በመድፈር የተወነጀለው ሮናልዶ አይከሰስም ተባለ

ክርስቲያኖ ሮናልዶ Image copyright Getty Images

የአሜሪካ አቃቤ ሕግ ክርስቲያኖ ሮናልዶ አስገድዶ በመድፈር እንደማይከሰስ አስታወቀ።

የ34 ዓመቷ ካትሪን ማይርጋ፤ ሮናልዶ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2009 አሜሪካ፣ ላስ ቬጋስ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ አስገድዶ እንደደፈራት መናገሯ ይታወሳል።

ካትሪን ማይርጋ እና ፖርቹጋላዊው እግር ኳስ ተጫዋች ሮናልዶ 2010 ላይ ያለ ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብነት ስምምነት ማድረጋቸው ተገልጿል። ሮናልዶ በካትሪን የቀረበበትን ውንጀላ ባይቀበልም፤ 2018 ላይ ክስ ከፍታለች።

ሮናልዶ "ደፍሮኛል" ያለችው ሴት ከመብት ተሟጋቾች ድጋፍ አገኘች

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ከቀረበበት የመድፈር ክስ ጋር በተያያዘ የዘረመል ናሙና እንዲያቀርብ ታዘዘ

ናይኪ ሮናልዶ ላይ የቀረበው ውንጀላ"አሳስቦኛል" አለ

ትላንት የላስ ቬጋስ አቃቤ ሕግ በሰጡት መግለጫ "ክሱን የሚያጠናክር ማስረጃ የለም" ብለዋል።

ካትሪን መደፈሯን ሪፓርት ያደረገችው 2009 ላይ ነበር። በወቅቱ ማን፣ የት እንደደፈራት በይፋ ለመናገር ፈቃደኛ አልነበረችም። "ስለዚህም ፖሊሶች ምርመራ ማድረግ አልቻሉም ነበር" ተብሏል።

ነሀሴ 2018 ላይ ምርመራ ይደረግልኝ ብላ በመጠየቋ፤ የላስ ቬጋስ ፖሊስ በድጋሚ ጉዳዩን መመርመር ጀምሯል።

አቃቤ ሕግ በመግለጫው "አሁን በእጃችን ያለውን መረጃ ስንፈትሽ፤ ከቀረበው ክስ ባሻገር ክርስቲያኖ ሮናልዶ ወሲባዊ ጥቃት ስለማድረሱ ማስረጃ ስለሌለን ሮናልዶ አይከሰስም" ብሏል።

አምና ክሱን ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረገው 'ደር ስፒግል' የተባለ የጀርመን ጋዜጣ ነበር። 2010 ላይ ካትሪን ክሱን በይፋ እንዳታቀርብ ከሮናልዶ ጋር በ375,000 ዶላር ተስማምተው እንደነበር ተገልጿል።

የካትሪን ጠበቃ እንዳሉት፤ ካትሪን መደፈሯን በይፋ ተናግራ ክስ ለመመስረት የወሰነችው በ 'ሚቱ' (#MeToo) ንቅናቄ ተነሳስታ ነው።

ሮናልዶ ከካትሪን ጋር 2009 ላይ ላስ ቬጋስ ውስጥ እንደተገናኙ ባይክድም፤ በመሀከላቸው የተፈጠረው ነገር "በጋራ ስምምነት የተደረገ" እንደነበረ ገልጿል።

በወቅቱ የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች የነበረው ሮናልዶ ወደ ሪያል ማድሪድ እየተዘዋወረ ነበር። ሮናልዶ አሁን ለጁቬንቱስ ይጫወታል። አምስት ጊዜ የዓለም ምርጥ ኳስ ተጫዋች ተብሏል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ