ሂትለርም ልክ እንደግራዚያኒ የግድያ ሙከራ እንደተደረገበት ያውቃሉ?

ሙሶሎኒና ሂትለር ቦምቡ የፈነዳበትን መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲጎበኙ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ሙሶሎኒና ሂትለር ቦምቡ የፈነዳበትን መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲጎበኙ

እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በጁላይ 20፣ 1944 ዓመተ ምሕረት አንድ የ36 ዓመት ወታደራዊ መኮንን እጅግ ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግበት ሕንጻ ሾልኮ ገባ። ሾልኮ እንኳ አልገባም፤ ኮራ ብሎ ነው የገባው። ምክንያቱም ፕሮቶኮሉ ያን ለማድረግ ይፈቅድለታል።

ሕንጻው እጅግ ምስጢራዊና የፕረሺያ ጫካ ውስጥ የሚገኝ ነበር። አዶልፍ ሂትለርና የጦር መኮንኖቹ ስብሰባ ነበራቸው።

እንዲያውም ሂትለር ምሥጢራዊው ቢሮው እዚያ ጫካ ውስጥ ነው የነበረው ይባላል።

ይህ ወጣት መኮንን ታዲያ ዕለታዊ መመሪያ ለመቀበል ነው ወደ ሕንጻው የገባው። ይህ የተለመደ ተግባር ነው። የተለመደ ያልሆነው መኮንኑ የያዘው ሳምሶናይት ነው።

በእጁ አንድ ሳምሶናይት ይዞ ነበር። በውስጡ የጦር ካርታ አልነበረም የታጨቀው፤ ቦምብ እንጂ። የዓለም እጅግ አስፈሪውን ሰው አዶልፍ ሂትለርን ለመግደል የተቀመመ ቦምብ።

ለልጃቸው "ሂትለር" የሚል ስም የሰጡ እናትና አባት ተፈረደባቸው

የሂትለር ሥዕሎች ለምን አልተሸጡም?

ቻይናዊው የመብት ተሟጋች ታሠረ

ምሥክርነት

በወቅቱ እዚያ ሕንጻ ከነበሩት መኮንኖች አንዱ ጄኔራል ዋልተር፣ በ1967 ለቢቢሲ ቃለምልልስ ሰጥቶ ነበር።

"ክብ ሰርተን ቆመን እያለ ሂትለር መጣና ወደ ስብሰባ አዳራሹ ገባን። ድንገት የስብሰባ አዳራሹ በር በድጋሚ ተከፈተና ይሄ ወጣት መኮንን ገባ፤ እኔን ፊት ለፊት ነበር የሚመለከተኝ፤ አንድ ዓይኑ በጨርቅ ተሸፍኖ ነበር፤ አንድ ክንዱ የተቆረጠ መኮንን ነው። ሂትለር ፊቱን አዙሮ በግዴለሽነትና ተመለከተው...።"

ይህ መኮንን ግራ እጁንና አንድ ዓይኑን ያጣው ቱኒዚያ በጦርነት ላይ ሳለ ነበር። ያን ጊዜ አካል መጉደል ብርቅ አይደለም፤ እንዲያውም ተራ ነገር ነው።

መኮንኑ እኮ መጀመርያ የናዚ ጀርመን ደጋፊም ነበር፤ አክራሪ ብሔርተኛም ነበር። ኋላ ላይ ግን ጦርነቱ እያመጣ ያለውን ጥፋት ሲመለከት ልቡ ሸፈተ።

በዚህ ስሜት ላይ ሳለ ታዲያ በሂትለር ላይ እየዶለቱ የነበሩ ጄኔራሎች አገኙት። ጥሩ አጋጣሚ ነበር። ይህንን አኩራፊ ቡድን ይመሩት የነበሩት ጄኔራል ትሬስኮቭ ነበሩ። ዋናው ግባቸው ሂትለርን ገድሎ የናዚን ሥርዓት እስከናካቴው መቀየር ነበር። ይህ መኮንን ሙሉ ስሙ ክላውስ ቮን ስታፈንበርግ ይባላል። ሳያቅማማ ሁነኛ አባላቸው ሆነ።

Image copyright GERMAN FEDERAL ARCHIVE
አጭር የምስል መግለጫ ሂትለር ያን ጊዜ ቦምቡ ሲፈነዳ ለብሶት የነበረው ሱሪ

የሳምሶናይቱ ቦምብ

በ1944 መኮንን ክላውስ ቮን ስታፈንበርግ የጀርመን ተተኪ ጦር መሪ ሆኖ ተሾመ። ይህ ሥልጣኑ ታዲያ ከሂትለር ጋ በቅርብ ለመገናኘት መልካም አጋጣሚን ፈጠረለት።

አፈንጋጩ ቡድን ታዲያ ሂትለርን እስከወዲያኛው ለማጥፋት ከዚህ የተሻለ ዕድል እንደሌለ በማመን የሞት ድግስ መደገስ ያዘ።

እቅዱ በአጭሩ የሚከተለውን ይመስላል፦

መኮንን ስታፈንበርግ ለስብሰባ ወደ አዳራሹ ሲገባ በሳምሶናይቱ ቦምብ ይዞ እንዲገባ፣ ሳምሶናይቱን ከሂትለር አቅራቢያ ጠረጴዛ ሥር እንዲያስቀምጠውና ከዚያ ይቅርታ ጠይቆ ከስብሰባው እንዲወጣ፤ ከዚያ ግቢውን ለቆ በፍጥነት ወደ በርሊን ተመልሶ ሥዒረ መንግሥቱን የዶለቱትን ጄኔራሎች እንዲያገኝ፤ በመጨረሻም ተጠባባቂውን ጦር በመምራት ጀርመንን በቁቁጥር ሥር ማዋል ነበር ሐሳቡ።

በሳምሶናይቱ ውስጥ ያለው ቦምብ ልክ 12፡30 ሲሆን እንዲጎን ሰዓቱ ተስተካከለ፤ ነገር ግን መኮንኑ አንዱን ሰዓት እንደሞላ ሌላኛውን ሳያዘጋጅ ሰው መጣበት፤ ሳምሶናይቱን ዘግቶ ባልተቆረጠው እጁ አንጠልጥሎት ወደ ስብሰባው ገባ።

በ1967 ለቢቢሲ ምስክርነታቸውን የሰጡት ጄኔራል እንደሚሉት ወጣቱ መኮንን ወደ ስብሰባ አዳራሹ ጥቁር ሳምሶናይት ይዞ ሲገባ እንደሚያስታውሱ ከዚያ በኋላ ግን ጠረጴዛ ሥር ሲያስቀምጠውና ክፍሉን ለቆ ሲወጣ እምብዛምም ትዝ እንደማይላቸው ተናግረዋል።

Image copyright AP
አጭር የምስል መግለጫ መኮንኑ ከልጆቹ ጋ

ድንገት ፍንዳታ ተሰማ።

ስታፈንበርግ ግቢውን ሲለቅ ፍንዳታውን ሰምቶታል። ሂትለር ስለመገደሉ እርግጠኛ ሆኖ ነበር ወደ በርሊን የተሳፈረው።

የሚገርመው ግን ፍንዳታው ከመከሰቱ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በአጋጣሚ ሳምሶናይቱ ከሂትለር እግር ሥር ገለል ተደርጎ ነበር። ቦምብ ስለመሆኑ ግን ተጠርጥሮ አይደለም፤ እንዲሁ አለ አይደል...? ሂትለርም ከተቀመጠበት ተነስቶ ለወታደሮቹ የጦር ካርታ እያመላከተ ነበር፤ ስለዚህ በሳምሶናይቱና በሂትለር መሀል ርቀት ተፈጠረ፤ ቦምቡ ሲፈነዳ ሂትለር ተረፈ፤ አራቱ ጄኔራሎች እዚያ ጭጭ አሉ።

ሂትለር አብቅቶለታል ያሉት የተጠባባቂ ጦር አባላት አገሪቱን ለመቆጣጠር ተንቀሳቀሱ፤ በአንጻሩ የሂትለር ጦር ደርሶ አደናቸው፤ ከያሉበት ተለቅመው ታጎሩ፤ ዋናዎቹ 200 የሚሆኑት በነገታው በጥይት ተደብድበው ተገደሉ። ስታፈንበርግም እንደዚያው።

ይህን አዶልፍ ሂትለርን ለመግደል የጀገነን ወጣት መኮንን ለመዘከር መራሂተ መንግሥት አንጌላ ትናንት በርሊን በሚገኝ ኢግዚብሽን ላይ ተገኝተው ነበር፤ ለ75ኛ ዓመት ክብረ በዓል።

ማርከል የያን ጊዜውን መኮንን ድርጊት ካሞካሹ በኋላ አሁን ጊዜው ጽንፈኛ ቀኝ አክራሪዎችን የምንመክትበት ጊዜ ነው ብለዋል። በጀርመን የቀኝ አክራሪዎች ድጋፍ ከዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል። ቢያንስ 24ሺ የሚሆኑ የአክራሪ የቀኝ ዘመም ደጋፊዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ለናዚና ለአዶልፍ ሂትለር ስሱ ስሜት ያላቸው ናቸው።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ክላውስ ቮን ስታፈንበርግ

የዚህ ወጣት መኮንን ጀብድ በ2008 የተዋጣለት ፊልም መሆን ችሎ ነበር። ቶም ክሩዝ የሚተውንበት ይህ ፊልም «ኦፕሬሽን ቫልኬሪ» ይሰኛል።

ድርጊቱ ከኛዎቹ አብረሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ፋሺስቱን ግራዝያኒን ለመግደል ካደረጉት ሙከራ በመጠኑ የሚመሳሰል ይመስላል። ይህ የጀርመን ታሪካዊ ኩነት በዓለም ታሪክ እምብዛምም ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል። አሁን ግን ለመኮንኑ በጀርመን የአርበኞች መታሰቢያ ማዕከል ሀውልት ቆሞለታል።

የመኮንኑን መገደል ተከትሎ ባለቤተቱ በጌስታፖ ራቬንስበረክ ማጎርያ ማዕከል እንድትገባ ተደርጋ ነበር። ከጦርነቱ ማብቂያ በኋላ ነጻ ወጥታለች። ሆኖም ሌላ ባል ሳታገባ ለርሱ ታማኝ እንደሆነች ኖራለች። የግድያ ሙከራው በከሸፈ ማግስት የመኮንኑ የልጆች ማደጊያ ካምፕ ተወስደው ስሞቻቸው ተቀይረው እንደ አዲስ እንዲኖሩ ተደርገዋል። ይህ ከሂትለር ሰዎች የማይጠበቅ መልካምነት ይመስላል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ