ኢራን የ 'ሲአይኤ ሰላይ' ያለቻቸውን በሞት እቀጣለሁ አለች

በኢራን የኒውክሌር ፕሪግራም ሳቢያ ሁለቱ አገራት እንደተፋጠጡ ነው Image copyright AFP/Getty Images

ኢራን ለሲአይኤ እየሠሩ ነበር ያለቻቸውን 17 ሰላዮች በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ይፋ አደረገች። ከነዚህ ገሚሱ ሞት ተፈርዶባቸዋል ተብሏል።

የኢራን የደህንነት ሚንስትር እንዳለው፤ ተጠርጣሪዎቹ ስለ ኒውክሌር፣ መከላከያ እና ሌሎችም ዘርፎች መረጃ እየሰበሰቡ ነበር።

የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን ክስ "ሀሰት ነው" ሲሉ አጣጥለዋል። በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ሳቢያ ሁለቱ አገራት እንደተፋጠጡ ነው።

ትራምፕ ከዓለም አቀፉ የኒውክሌር ስምምነት ባለፈው ዓመት ወጥተው ኢራን ላይ የንግድ ማእቀብ መጣላቸው ይታወሳል።

ኢራን የአሜሪካ የቅኝት ድሮንን መትታ ጣለች

እንግሊዝ፦ 'ከኢራን ጎን ነኝ'

ኢራን እስሩን እንዳሳወቀች "ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ እየተቸገርኩ ነው" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።

ስለ 'ሰላዮቹ' እስካሁን የምናውቀው

ኢራን ለአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይኤ ይሰራሉ ያለቻቸውን ግለሰቦች ያሠረችው ባለፉት 12 ወራት እንደሆነ ተናግራለች።

17ቱም ኢራናዊ ሲሆኑ፤ በመከላከያና ኒውክሌር ማዕከሎች አካባቢ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አንድ የኢራን ከፍተኛ የደህንነት ኃላፊ ገልጸዋል። ከታሠሩት መካከል ምን ያህሉ ሞት እንደተፈረደባቸው ያሉት ነገር የለም።

የኢራን የደህንነት ሚንስትር መሀሙድ አልቪ "ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰላዮችን እሥር የተመለከተ ዘጋቢ ፊልም በኢራን ቴሌቭዥን ይታያል" ብለዋል።

የደህንነት ተቋሙ የዘጋቢ ፊልሙን ቅንጫቢ የያዘ ሲዲ ለቋል። በሲዲው የሰላዮች ስብሰባና ቃለ ምልልስን በማስመሰል የተሠራ ትዕይንትም ይታያል።

ሚንስትሩ እንዳሉት በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል የአሜሪካ ቪዛ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ሳለ በሲአይኤ የተመለመሉ ይገኙበታል። አንዳንዶቹ ደግሞ የአሜሪካ ቪዛቸውን ለማሳደስ ሲሞክሩ ሲአይኤ ተጽዕኖ አድርጎ የመለመላቸው ናቸው ብለዋል። የተቀሩት በገንዘብ፣ በህክምና አገልግሎትና ሌሎችም ጥቅማ ጥቅሞች ተደልለዋል ሲሉም አክለዋል።

ኢራን አሜሪካ ዳግም የጣለችውን ማዕቀብ አወገዘች

ትራምፕ ጦርነት ከተጀመረ ኢራን ከምድረ ገጽ ትጠፋለች ሲሉ አስጠነቀቁ

ባለፈው ወር ኢራን ከ "ሲአይኤ የስለላ ሰንሰለት ጋር የተገናኘ" ነው ያለችውን መስመር መበጣጠሷን አሳውቃ ነበር። የአሁኑ ከዚህ ሰንሰለት ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ የተባለ ነገር የለም።

ተንታኞች ምን ይላሉ?

የአካባቢውን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች የኢራን መግለጫን በጥርጣሬ ያዩታል።

የኢራን ደህንነት ሚንስትር ባለፈው ወር የሲአይኤን የስለላ ሰንሰለት በጣጥሻለሁ ብትልም፤ አሁን ደግሞ 17 ተጠርጣሪዎችን አሥሬያለሁ ብላለች።

አንዳንዶች እንደሚሉት 17ቱ ግለሰቦች ለበርካታ ዓመታት በስለላ የተጠረሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ኢራን ውስጥ ለተለያዩ አገራት ሲሰልሉ ነበር በሚል የተጠረጠሩ ብዙ እስረኞች አሉ።

የኢራን የደህንነት ሚንስትር መግለጫ ያወጣው አዳዲስ ተጠርጣሪዎች አሥሮ ሳይሆን፤ ከሪቮሉሽነሪ ጋርዶች ጋር እየተደረገ ያለውን ፉክክር አስታክኮ ነው የሚሉም አሉ።

ኢራንና እንግሊዝ ተፋጠዋል

ከሁለት ሳምንት በፊት የኢራን ቴሌቭዥን የኢራንን የደህንነት ተቋም የሚያሞግስ ዘጋቢ ፊልም አቅርቦ ነበር። አሁን ደግሞ የደህንነት ሚንስትሩ ስኬቱን የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ሊያቀርብ ነው።

በኢራን ውስጥ ያሉት ተፎካካሪ ተቋሞች አንዳቸው ከሌላቸው የተሻሉ መሆናቸውን ለማሳየት የሚያደርጉት ጥረትም ይመስላል።

የፍጥጫው መንስኤ ምንድን ነው?

ተከታዮቹ ክስተቶች በኢራን፣ አሜሪካና እንግሊዝ መካከል ያለውን ፍጥጫ ለመረዳት ያግዛሉ።

  • ባለፈው አርብ ኢራን የእንግሊዝ ሰንደቅ አላማ ያነገበ የነዳጅ መርከብ አግታለች።
  • ባለፈው ሳምንት አሜሪካ የኢራንን ሰው አልባ አውሮፕላን መትታ መጣሏን ትራምፕ ቢናገሩም ኢራን አስተባብላለች።
  • ባለፈው ወር ኢራን የአሜሪካን ሰው አልባ አውሮፕላን መትታ ጥላለች። የኢራንን የአየር ክልል እንደጣሰ ብትናገርም፤ አሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላኑ በዓለም አቀፍ ክልል ውስጥ እየተንቀሳቀሰ እንደነበር ገልጻለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ