ቦሌ አየር ማረፊያ በታሪኩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ደንበኞች አስተናገደ

አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ Image copyright MICHAEL TEWELDE
አጭር የምስል መግለጫ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ

አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ባሳለፍነው ረቡዕ ሐምሌ 10 ፣2011 ዓ.ም. ላይ ብቻ 29ሺህ 528 ዓለም አቀፍ ተጓዦችን በማስተናገድ በታሪኩ በአንድ ቀን ውስጥ አስተናግዶ የማያውቀውን ቁጥር አስመዝግቧል።

ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው አንድ የአየር መንገዱ ባልደረባ ለቢቢሲ እንደጠቆሙት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል የሚያልፉ ወይም መዳረሻቸው ኢትዮጵያ ያደረጉ ተጓዦች ቁጥር መናር አንዱ ምክንያት ከፈረንጆቹ በጋ (summer) ወቅት ጋር የተያያዘ ነው።

የፈረንጆቹ ሞቃታማ ወቅት በርካታ የምዕራባውያን ሃገራት ዜጎች ለጉብኝት ከሃገር ወደ ሃገር የሚንቀሳቀሱበት ወቅት ነው።

ሌላኛው በቦሌ አየር ማረፊያ የዓለም አቀፍ ተጓዦች ቁጥር መጨመር ምክንያቱ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዝና እና የአውሮፕላኖቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ እንደሆነ መረጃውን ያቀበሉን የአየር መንገዱ ባልደረባ ነገረውናል።

አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ፤ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ረቡዕ ሐምሌ 10 ላይ ብቻ 310 በረራዎችን ያስተናገደ ሲሆን በእነዚህ በረራዎች 21ሺህ 28 ተጓዦች መነሻቸውን ከቦሌ አየር ማረፊያ ያደረጉ ሲሆን፤ 8 ሺህ 500 የሚሆኑት ደግሞ መዳረሻቸውን ቦሌ አየር ማረፊያ ያደረጉ ናቸው ።

በተመሳሳይ መልኩ የአየር መንገዱ መግለጫ ይህ ቁጥር የቦሌ አየር ማረፊያ ደንበኞች ማስተናገጃ ተርሚናል በታሪኩ አይቶት የማያውቀው ነው ብሏል።

"የሞተው የኔ ያሬድ ነው ብዬ አላሰብኩም" የካፕቴን ያሬድ የ11 አመት ጓደኛ

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአደጋው በኋላ

የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታነህ አደራ፤ "እየተስፋፋ ያለው እና በከፊል ክፍት የተደረገው የአየር ማረፊያው የመንገደኞች ማስተናገጃ፤ መንገደኞች የማስተናገድ አቅምን በእጥፍ በላይ ለማሳደግ አቅም ይፈጥራል።" ብለዋል።

አቶ ጌታነህ ጨምረውም ''በዚህ የፈረንጆቹ ሞቃታማ ወቅት ታይቶ የማይታወቅ የመንገደኞች ቁጥር ለማስተናገድ ዝግጁ ነን"ብለዋል።

በመላው ዓለም ከ120 በላይ መዳረሻዎች ያሉት አየር መንገዱ፤ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የሚያርፉ እና ሚነሱ የአውሮፕላኖች ቁጥርን በመቶዎች እንዲቆጠሩ አስችሏል።

በቦሌ አየር ማረፊያ እየተደረገ ያለው የማስፋፊያ ፕሮጄክት አየር ማረፊያ በዓመት እስከ 22 ሚሊዮን ደንበኞችን ማስተናገድ እንዲያስችል አቅም ይፈጥርለታል ተብሎ ይጠበቃል።

እንደ ኤርፖርትስ ካውንስል ኢንተርሽናል ሪፖርት ከሆነ፤ በጆርጂያ ግዛት አትላንታ ከተማ የሚገኘው አትላንታ-ህርትስፊልድ-ጃክሰን አየር ማረፊያ በዓመት 107 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን በማስተናገድ የዓለማችን በርካታ ተጓዦችን የሚያተናግድ አየር ማረፊያ ተብሏል።

የቻይናው ቤይጂንግ አየር ማረፊያ ደግሞ በዓመት 100 ሚሊዮን ተጓዦችን በማስተናገድ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ዱባይ አየር ማረፊያ፣ ሆንግ ኮንግ አየር ማረፊያ፣ በቴኔሲ አሜሪካ የሚገኘው ሜምፊስ አየር ማረፊያ እና ሻንጋይ አየር ማረፊያ በርካታ ተጓዦችን በማስተናገድ የሚጠቀሱ መዳረሻዎች ናቸው።