድተዋል።